የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሙት ዓመት አከባበር ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ሠራተኞቹን በየደረጃው ማወያየት ጀመረ፡፡ሕዝብ በከፍተኛ ደረጃ ከመሰልቸቱ ጋር ተያይዞ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሽፋናቸው እንዲቀንስ ተደርጎ የነበሩት የአቶ መለስ ርዕሰ ጉዳይ- ሙት ዓመታቸውን ተከትሎ እንደገና አዲስ አጀንዳ ሆኗል፡፡
የአስተዳዳሩ ምንጮች እንደገለጹት የአቶ መለስን ሙት ዓመት በአረንጓዴ የልማት ዘመቻ ለማክበር ታስቦ ሥራው መጀመሩን፣ የሻማ ማብራት ስነስርዓት እንደሚኖር፣ የእሳቸውንም ራዕይ ለማሳካት የተጀመረው ጥረት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለሠራተኞቹ ተነግሯቸዋል፡፡
ባለፈው ዓርብ ዕለት የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ሠራተኞች በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በመወያየት የመለስን ራዕይ አጠናክሮ ለመቀጠል እንደሚተጉ ባወጡት የአቋም መግለጫ ጠቅሰዋል፡፡
አንዳንድ የኢህአዴግ አባላትና ካድሬዎች በስብሰባው ላይ እንደ አዲስ ሲያለቅሱም ታይተዋል፡፡
ነሐሴ 14 ቀን 2005 ዓ.ም ታስቦ የሚውለውን የአቶ መለስ ሙት ዓመት በማስመልከት ከ40 ሚሊየን ብር በላይ ይገኝበታል የተባለ በሞባይል የሚካሄድ ሎተሪ እንደሚጀመር ለሠራተኞቹ እንደተገለጸላቸው፤ ይህም ገቢ ለመለስ ፋውንዴሽን ሥራዎች ይውላል ተብሎ እንደተነገራቸው ታውቋል፡፡
የፋውንዴሽኑ የቤተመጽሐፍትና ሙዚየም ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በዚሁ ሰሞን ይጣላል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ለተመረጡ ተማሪዎች በአቶ መለስ ስም ስኮላርሺፕ መስጠትን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በእነ አርቲስት ሰርጸ-ፍሬ ስብሃት፣ ደበሽ ተመስገንና ሰራዊት ፍቅሬ የሚመራ የስነጥበብ ባለሙያዎች ቡድን ለሙት ዓመቱ ለየት ያሉ ስራዎች ለማቅረብ ደፋ ቀና እያለ እንደሚገኝ ምንጮቻችን ጠቅሰዋል፡፡
የመለስ ፋውንዴሽን በአዋጅ ቁጥር 781/2005 ተቋቁሞ በመጋቢት ወር መጨረሻ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደ ስነስርዓት በይፋ መመስረቱ የሚታወቅ ሲሆን በዕለቱም በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ በአንድ የእራት ምሽትብቻ ከ110 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡ አይዘነጋም፡፡ ፋውንዴሽኑ በአዋጅ
እንደመቋቋሙ ከመንግስት ዓመታዊ በጀት እንደሚኖረው ተመልክቷል
ፋውንዴሽኑ ባለፉት አምስት ወራት ገንዘብ ከማሰባሰብ የዘለለ የረባ ስራ አለመስራቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ገልጸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ጎዳናዎች ላይ የተሰቀሉ የአቶ መለስ ምስሎችና ፖስተሮች በክብር እንዲወርዱ በአቶ አዲሱ ለገሰ በኩል ከስድስት ወራት በፊት በይፋ የተላለፈው ጥሪ ተቀባይነት ሳያገኝቀርቷል፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ ክፍለከተሞችና ወረዳዎች ሹማምንት ትልልቅ ፖስተሮችን በውድ ክፍያ በማሰራት ጭምር ጠቀም ያለ ኮምሽን ሲሰበስቡበት መቆየታቸውን ምንጮቻችን አስታውሰው በአሁኑ ወቅትም በተለየ ምክንያት ሊወድቁ የደረሱ ምስሎችን ለመተካት በሚል የመንግስት ገንዘብ ወጪ እየሆነ አዳዲስ ፖስተሮች እየተለጠፉ መሆኑ ታውቋል፡፡
በተለይ በወ/ሮ አዜብ መስፍን የሚመራው ፋውንዴሽን ይህን አስመልክቶ እስካሁን በይፋ አቋሙን አለማሳወቁ በአቶ መለስ ስም ለመነገድ ያለውን ፍላጎት በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን የአዲስአበባው ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ሰዎች አስተያየታችውን ስጥተዋል
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar