ሀምሌ 7፣ 2005 ዓ/ም በደሴና ጎንደር ከተሞች አንድነት ፓርቲ የጠራቸው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች በታቀደላቸው ጊዜ እንደሚካሄዱ ከመንግስት እውቅና የተሰጣቸው ቢሆንም፣ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና ባለስልጣናት የቅስቀሳ ወረቀቶችን የሚበትኑትን ሰዎች ከማሰር እና ከማስፈራራት አልፈው ፣ ከአዲስ አበባ የሄዱ የፓርቲው አመራሮች አልጋ እንዳያገኙ የሆቴል ባለንብረቶችን እስከ ማስፈራራት መድረሳቸውን የፓርቲው አመራሮች ለኢሳት ገልጸዋል።
የአንድነት ፓርቲ የብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ዘካሪያስ የማነብርሀን ፣ የደሴ ከንቲባ ፣ አፈ ጉባኤውና 7 የምክር ቤት አባሎች በተገኙበት ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። የደሴ ከንቲባ አቶ አለባቸው ፓርቲው ሰላማዊ ሰልፉን ከረመዳን ጾም በሁዋላ እንዲያካሂድ ጥያቄ አቅርበዋል።
ከንቲባው ካቀረቡዋቸው ምክንያቶች መካከል “ወሩ የረመዳን ጾም የተጀመረበት በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ ጸጥ ብሎ እንዲጾም እና እንዳይረበሽ፣ በቅርቡ በደሴ ከተማ ተገደሉት ሼክ ሟች ቤተሰቦች ብስጭት ላይ ስለሆኑ በሰልፉ ላይ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ፣ ገዳዮችን ለማፈላለግ የጸጥታ ሀይሎችን ስላሰማራን ሀይል ባለመኖሩ” የሚሉት ይገኝበታል። ፓርቲው ” በቅዱስ ረመዳን ወቅት ጽዱስ ስራ መስራት ተገቢ ነው” በማለት በከንቲባው የቀረቡትን ምክንያቶች ውድቅ አድርጓል፡፡
ፓርቲው በጸጥታ ሀይሎች እየደረሱ ናቸው ያላቸውን ችግሮች ዘርዝሮ ለከንቲባው አቅርቧል። ከንቲባውም ስራችሁን ቀጥሉ ችግሮች ካሉ እንነጋገራለን ማለታቸውን አቶ ዛካሪያስ አስታውሳው ይሁን እንጅ ቅስቀሳ ለማድረግ የወጡ ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ መታሳራቸውን ገልጸዋል። የጸጥታ ሀይሎች በአንድነት አመራሮች ላይ የሚደርሱትን እንግልት የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ” ለምን?’ በማለት ሲቃወሙ መታየታቸውንም አቶ ዘካሪያስ ገልጸዋል:: በከተማዋ የሚገኙ አንዳንድ ነዋሪዎች በመጪው እሁድ በሚደረገው ሰልፍ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል
በጎንደር ከተማ ደግሞ ከአዲስ አበባ የሄዱ ፓርቲው አመራሮች አልጋ እንዳያገኙ እስከመከልከል የደረሰ እርምጃ መሰዱን የአንድነት ፓርቲ የሰሜን ጎንደር ዞን ተወካይ አቶ እእምሮ አወቀ ገልጸዋል ። በነገው እለት ከአዲስ አበባ ከሄዱት አባሎች ጋር በመሆን ወረቀት ማሰራጨት እና በመኪና ላይ ቅስቀሳ እንደሚያደርጉ አቶ አእምሮ አስታውቀዋል።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar