fredag 1. august 2014

የአዲስጉዳይ ፎቶ ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድ ተጨማሪ የ5 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባት

• መኖሪያ ቤቷ በፖሊስ ተበርብሯል
በአንዋር መስጂድ በተፈጠረው ሁከት ሳቢያ በአካባቢው በነበሩ የፀጥታ ኃይሎች የታሰረችው የአዲስጉዳይ መጽሔት ፎቶ ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድ ሐሙስ ሐምሌ 24 ቀን 2006 ዓ.ም ሜክሲኮ በሚገኘው በአዲስ አበባ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ምድብ ችሎት ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር ቀርባለች።
አዚዛ መሃመድ - የአዲስ ጉዳይ መጽሄት ፎቶ አንሺ።
አዚዛ መሃመድ – የአዲስ ጉዳይ መጽሄት ፎቶ አንሺ።
ምርመራውን በማጣራት ላይ ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል ባለፈው ሳምንት የብርበራ ትዕዛዝ በማውጣት ወደአዚዛ መኖሪያ ቤት ተጉዞ ብርበራ ማድረጉ ታውቋል። በዚህ ብርበራ ፖሊስ አዚዛን በጥርጣሬ
ከያዘበት ጉዳይ ጋር ተያያዠነት ያለው ማስረጃ እንዳላገኘ ነው ፎቶ ጋዜጠኛዋ የተናገረችው።
ጉዳዩን በማጣራት ላይ ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ክፍል አዚዛን ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት ያቀረባት ሲሆን ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ለማጣራት የሚያስችለው 14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ ግን አምስት ቀን ብቻ በመፍቀድ ለማክሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት አዚዛና ሌሎቹ ተጠርጣሪዎች እንዲቀርቡ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
በዕለቱ የተጠርጣሪዎቹን የፍርድ ሂደት ለመከታተል በርካታ ግለሰቦችና ቤተሰቦቻቸው የተገኙ ቢሆንም ችሎቱ ግን በዝግ ተካሂዷል።
ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ይሰየማል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ችሎት አርፍዶ ነበር የተሰየመው።ፖሊስ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ሲጠይቅ በፍርድ ቤቱ ከመፈቀዱ በቀር አዚዛ በችሎቱ የተጠየቀችው ነገር እንዳልነበር ነው የተናገረችው።
በስፍራው ለስራ ከመገኘቴ በቀር በፖሊስ ሊያሳስረኝ የሚያስችል ምንም የወንጀል ድርጊት አልፈፀምኩም የምትለው ፎቶ ጋዜጠኛ አዚዛ መሃመድ ምንም አይነት ጥፋት ለመፈጸሟ ማስረጃ ባይቀርብባትም ፖሊስ ለቀጣይ 5 ቀናት በእስር ላይ እንድትቆይ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል።
አዚዛ እስካሁን በፖሊስ የቀረበባት እና የተጠረጠረችበትን ጥፋት የሚያረጋግጥ ማስረጃ ባለመኖሩ ፍርድ ቤቱ በሚቀጥለው የጊዜ ቀጠሮ በነጻ ሊያሰናብታት አለያም በዋስ ሊፈታት እንደሚችል ያላትን ተስፋ ለባልደረቦቿ ተናግራለች።
አዚዛ በሚቀጥለው ቀጠሮ ፍርድ ቤት ስትቀርብ የእስር ቆይታዋ 18 ቀናት ይሆናል ማለት ነው።
ምንጭ፡ አዲስ ጉዳይ

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar