mandag 12. mai 2014

በጊምቢ ከተማ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች የዘር ፍጅት ሊነሳ እንደሚችል አስጠነቀቁ

በኦሮምያ ክልል በምእራብ ወለጋ በጊምቢ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የአማራ ተወላጆች፣ ከአካባቢው እንዲወጡ በሚፈልጉ ወጣቶች ቤታቸው እየተደበደበ መሆኑንና ህይወታቸውም አደጋ ላይ መውደቁን ተናግረዋል።
አንድ ከወሎ አካባቢ የመጡ የመንግስት ሰራተኛ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ባለቤታቸውን አግብተው ለዘመናት ከኖሩ በሁዋላ፣ ሰሞኑን ወደ መጣህበት ሂድ ተብለው በባለቤታቸው ልመና ከሞት እንደተረፉና የቤታቸው ጣሪያም ወንፊት እንደሆነባቸው እያለቀሱ ተናግረዋል።
ባለቤታቸውም በከተማዋ ውስጥ ያንዣበበውን አደጋ በተመለከተ በኦሮምኛ ቋንቋ ስሜታቸውን ገልጸዋል።
ህወሃት ከኦህዴድ ጋር በመሆን የአማራንና የኦሮሞን ብሄሮች ለማጋጨት እቅድ መንደፉን እና ህዝቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ኢሳት ሲያሳስብ ቆይቷል።
ህወሃትና ኦህዴድ ያሰማሩዋቸው ካድሬዎች ” ኦሮሞው” ባህርዳር ላይ ተሰደበ በሚል ከአዲስ አበባ የመሬት መስፋፋት ጋር በተያያዘ የተነሳውን ጥያቄ የብሄር አጀንዳ ለመስጠት እየሞከሩ ነው።
በጄ/ል ከማል ገልቹ የሚመራው ኦነግ፣ በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱት የኦሮሞ ፌደራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የኦሮሞ ወጣቶች ትኩረታቸውን በህወሃት አገዛዝ ላይ ብቻ እንዲያደርጉ ማሳሰባቸው ይታወቃል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar