onsdag 27. februar 2013
በአምስት ዓመታት ጊዜያት ውስጥ 196 ፕሬሶች ከሕትመት ውጪ ሆኑ
በኢትዮጽያ ባለፉት አምስት ዓመታት በፖለቲካ፣በማኀበራዊ፣በኢኮኖሚ ፣በስፖርት፣በሃይማኖት፣በፍቅር፣ በኪነጥበብ እና በመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዮች አተኩረው ይታተሙ ከነበሩ 235 የፕሬስ ውጤቶች መካከል 196 ያህሉ በተለያየ ምክንያት ከህትመት ውጪ መሆናቸውን የብሮድካስት ባለስልጣን ሰሞኑን በድረገጹ በለቀቀው መረጃ አስታወቀ፡፡
ባለስልጣኑ ከየካቲት 2001 እስከ ጥር 2005 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ለ91 ጋዜጦችና ለ144 ያህል መጽሔቶች በድምሩ ለ235 ያህል የፕሬስ ውጤቶች የምዝገባ የምስክር ወረቀት መስጠቱን አስታውሶ ከነዚህ መካከል እስከ ጥር ወር 2005 ዓ.ም ድረስ መዝለቅ የቻሉት 18 ጋዜጦች እና 21 ያህል መጽሔቶች በድምሩ 39 ያህል የፕሬስ ውጤቶች ብቻ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
ባለስልጣኑ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአስደንጋጭ መልኩ ፕሬሶቹ ከሕትመት ውጪ የሆኑበትን ዝርዝር ምክንያት ባያስረዳም ጠቅለል ያሉ ምክንቶችን ለማቅረብ ሞክሯል፡፡
በዚሁ መሰረት 15 የሕትመት ውጤቶች ፈቃድ ከወሰዱ አንድ ዓመት በታች በመሆናቸው በዝግጅት ላይ መሆናቸውን፣ 81(42 ጋዜጦች፣39 መጽሔቶች) በራሳቸው ፈቃድ ስርጭት ማቋረጣቸውን፣ 89 (27 ጋዜጦች እና 62 መጽሔቶች) ፈቃድ ወስደው ወደሕትመት ስራ ሳይገቡ ከአንድ ዓመት በላይ በማስቆጠራቸው በሕጉ መሰረት መሰረዛቸውን አመልክቷል፡፡
በያዝነው የካቲት ወር 2005 ዓ.ም “መሰናዘሪያ” እና “አዲስታይምስ” የተባሉ ጋዜጣና መጽሔት ከሕትመት ውጪ በመሆናቸው በሕትመት ላይ ያሉት ፕሬሶች ጠቅላላ ቁጥር ወደ 37 ዝቅ ያደርገዋል፡፡
ባለስልጣኑ በአሁኑ ወቅት በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት ውጪ የፕሬስ ምዝገባ ጥያቄ ሲቀርብለትና ዓመታዊ የፈቃድ እድሳት የብቃት ማረጋገጫ በሚጠየቅበት ወቅት አንዳንድ አሳታሚዎችን የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ የምዝገባ የምስክር ወረቀት የሚከለክልበት አሰራር ሕጋዊና ተቋማዊ አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
በቅርቡም “አዲስታይምስ” የተባለውን መጽሔት ዓመታዊ እድሳት የሙያ ማረጋገጫ ፈቃድ በመከልከሉ መጽሔቱ ከሕትመት ውጪ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በኢትዮጽያ በፕሬስ የመሰማራት መብት በሕገመንግስት ተረጋግጧል ቢባልም አስፈጻሚው አካል እያካሄደ ባለው ግልጽና
ስውር ተጽዕኖ ምክንያት በርካታ ጋዜጦችና መጽሔቶች ከሕትመት ውጪ ከመሆናቸውም ባሻገር ወደዘርፉ ለመግባት ፍላጎት
ያላቸውን ወገኖች ስራውን ሳይጀምሩት ተስፋ ቆርጠው የሚወጡበት ሁኔታ የመኖሩ ጉዳይ በዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጭምር
በየጊዜው አቤቱታ የሚቀርብበት መሆኑ ይታወቃል፡፡
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar