onsdag 27. februar 2013

ተከራካሪውን በማህበራዊ ፍርድ ቤት ውስጥ በሽጉጥ የገደለው ፖሊስ አልተያዘም


ድርጊቱ የተፈጸመው ከአንድ አመት ከስድስት ወር በፊት በአስኮሪ ከተማ ነበር። ወ/ሮ ወርቅነሽ ኢፋ የተባሉ አርሶአደር በ2002 ዓም የልማት ጀግና ተብለው ተሸልመዋል። ወ/ሮ ወርቅነሽ ሳጂን ኣካለወልድ ተክለማርያም የተባለ የእንጀራ ልጅ አላቸው።

 ግለሰቡ የእንጀራ እናቴ በአደራ የሰጠሁዋትን መሬት ክዳለች በሚል በፍርድ ቤት ክስ መሰረተ። ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ለሳጅን አካለወርድ መፍረዱን ተከትሎ ወ/ሮ ወርቅነሽ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የኦሮሚያ ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ጠይቀው፣ ይፈረድላቸዋል። የፍርድቤቱ ውሳኔ በማህበራዊ ፍርድ ቤት በኩል እንዲፈጸም በተሰጠው ውሳኔ መሰረት፣ ማህበራዊ ፍርድ ቤቱ ተሰይሞ ሳጅን አካለወልድ መሬቱን እንዲያስረክብ ይጠይቃል።

 ሳጅኑም ብድግ ብሎ በጃኬቱ ውስጥ ሸፍኖ ያስቀመጠውን ሽጉጥ በማውጣት የሴትዮዋን ልጅ የ41 አመቷን ወ/ሮ ብርቅነሽ ተክለማርያምን ይመታቸዋል።

 ወ/ሮ ወርቅነሽ የልጃቸውን መመታት ሲያዩ በላዩ ላይ ሄደው በመውደቅ ሊከላከሉ ሲሞክሩ እሳቸውንም በሽጉጥ ይመታቸዋል። በሁኔታው የተደናገጡት የፍርድ ሸንጎው አባላት ተቃውሞ ሲያቀርቡ በእነሱም ላይ ለመተኮስ ቃታውን ሲስብ መሳሪያው ነክሶበታል።

  በዚህም ሌሎች ሰዎች ከመመታት ይድናሉ፣ የሟች ልጅ ኤደን ብርሀኑ ለኢሳት እንደገለጠችው
የሰው ነፍስ ያጠፋ ሰው የዋስትና መብት እንደማይሰጠው ህጉ ቢደነግግም፣ በፖሊስ ሳጅን አካለወልድ ግን ወዲያውኑ በገንዘብ ዋስ እንዲለቀቅ ተደርጓል።

 የሟች ቤተሰብም ጉዳዩን ወደ ዞን ፍርድ ቤት በመውሰድ ገዳይ እንዲቀርብ ቢያስወስንም፣ አቃቢ ህጉና ፖሊስ ግለሰቡን ልናገኘው አልቻልንም የሚል መልስ ለፍርድ ቤት በመስጠት ግለሰቡ ላለፈው አንድ አመት ከ6 ወር ያክል ጊዜ ፍርድ ቤት እንዳይቀርብ ማድረጉን ኤደን ተናግራለች።

ፖሊሶቹ የገዳይ ወገኖች በመሆናቸው ሳጅን አካላወልድን እንደለቀቁት ኤደን ተናግራለች።
ግለሰቡ ሳሪስ አካባቢ እንደነበር የገለጠችው ኤደን በአሁኑ ጊዜ ናዝሬት ከተማ ውስጥ ያለምንም ችግር እንደሚኖር ሰዎች እንደነገሯት ገልጻለች።

ሟች እናት ወጣት ኤድንን ጨምሮ አንድ ሌላ የ12 አመት ልጅ እንደነበራቸው ታውቋል።
የመንግስት ባለስልጣናት በአገሪቱ ውስጥ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እየፈጸሙ በነጻ የሚለቀቁበት አሰራር በስፋት እየታየ ነው።

የኦሮሚያ ፖሊስ ጽ/ቤትን አስተያየት ለማወቅ ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብናደርግም ምላሽ ለማግኘት አልተቻለም።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar