tirsdag 26. februar 2013

የ6ኛው ፓትርያርክ እጩዎች ምርጫ አከራካሪ እንደሆነ ቀጥሏል


የ6ኛው ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ በእጩነት ባቀረባቸው 5 ሊቃነ ጳጳሳት ዙሪያ ተወያይቶ ለማፅደቅ ባሳለፍነው ቅዳሜ የተሰበሰበው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስሲኖዶስ ምልአተ ጉባዔ፣ ያለ አንዳች ውሳኔ መበተኑ ታወቀ።

እንደ ሃራ ተዋሕዶ ብሎግ ዘገባ የዕለቱ የቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባዔ፣ በተለይም ለእጩነት በቀረቡት አባቶች መካከል ከረር ያለ የቃላት ልውውጥ የተስተናገደበት፤ ዋና ጸሐፊውን ተክቶ የኮሚቴውን ሪፖርት ያቀረበውየሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው አቶ ባያብል ሙላቴ ለቅ/ሲኖዶሱና ለአጀንዳው ታላቅነት የማይመጥን፣ እንዲሁም ውክልናውና ያጸደቀለትን ማህበሩን የሚያስንቅና የሚያስወቅስ ደርዝ የሌለው ንግግር የተደመጠበት፣ ኮሚቴውም ከብፁዓን አባቶች ለቀረቡለት ጥያቄዎች የተረጋገጠ መልስ ሊሰጥ ያልቻለበት ነበር፡፡

በጉባዔው ላይ አምስቱ ዕጩዎች የተመረጡት የትውልድ አካባቢያቸውን መሰረት በማድረግ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፣ እነርሱም ከትግራይ ብፁዕ አቡነ ማትያስ፣ ከጎንደር ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ከወሎ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ከሸዋ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ እና ከኦሮሚያ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ናቸው። ይህም ምርጫው የተደረገው የተሿሚውን መንፈሳዊ ብቃት ከግምት በማስገባት ሳይሆን የዘመኑ ፖሊቲካዊ አስተሳሰብና ጎጠኛ ስሜት ላይ ተመስርቶ ለመኾኑ ማረጋገጫ ሆኖ ተገኝቷል ተብሏል።


በዚሁ ስብሰባ ላይ ለአስመራጭ ኮሚቴው ከቀረበሉት ጥያቄዎች አንዱ ‹‹መንግሥት ጣልቃ ገብቷል ወይስ አልገባም?›› የሚል ሲሆን ከኮሚቴው አባላት አንዳቸውም ቢሆኑ ለጥያቄው ምላሽ ሊሰጡ እንዳልደፈሩ ታውቋል፡፡

 ከሕዝብ ግንኙነት ሃላፊው በስተቀር ሌሎቹ የኮሚቴው አባላት በስብሰባው ላይ ብዙም ለመናገር ፈቃደኞች እንዳልነበሩ የተገለፀ ሲሆን፣ የኮሚቴው ዋና ፀሃፊ የሆኑት ሊቀ ማእምራን ፈንታሁን ሙጬ “አሞኛል” በማለት በኮሚቴው ውስጥ መታየት ካቆሙ የሰነባበቱ ሲሆን፣ የታዋቂ ምዕመናን ተወካይ የተባሉት ቀኝ አዝማች ኀይሉም ራሳቸውን ማግለላቸው ይነገራል። በዚህም የተነሳ ኮሚቴው በዕጩዎቹ ማንነት

ላይ በአንድ ድምፅ፣ ያለልዩነት የተፈራረመበት ቃለ ጉባኤ ስለመኖሩ ለቅዱስ ሲኖዶሱ የቀረበ ማስረጃ አለመኖሩ ታውቋል።


በዚሁ የፓትርያርክ ምርጫ የሕወሃት መንግስትን ይሁንታ አግኝተዋል የተባሉት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ሲሆኑ፣ ይህንኑ ጠንቅቀው የተገነዘቡት ሌሎቹ 4 ሊቃነ ጳጳሳትእኛ የታጨነው ለአጃቢነት ብቻ ነው!” በማለት በጉባዔው ላይ የተለያየ ሃይለ-ቃል ሲናገሩ ተደምጠዋል።



በዚህም መሰረት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ÷‹‹በአበው ገዳማዊ ሥርዐት በዕጩነት መመረጥ አይገባኝም፤ እንኳን አይደለም ፕትርክናው ጵጵስናውም ከብዶኛል፤ ይህን ነገር ከሰማኹ ጀምሮ ብርክ ይዞኛል፤ እኔን ተዉኝ፤ እኔ እጠፋለኹ፤›› ያሉ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል‹‹ያው አጃቢ ነን፤ እናየዋለን›› ማለታቸው ተሰምቷል። ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በበኩላቸው÷ ‹‹እኛ መናጆ ተብለን ነው የገባነው፤ የሚመረጠው አባ ማትያስ ነው፤ ያኔ በዕጣ ይኹን ብዬተከራክሬ ነበር፤ የኾነ አካል አባ ማትያስን አምጥቶ ያስቀምጣል፤ እኔ መናጆ አልኾንም፤ ይህ መንፈስ ቅዱስ የተለየውና ሥርዐተ ቤተክርስቲያን ያልጠበቀ ምርጫ ነው።

» በማለት በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡


አጠያያቂ ስለሆነው የብፁእ አቡነ ማትያስ አሜሪካዊ ዜግነታቸው ጉዳይ በብፁዕ አቡነ ገብርዔል እና በብፁዕ አቡነ አብርሃም ጥያቄ ቀርቦላቸው አሜሪካዊ ዜግነቴን መልሻለሁ ብለዋል፡፣ ሆኖም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚሉ ከኾነ ማረጋገጫው ፓስፖርቱ ነው፤ ፓስፖርቱን ያምጡ? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው የተጠየቁትን ማቅረብ አልቻሉም። እንደሚታወቀው «ቤተክርስቲያኗ በቅርቡ ባፀደቀችው የምርጫ ሕግ መሰረት ለፓትርያርክነት የሚመረጥ ሰው በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆነ እድሜውም ከ50 ዓመት ያላነሰ ከ75 ዓመት በላይ ያልበለጠ መሆን አለበት የሚል ድንጋጌ የተቀመጠበት ሲሆን ይህም ሆን ተብሎ የተካተተው አቡነ ማትያስን ከምርጫው ለማስወጣት እንደሆነ ሲነገር ነበር።



ፓትርያርክ ለመሰኘት የቤተክርስቲያኗን ገንዘብ ለቅስቀሳና ለማግባባት አውለዋል በመባል የሚታሙት ብፁዕ አቡነ ሳሙዔልም የብፁዕ አቡነ ማትያስ ዜግነት ጉዳይ ሳይጣራ ከዝርዝሩ ውስጥ መግባታቸውን በመኮነን ለዕጩነት መቅረባቸው አግባብ አይደለም ሲሉ ኮንነዋል። ባጠቃላይ የቤተክርስቲያኗ አባቶች ምርጫውን አስመልክቶ ያላቸው የተከፋፈለ አቋም፣ እንዲሁም እያሰሙት ያለው ቅሬታና ተቃውሞ 6ኛ ፓትርያርክ ተብሎ የሚሾመው ሊቀ ጳጳስ የሚኖረውን ተቀባይነት ከወዲሁ ጥያቄ ውስጥ የሚከተው ሆኖ ተገኝቷል።


አስቀድሞ ለምርጫው በወጣው መርሃ ግብር መሰረት ቅዱስ ሲኖዶሱ በአስመራጭ ኮሚቴው የቀረቡለትን አምስት እጩዎች ዛሬ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህንኑ ተከትሎም የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ በመጪው ሓሙስ የካቲት 21 ቀን 2005 . ተደርጎ በዓለ ሲመቱ የካቲት 24 ቀን እንደሚከናወን ታውቋል ሲል ቅዱስ-ሀብት በላቸው ከአውስትራሊያ ዘግቧል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar