onsdag 27. februar 2013

በስደት ላይ የሚገኘው ሲኖዶስ አዲስ የሚሾሙትን ፓትሪያርክ ህዝቡ እንዳይቀበል ጥሪ አቀረበ


ሲኖዶሱ ለኢሳት በላከው መግለጫ አገሪቱን እስር ቤት አድርጎ ህዝቡን በባርነት ለመግዛት የተነሳው ሀይል የቤተ ክርስቲያንን ሀዋርያዊና የነጻነት አንደበት ለመዝጋት ከሚጠቀምባቸው መንገዶች ተቀዳሚውና ዋነኛው ለህገ ቤተክርስቲያን ሳይሆን ለራሱ ፈቃድ ተገዢ የሆነ ሰው በፓትሪያርክ ስም በቤተ ክርስቲያን መንበር ላይ በማስቀመጥ ቤተክርስቲያንን መድፈር ነው ብሎአል።

ሲነዶሱ ” ላለፉት 21 አመታት በመንግስት አስተባባሪነትና ደጋፊነት በህገ ወጥ መንገድ በተቀመጡት አባት ምክንያት ቤተ ክርስቲአንን ክፉኛ የጎዳው መከፋፈል እና መለያየት ሳያንስ አሁን ደግሞ እነዚህ ጥቂት {አ{አሳት በስልጣን አለውን የመንግስት ሀይል መከታ አድርገው ፓትሪያርክ ብለው የሚሰይሙትም ፣ አባትነቱ የሀሰት አባት፣ ሹመቱም የሲሞ ን መሰርኢ ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ያወግዘዋል።

 በተለይም ለቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት ከፍተኛ መስዋትነት በመክፈል የቆሙ እውነተኛዎቹ አባቶች በዚህ ሂደት ውስጥ ተሳታፊዎች ሆነው በታሪክም በእግዚአብሄርም ተወቃሾች እንዳይሆኑ” ጥሪ አቅርቧል።

ሲኖዶሱ የቤተከርስቲያን ልጆች በአንድነት የሚቆሙበት ጊዜ አሁን መሆኑም በአጽንኦት ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኖርዝ ካሮላይና ቤተክርስቲያን በአቡነ መርቆርዮስ የሚመራውን ሲኖዶስ እንደሚደግፍ አስታውቋል።

የኖርዝ ካሮላይና መካነ ብርሀን ቅድስት ስላሴ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለኢሳት በላከው መግለጫ ፣ ላለፉት 13 አመታት በገለልተኝነት ከሁሉም የአስተዳደር መዋቅር ውጭ ሆኖ ቢቆይም፣ አሁን ግን በብጹወ ቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ በሚመራው ህጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚተላለፈውን አመራር እንደሚቀበል አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ እየተከናወነ አለው ህገወጥ የስድስተኛ ፓትሪያርክ ሲመት የቤተ ክርስቲያን የሰላም በር የሚዘጋ በመሆኑና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን የመከራና ልዩነት ዘመን የሚያረዝም በመሆኑ ፣ ምርጫውን አጥብቆ እንደሚቃወም ገልጿል።

ከቀኖና ቤተክርስቲያን አኳያ በስደት አለም የሚገኙት 4ኛው ፓትሪያርክ ብጹወ ቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ርእሰ ሊቃነጳጳስ መሆናቸውን እንደሚቀበል መግለጫው አመልክቷል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar