lørdag 16. februar 2013

ከፍተኛ ስጋት ላይ የወደቀው መንግስት ሞባይል ኔትወርክ አቋርጦ እንደነበር ታወቀ



በዛሬው ዕለት ከተካሄደው ጁምአ ጸሎት ስርዓት ጋር ረብሻና ከፍተኛ ተቃውሞ ሊነሳ ይችላል በሚል ስጋት በተያያዘ በአዲስአበባ ዛሬ ማለዳ ላይ የሞይባል አገልግሎት ከአምስት ሰዓታት በላይ ተቋርጦ እንደነበር ተሰማ፡፡

በዛሬው ዕለት ሙስሊሙ ህብረተሰብ በመደበኛ የጁምአ ፕሮግራሙ እርስ በእርስ በመጠራራት እና አጫጭር የስልክ መልዕክቶችን በመለዋወጥ ከፍተኛ ተቃውሞ ሊያደርግ ይችላል በሚል ግምት ሐሙስ ለዓርብ አጥቢያ በግምት ከለሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 4፡00 ሰዓት ድረስ የተወሰኑ የሞባይል ሰልክ ቁጥሮችን ከግንኙነት ውጪ በማድረግ ወይ
ኔትወርክ በማቋረጥ እርምጃ ተወስዷል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ የአጭር መልዕክት ልውውጥ
እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ ግድ ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያት በርካታ ግለሰቦችና የቢዝነስ ተቋማት የእርስ በርስ ግንኙነት ማድረግ ሳይችሉ ለማርፈድ ተገደዋል፡፡

ሁሉም የሞይባል አገልግሎት ያልተቋረጠበት ዋንኛ ምክንያት ምን እንደሆነ የተጠየቁት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ የተወሰኑ የደንበኛ ጭነት ያለባቸውን መስመሮች ግንኙነት ከተቋረጠ ያልተቋረጠባቸው ስልኮች ከእነዚህ ጋር ግንኙነት ማድረግ አይችሉም ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ሁሉም ቁጥሮች አለመቋረጣቸው ቴሌ ለሚነሳበት ቅሬታ የኔትወርክ መጨናነቅ
ነው በሚል ጉዳዩን ለማስተባበል ስለሚረዳው ሆን ተብሎ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው የዚህ ዓይነቱ አሰራር ሲፈጸም የመጀመሪያው አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡

እንደምንጫችን ገለጻ ከዚህ በፊት ጠ/ሚኒስትሩ እና ሌሎች የአገር መሪዎች
በከተማ ውስጥ ሲዘዋወሩ፣ሲገቡና ሲወጡ መንገዶችን ከመዝጋት ባሻገር ሸብርተኝነትን አስቀድሞ ለመከላከል በሚል የተወሰኑ የሞይባል ግንኙነቶች ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሲቋረጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በመንግስት ሞኖፖል የተያዘው የቴሌኮም ዘርፍ ለግሉ ዘርፍ ክፍት እንዲሆን ከማይፈለግባቸው ምክንያቶች አንዱ መንግስት ባሻው ጊዜ ስልኮችን የማቋረጥ፣የመጥለፍና የመሳሰሉ ኢ-ሕገመንግስታዊና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ለመፈጸም እንዲረዳው በማሰብ መሆኑን ጠቅሶ ዘርፉ በግል ተይዞ ቢሆን ኖሮ መንግስት የዚህ ዓይነቱ ዕድል የማይኖረው
ከመሆኑም በላይ ከጸጥታ ጉዳይ ጋር ተያይዞ እንኳን አገልግሎት ማቋረጥ ቢከሰት ኪሳራ የመክፈል ግዴታ ስለሚኖርበት የዜጎችም መብት ለማስከር ይረዳ እንደነበር ምንጫችን አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ደህንነት መ/ቤት “ጀሃዳዊ ሃራካት” በሚል ርዕስ በሕግ ጥላ ስር የሚገኙ ሙስሊም እስረኛችን በማስገደድ የተጠናቀረ ፊልም ጥር 28 ቀን ምሽት በኢቴቪ ካሰራጨ በኋላ እንደገና ከዳር እስከዳር የተቀጣጠለውን የሙስሊሞች ተቃውሞ ለማዳፈን ዜጎች በነፍስ ወከፍ ኮንትራት ገብተው እያገኙ ያሉትን የሰልክ አገልግሎት ከፈቃዳቸው ውጪ በማቋረጥና በማስተጓጎል ሥራ ውስጥ መጠመዱ የገባበት ገደብየለሽነት ፍርሃት የሚያሳይ ነው፡፡

ኢህአዴግ የቴሌኮሚኪሽን መስሪያ ቤት ማኔጅመንት እጅግ ታማኝ በሆኑ የህወሀት አባላት እንዲያዝ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።

  ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን በብዛት መልእክቶችን የሚለዋወጡት በሞባይል ስልኮች በመሆኑ መንግስት ምናልባትም ዘወትር አርብ ኔትወርክ በማጥፋት ስራው ሊቀጥል ይችላል የሚል ግምት መኖሩን ዘጋቢያችን ገልጿል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar