fredag 15. februar 2013
33ት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጂሀዳዊ ሀረካትን ተብሎ በኢቲቪ የቀረበውን ፊልም አወገዙ
በመጪው የአዲስ አበባ እና የአካባቢ ምርጫ ላለመሳተፍ የወሰኑ 33ቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ” መንግስት ጅሀዳዊ ሃረካት በሚል ርእስ በኢቲቪ ያስተላለፈው ፊልም ዋና አላማ የህዝብን የዘመናት አብሮነት በመሸርሸርና የመብት ጥያቄ የሚያነሳን ከሽብረተኝነትና ጦርነት ጋር በማያያዝ ህዝብን ለማሸማቀቅ ሆኖ በውጤቱም ህዝብ በአገሩ ላይ ያለውን የባለቤትነትና ሃላፊነት ስሜት በመናድ አንገት ማስደፋትና መብት ጠያቂዎችን በመነጣጠልና መከፋፈል ጥያቄዎችን ማደፈንና ማፈን ነው” ብለዋል።
ኢህአዴግ በለመደው መንገድ ፊልሙን ሲያዘጋጅ በኪሚቴአባላት ላይ ለከፈተው የፈጠራ ክስ በፍትህ አደባባይ ሊያቀርብ ያልቻለውን መረጃና ማስረጃ በህገወጥ መንገድ ታሳሪዎችን በማሰቃየት ” ከተናገሩት”ና ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ጉዞው ከተለያዩ ከጉዳዩ ጋር ተዛማጅ ካልሆኑ የሌላ አገር ፊልሞችን ጨምሮ በተቀናበረ የፕሮፓጋንዳ ድርሰት ለማስደግፍ ቢሆንም የተፈለገውን ውጤት አላስገኘለትም ብሎአል።
ፓርቲዎቹ ” የስርአቱ ህልውና በሰለጠነ መንገድ ከመወያየት ይልቅ በማጭበርበር፣ ህዝብ ከህዝብ በማጋጨትና በመነጣጠል፣ በማሸበርና በሀሰት ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ በአደባባይ ለመከራከርና መፍትሄ ለመሻት ተፈጥሮውና ባህሪው አይፈቅድለትም” ብሎአል።
ፓርቲዎ፤የፊልሙ ግብ መንግስት ላለፉት 21 አመታት ህዝብን በጎሳ፣ በብሄር፣ በክልል እና በሀይማኖት ለመከፋፈል፣ ለመነጣጠል፣ ለማጋጨት ሲያደርግ የነበረውን ሙከራ መድገም ቢሆንም አለመሳካቱን፣ የኮሚቴ አባላቱን ከሙስሊሙ ማህበረሰቡ ያለመነጠሉን፣ በህዝበ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ መካከል የመከፋፈልና የጥርጣሬ ስሜት ለመፍጠር የተደረገው ጥረት በተቃራኒው ህብረተሰቡ እንዲተባበርና በጋራ እንዲቆም ትምህርት መስጠቱን አመልክተዋል።
ፓርቲዎቹ በማያያዝም ” ገዢው ፓርቲ ህገመንግስቱን የማያከብርና ከህግ በላይ መሆኑን፣ የሙስሊሙን ሰላማዊ ተቃውሞ ሊቀለብሰው አለመቻሉን፣ ህዝቡ በኮሚቴ አባላት ላይ ያለው እምነት መጠናከሩን፣ በሙስሊሙና ክርስቲያኑ ህዝብ መካከል ባለው የዘመናት መከባበርና አብሮነት ቀጣይነት ላይ ችግር አለመፍጠሩን፣ የፍርድቤቶች ህገመንግስታዊ ስልጣንና ሃለፊነት በአስፈጻሚው አካል መነጠቁን፣ ህዝቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ በመንግስት ላይ ያለው እምነት መሟጠጡን፣ የለውጥ ፍለጎቱ እንዲጨምርና ለመብቱ በጋራ እንዲነሳ ያደረገው መሆኑን” ጠቅሰዋል።
በመጨረሻም የፊልሙ አዘጋጆች፣ ኢቲቪ እንዲሁም የስራ አስፈጻሚዎች በህግ እንዲጠየቁ፣ የሙስሊም መሪዎች እንዲፈቱ፣ ጥያቄያቸው መልስ እንዲያገኝ እና ህዝቡ ለሰላማዊ ትግል በህብረትና ቆራጥነት በጋራ እንዲቆም ” ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል።
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar