torsdag 21. februar 2013
አቡነ ሳሙኤል ለፓትሪያርክነት ለመመረጥ ቅስቀሳ መጀመራቸው ተዘገበ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን አወዛጋቢውን ጳጳስ አቡነ ጳውሎስን የሚተካ ስድስተኛው ፓትሪያሪክ ለማስመረጥ በዝግጅት ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት ከዚህ የፓትሪያሪክ ምርጫ ጋር በተያያዘ የቤተ ክርስትያኒቷ የተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስና ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በነበሩበት ወቅት ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው የነበሩት አቡነ ሳሙኤል በቀጣዩ ምርጫ ስድስተኛው ፓትሪያሪክ ሆነው ለመመረጥ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ የቤተክህነት አመራሮችን፣ የተለያዩ ሀገረ ስብከቶች ስራ አስኪያጆችንና ታዋቂ ግለሰቦችን በማግባባት ላይ መሆናቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን ጋዜጣው ዘግቧል።
ሊቀ ጳጳሱ ለዚህ ይረዳቸው ዘንድ ከፍተኛ ገንዘብ መድበው እየተንቀሳቀሱ ነው የሚለው ጋዜጣው፣ በጥቅምት ወር በተካሄደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን 31ኛው ጉባኤ ወቅት ተሳታፊ ለነበሩ ቁጥራቸው ወደ 900 የሚጠጋ ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተሰባሰቡ ተሳታፊዎች 500 ሺህ ብር በአበል መልክ እንዲከፈል አድርገዋል።
ይህም ለሚካሄደው የፓትሪያሪክ ምርጫ
ይጠቅማቸው ዘንድ ያከናወኑት መሆኑን ጋዜጣው ዘግቧል።
አያይዘውም ገንዘቡ በሶማሌ እና አፋር ክልሎች ለሚሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲውል ከእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የተገኘ እንደሆነና ተሳታፊዎቹም ከየሀገረ ስብከታቸው አበል ተከፍሏቸው የመጡ መሆናቸው ነገር ግን አቡነ ሳሙኤል ተወዳጅነት ለማግኘት ሲሉ የልማት ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስነታቸውን በመጠቀም ገንዘቡ ለተሳታፊዎች እንዲበተን ማድረጋቸውን ዘገባው ያመለክታል።
በዚህ የምረጡኝ ዘመቻቸው ወቅት ድምፅ ለሚሰጡዋቸው እና ከጎናቸው ለሚሆኑ ሰዎች ፓትሪያሪክ ሆነው ከተመረጡ በኋላ በተሻለ የኃላፊነት ቦታ እንደሚሾሟቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው የውጭ ዕድል እንደሚያመቻቹላቸውና ቤተ ክርስትያኒቷ በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በምታስገነባቸው ህንፃዎች ውስጥ የንግድ ቦታ እንደሚሰጧቸው ቃል እየገቡላቸው እንደሆነ ተዘግቧል።
ከአቡነ ጳውሎስ ህልፈት በኋላ በአዲስ አበባና በአሜሪካው ሲኖዶስ መካከል ሲደረግ የነበረው እርቀ-ሰላም እንዲቋረጥ እና የቀድሞው ፓትሪያሪክ አቡነ መርቆሪዮስ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ አቋም ከነበራቸው ጳጳሳት መካከል አቡነ ሳሙኤል ግንባር ቀደሙ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ አቡነ ሳሙኤል አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናትን እንዳግባቡና መንግሰት ፓትሪያሪክ ሆኜ እንድመረጥ ይፈልጋል የሚለው አቡነ ሳሙኤል ተናግረውታል የተባለው ወሬ በአሁኑ ሰዓት በጠቅላይ ቤተክህነት ውስጥ በሰፊው እየተነዛ እንደሚገኝ ተገልጿል።
አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳትንና የቤተ ክህነት አመራሮችን በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረው ጋዜጣው አቡነ ሳሙኤል እያደረጉት ያለው ተግባር ከአንድ ኃላፊነት የሚሰማው የሀይማኖት አባት የማይጠበቅ እና ሀይማኖታችን የማይፈቅደው ተግባር ነው ብለዋል።
አቡነ ሳሙኤል ዕድሜያቸው ከ50 የማይበልጥ በመሆኑ እና በስነ ምግባራቸውም በተደጋጋሚ ከሲኖዶሱ አባላት ጋር ግጭት ሲፈጥሩ የነበሩ አባት በመሆናቸው ለቤተ ክርስትያኒቷ ትልቅ ኃላፊነት እንደማይመጥኑ አንዳንድ ምዕመናን አስተያየታቸውን ለጋዜጣው ሰጥተዋል።
የአስመራጭ ኮሚቴው ባወጣው መርሃ ግብር መሠረት በዕጩነት ከቀረቡት አምስት አባቶች መካከል የሚመረጡት 6ኛው ፓትሪያሪክ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም በዓለ ሲመታቸውን ይፈፀማል።
ህወሀት መራሹ መንግስት በፖለቲካው ውስጥ የሚታየውን ዘረኝነት በቤተክርስቲያን ውስጥ አስገብቷል በሚል የሚቀርብበትን ትችት የአቡነ ሳሙኤልን ሹመት በማገድ ለማለሳለስ ይሞክር ይሆናል የሚሉ አስተያየቶች ይቀርባሉ።
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar