onsdag 20. februar 2013
ጣሊያን ኢትዮጵያውያንን በግፍ የጨፈጨፈችበት 76ኛ አመት በመላው አለም ታስቦ ዋለ
ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረች ማግስት፣ አገራቸውን ከወረራ ለመታደግ ሞገስ አስገዶምና አብረሀ ደቦጭ የተባሉ ሁለት ኢትዮጵያውያን፣ የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒቶ ሙስሎኒ የኢትዮጵያ ልኡክ የነበረውን ሮዶልፎ ግራዚያኒን ለመግደል ሙከራ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ ወራሪው ሀይል ከ30 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያንን በአንድ ቀን በግፍ መጨፍጨፉ ይታወሳል።
ኢትዮጵያውያን በእየአመቱ የካቲት 12 የሚያከብሩት ይህ የሰማእታት ቀን በመላው አለም በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ዘንድሮም ተከብሮል።
በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማዕታት ሐውልት የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አርበኞች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተገኙበት የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል። ሰማዕታቱን ለማሰብም በሐውልቱ ሥር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው አስተዳደሩን በመወከል የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል። የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ተወካይም የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።
በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ በቨርጂን ሜሪ ኦርቶዶክስ ካቴደራል ልዩ የጸሎት ስነስርአት ተካሂዶአል። በስነስርአቱ ላይ አባ አለቃ ማሪያም እና ቀሲስ መላኩ ባወቀ ፋሺስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመችውን ግፍ ዘርዝረው አቅርበዋል። በዚሁ እለት ከ200 በላይ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት መገደላቸውም ተወስቷል።
በአምስተርዳም ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እውቁ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆነው አርሰቲስት ታማኝ በየነ በተገኘበት እለቱን የህሊና ጸሎት በማድረግ አስበውታል።
ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን አንበርክካ ቅኝ ግዛቷ ለማድረግ በተደጋጋሚ ብትሞክርም፣ በኢትዮጵያውያን አስደናቂ ጀግንነት ምኞቷ ህልም ሆኖ እንደቀረ ይታወቃል።
በአፍሪካ ውስጥ በቅኝ ግዛት ውስጥ ካልተያዙ ሁለት አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዱዋ ናት።
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar