søndag 24. februar 2013
ፓትሪያርክ ለማሾም የሚደረገ ው የምረጡኝ ዘመቻ ቀጥሏል
በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ሀይማኖት ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ፣ የፓትሪያርክ የምርጫ ቅስቀሳ በስፋት እየተካሄደ መሆኑን የሀይማኖት አባቶች ገለጹ። ሰሞኑን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ሲዘገብ የቆየውን የፓትሪያርክ የምርጫ ቅስቀሳ፣ ፓትሪያርክ ይሆናሉ ተብሎ ባለፈው ሳምንት በተሰራጨው ዘገባ ላይ ስማቸው የተነሳው አቡነ ሳሙኤል አረጋግጠዋል።
አቡነ ሳሙኤል ለአዲስ አድማስ በሰጡት አጭር ቃለምልልስ እንደገለጡት በምርጫው ዙሪያ የተለያዩ ቡድኖች ተፈጥረው የምርጫ ቅስቀሳ እያካሄዱ መሆኑን አጋልጠዋል። አቡነ ሳሙኤል ” በየብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ቤት ፣ በእኔም ቤት ሳይቀር እየዞሩ እገሌን ካልመረጣችሁ፣ ካላስመረጣችሁ የሚሉ አካላት እንዳሉ ግልጽ ነው” ያሉት አቡነ ሳሙኤል ፣ “ስልጣን ባለው አካል መንፈሳዊ ስልጣንን ለመያዝ የሚደረገው ሽር ጉድ ሁሉ በፍትህ መንፈሳዊ፣ በቀኖና ቤተክርስቲያን የተወገዘ መሆኑን” በመግለጽ ድርጊቱን አውግዘዋል።
እንዲህ ሆኖ የሚሾመው አባትም ቢሆን ሲመቱ ስጋዊ ሹመት ይሆንና በነፍስም በስጋም ያጎድለዋል፣ ያለጊዜውም ሊያስቀስፍ ይችላል በማለት አስጠንቅቀዋል። በመሆኑም ይላሉ አቡነ ሳሙኤል ” በምርጫው የሚሳተፉ ካህናትና መእምናን ለቤተ ክርስቲያንና ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ማሰብ መወሰንና መቆም ይገባቸዋል።”
አቡነ ሳሙኤል ባለፈው ሳምንት ” ፓትሪያርክ ሆነው ለመመረጥ ቅስቀሳ ጀምረዋል” የሚለውን የሰንደቅ ጋዜጣ ዘገባ አስተባብለዋል።
” ምረጡኝ ብየ አላልኩም፣ ምረጡኝ ብየ አላውቅም” ያሉት አቡነ ሳሙኤል፣ ይህንን የሚያስወሩት በምርጫው ዙሪያ የተደራጁ ቡድኖች ናቸው” ብለዋል። አቡነ ሳሙኤል ” ፓትሪያርክነት የአባትነት፣ የቡራኬ ስልጣን ነው፤ ለእኔ አገልጋይነት ይሻለኛል፤ አገልጋይ መሆን ነው እንጅ፣ አዛዥ፣ ገዢ፣ አሳሪ፣ አሳሳሪ መሆን አይደለም” በማለት ተናግረዋል።
አቡነ ሳሙአል ፓትሪያርክነት በ ” አዛዥነት፣ በገዢነት፣ በአሳሪና አሳሳሪነት የተመለከቱበት መንገድ ለውዝግብ ሳይዳርጋቸው እንደማይቀር ይታመናል።
አቡነ ሳሙኤል ቀጣዩ ፓትሪያርክ ይሆናሉ ተብሎ ከተገመተ በሁዋላ በእጩነት አለመቅረባቸው ከምርጫው ጋር በተያያዘ እየተፈጸመ ያለውን ሴራ እንደሚያሳይ ዘጋቢያችን ገልጿል። የአቡነ ሳሙኤል ንግግር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤትክርስቲያን የገባችበት የዝቅጠት ደረጃ ያሳያል ያለው ዘጋቢያችን፣ የእርስ በርስ መጣላለፍ፣ የስም ማጥፋት፣ ለገዢው ፓርቲ ሎሌ ሆኖ መቅረብ፣ መንፈሳዊነትን ረስቶ ለስጋ ማደር፣ ጥቅምን ማሳደድ፣ ዘረኝነት እና ንግድ” የቤተክርስቲያኑዋ መገለጫ እየሆኑ ነው ብሎአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትሪያሪክ፤ መሠረተ ቢስ መረጃዎችን በማስተላለፍ ህዝቡን ለማደናገር ይሠራሉ በማለት ክስ የመሠረተባቸው አራት ጋዜጠኞች ማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ ቀርበው ቃላቸውን ሰጡ፡፡
በስልክ ከፖሊስ በደረሳቸው ጥሪ መሠረት ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቀርበው የተከሳሽነት ቃላቸውን የሰጡት፤ የ “ሎሚ” መጽሔት፣ የ “ሊያ” መጽሔት፣ የ“አርሂቡ” መጽሔት እና የ “የኛ ፕሬስ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጆች ናቸው።
እንደ አዲስ አድማስ ዘገባ፤ጋዜጠኞቹ ፎቶግራፍ እና አሻራቸው ተወስዶ በዋስ ተለቀዋል፡፡
የ“ሎሚ”፣ የ “ሊያ” እና የ “አርሂቡ” መጽሔት ዋና አዘጋጆች ማክሰኞ የካቲት 12 ቀን 2005 ዓ.ም ለፖሊስ ቃል የሰጡ ሲሆን፤ የ “የኛ ፕሬስ” ዋና አዘጋጅ ደግሞ ሃሙስ የካቲት 14/ ቀን ቃሉን ሰጥቷል፡፡
የየኛ ፕሬስ ጋዜጣ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ስዩም ለአድማስ እንደገለፁት፤ ዋ“ሲኖዶስ ተከፋፍሏል” እና “ስደተኛው ሲኖዶስ መግለጫ አወጣ” በሚሉ ርዕሶች በጋዜጣው ላይ በወጡ ዘገባዎች በዋና አዘጋጁ በካሳሁን ወልደዮሐንስ ላይ ክስ ቀርቦበታል፡፡
የ“አርሂቡ” መጽሔት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ካሣሁን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በመጽሔቱ የታህሳስ ወር እትም ቁጥር 40 ላይ “አቡነ ማቲዎስና አቡነ ሣሙኤል ተፋጠዋል” በሚል ባወጣው ዘገባ ክስ ቀርቦባቸዋል።
በክሱ ዙሪያ የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አበራ የተከሳሽነት ቃሉን ሰጥቷል።
የ“ሎሚ” መጽሔት ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛው ታዬ እንዳሉት ደግሞ የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ የሆነችው ወ/ት ብዙአየሁ ጥላሁን በሶስት ርዕሰ ጉዳዮች ለቀረበባት ክስ ማክሰኞ ዕለት ቃሏን ከሠጠች በኋላ -እርሳቸው የመኪናቸውን ሊብሬ አስይዘው በዋስ አስለቅቀዋታል።
ዋና አዘጋጇ “መንግሥት በሃይማኖት፤ ሃይማኖትም በመንግስት ጣልቃ አይገባም” የሚለውን ህገመንግስታዊ ድንጋጌ በመጣስ፣ ህዝብ- በመንግስትና በቤተክርስቲያን አመኔታ እንዳይኖረው የሚያደርግና ህዝብን ለአመጽና ለሁከት የሚያነሳሳ ጽሑፍ አትማ አሠራጭታለች “ የሚሉ ክሶች የቀረቡባት ሲሆን ለሁሉም ክሶች ቃሏን መስጠቷን አቶ ግዛው ገልፀዋል፡፡
የ“ሊያ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ መላኩ አማረ በበኩላቸው፤ ስለ ጉዳዩ ዋና አዘጋጇ ብዙም የምታውቀው ስለሌለ እሣቸው የተከሳሽነቱን ቃል እንደሰጡና በክስ ዝርዝር መግለጫው ላይም ከሳሽ ሆነው የቀረቡት አቡነ ናትናኤል መሆናቸውን ተናግረዋል።
መጽሔቱ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቀጣይ እጣ ፈንታ ምንድነው?” በሚል በቁጥር 19 እትሙ ባቀረበው ዘገባ ክስ እንደቀረበባቸውም አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡
ጋዜጠኞችን በመክሰስ፣በማሰር፣በማዋከብና በማሳደድ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱትና የፕሬስ ጠላቶች ከሚባሉት አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ኮሚቴ(ሲፒጄ) በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar