torsdag 21. februar 2013
በኦሮሚያ ለአባ ገዳ የተሰበሰበው ገንዘብ በባለስልጣናት ተመዘበረ
በጉጂ ኦሮሞ ባህል አንድ አባገዳ ስልጣን በተረከበ በስድስተኛው አመት ጉማታ ወይም ስጦታ ከህዝቡ ይሰበስባል።
ስልጣኑን የሚያስረክበው በስምንተኛው አመት ሲሆን፣ ለሁለት አመታት የሚሰራበትን ገንዘብ፣ እህል ወይም የቤት እንስሳ ከህዝቡ በስጦታ መልክ ይቀበላል።
በዚህ አመት አባገዳው ጉማታውን ለመሰብሰብ ዝግጅት በሚጀምርበት ጊዜ የቦረና ዞን የመንግስት ባለስልጣናት ከአሁን በሁዋላ ጉማታው መሰብሰብ ያለበት በመንግስት ነው በሚል ምክንያት፣ የጉማታ ሰብሳቢዎች በተለያዩ አካባቢዎች ተዋቅረዋል።
የመንግስት ባለስልጣናቱም ከህብረተሰቡ እየዞሩ በአባገዳው ስም የሰበሰቡትን እጅግ በርካታ ገንዘብ ፣ ለአባገዳው ሳይሰጡ የተወሰነውን ለመንግስት የተወሰነውን ለራሳቸው በማድረጋቸው፣ የአካባቢው ህዝብ መንግስት ባህላችንን ሆን ብሎ ለማፍረስ ወሰደው እርምጃ ነው በሚል ተቃውሞን እያሰማ ነው።
አባገዳው ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ አንድ ሳንቲም ባለማግኘቱ፣ አባገዳውና የእርሱ ተወካዮች አቤት ቢሉም ሰሚ አላገኙም።
ባለፈው እሁድ ከተወካዮች ምክር ቤት የተውጣጡ የፓርላማ አባላት ወደ አካባቢው በሄዱበት ወቅት፣ ባህላችንን ልታንቋሽሹ ሆን ብላችሁ የሰራችሁት ነው በሚል ተቃውሞ ገጥሞዓቸዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት የሰበሰቡት ገንዘብ ትክክለኛ መጠኑ ባይታወቅም፣ የዞኑ ነዋሪዎች ከ100 ብር እስከ 15 ሺ ብር እና በርካታ የቀንድ ከብቶችን ለግሰው እንደነበር የደረሰን መረጃ ያሳያል።
በጉዳዩ ዙሪያ አባገዳውን ለማግኘት ሙከራ ብናደርግም ስልካቸው ጥሪ አይቀበልም።
የአካባቢው ባለስልጣናትን ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም አልሳካም። ይሁን እንጅ ባለስልጣናቱ በዞኑ ውስጥ ለኢሳት መረጃዎችን የሚሰጡ ሰዎችን ለመያዝ በጀመሩት ጥረት አንዳንድ ተጠርጣሪ ግለሰቦችን ለመያዝ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን በመስተዳዳሩ ውስጥ ከሚሰሩ ውስጥ አዋቂዎች ለማወቅ ተችሎአል።
Abonner på:
Legg inn kommentarer (Atom)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar