በፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ካምፕ በሰብአዊ ፍጥረት ላይ ወንጀል ተፈጽሟል፡፡
“በአላህ እና በተበዳይ መካከል ግርዶሽ የለም!”
ጁምአ ሐምሌ 11፣ ለቅዳሜ ሐምሌ 12 አጥቢያ፣ ኮልፌ በሚገኘው የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ግቢ ውስጥ ሌሊቱን ሙሉ በሺህዎች በሚቆጠሩ ሰብአዊ ፍጡራን ላይ ከባድ ወንጀል ተፈጽሟል፡፡ …
በነፍስ ወከፍ ወፋፍራም ዱላ የያዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች መንትያ ሰልፍ ሠርተው ፊት ለፊት እየተያዩ ቆመዋል፡፡ በረድፍ በቆሙት ፖሊሶች መካከል ያለው ርቀት 3 ሜትር አይሆንም፡፡ በሁለቱ ረድፎች መካከል ያለው ርቀትም ከዚያ አይበልጥም፡፡ ከአንዋር መስጂድ ቅጥረ ግቢ በበርካታ የጭነት መኪና ታጭቀው የተወሰዱት የአዲስ አበባ ነዋሪ ሙስሊሞች ወፋፍራም ዱላ ይዘው ግራ እና ቀኝ በረድፍ በቆሙት ፖሊሶች መሃል ለመሃል በእንብርክክ እንዲሄዱ ታዘዙ፡፡ በእንብርክክ የሚሄዱበት መሬት ሆን ተብሎ ለቅጣት የተዘጋጀ ይመስላል፡፡ ጠጠራማ፣ አሸዋማ፣ ድንጋያማ፣ ኮረታማ እና ጭቃማ ነው፡፡ ፖሊሶቹ የሠሩት መንትያ ረድፍ ከ300 ሜትር ይበልጣል፡፡ በዚያ መሬት ላይ ይህን ያህል ርቀት በእንብርክክ መሄድ በራሱ ከባድ ቅጣት ነው፡፡ ዋናው ቅጣት ግን ይህ አልነበረም፡፡ ወፋፍራም ዱላ ይዘው በመንታ ረድፍ የቆሙት ፖሊሶች በሙሉ የእንብርክክ በሚሄደው በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ዱላቸውን ያሣርፉበታል፡፡ ወገቡን፣ ጭንቅላቱን፣ አንገቱን፣ ሽንጡን፣ እግሩን … በቃ ያገኙት ቦታ ላይ ይመቱታል፡፡ ተደብዳቢው አናቱ ላይ ተመትቶ ራሱን ከሳተ ጎትተው ከረድፋቸው ውጪ አውጥተው ጥለውት ፈጥነው ቦታቸው ላይ ይመለሳሉ፡፡ አንድም ልጅ ዱላችሁን ሳይቀምስ እንዳያልፍ የተባሉ ይመስላሉ፡፡ ጁምአ ዕለት ሐምሌ 11 ቀን በፆም የዋሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወንድሞች በዚህ መልኩ ከ300 ሜትር በላይ የእንብርክክ እየሄዱ ከግራና ከቀኝ በዱላ ተቀጥቅጠዋል፡፡ ይህ በሰብአዊ ፍጡራን ላይ የተፈፀመ ወንጀል (Crime against humanity) አይደለምን?! …
አገራችን ኢትዮጵያ ይህን መሰል ኢ ሰብአዊ ወንጀል በዜጎች ላይ እንዲፈፀም ትዕዛዝ ለመስጠት እና ይህን ትዕዛዝ ያለአንዳች ሰብአዊ ርኅራኄ ለመፈፀም የሚፈቅዱ በሰው አምሳል የተፈጠሩ ውሾች ያሉባት አገር መሆኗን ማወቅ በጣም ያሳምማል፡፡
ላለፉት ሁለት ተኩል ዓመታት እንደ ዜጋም፣ እንደ ሃይማኖት ማኅበረሰብም ስለ ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻችን መከበር በሰላማዊ መንገድ ስንጮህ፣ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት ለዚህ የህዝቦች የጋራ ጩኸት ተገቢ ምላሽ ከመሥጠት ይልቅ እኒህን መሰል ፍፁም ከሰብአዊነት የወጡ ወንጀሎችን መፈፀምን መርጧል፡፡ የሃይማኖት ነፃነትና የዜግነት መብቶቻችን እንዲከበሩ በጠየቅን የጅምላ ድብደባ ወንጀል ሲፈፀምብን ይህ የመጀመርያ አይደለም፡፡ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት ይህን መሰል ኢ ሰብአዊ የድብደባ ወንጀሎችን በመፈፀም ምን እንደሚያተርፍ ባይገባንም፣ በእኛ በኩል ዱላ እና ጥይት በሃይማኖታችን ምክንያት የተፈፀሙብንን እና ዛሬም እየተፈፀሙብን ያሉ ግልጽ የሃይማኖት ነፃነትና የዜግነት መብት ረገጣዎችን አሜን ብለን እንድንቀበል ሊያደርጉን እንደማይችሉ በአጽንኦት ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን፡፡
ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት የተፈፀሙብን የጭካኔ ድብደባዎች የሃይማኖት ነፃነትና የዜግነት መብት ጥሰቶችን በመቃወም ከምናደርገው ትግል እንድናፈገፍግ አላደረጉንም፡፡ መንግሥት እስካሁን ከወሰዳቸው በርካታ ሕገ ወጥ እርምጃዎች በኋላ፣ ዛሬም እንደ ሕዝብ ድምፃችንን ለማሰማት ስንሰበሰብ የዱላ አማራጭን መከተሉ እንደ መንግሥት ሊያፍርበት የሚገባ ድንቁርና ወለድ እርምጃ መሆኑን አስረግጠን ልንነግረው እንሻለን፡፡ ለዜጎች ሕጋዊ እና ትክክለኛ የመብት ጥያቄ፣ ዱላ እና ጥይት በምንም ዓይነት መፍትኄ አያመጡም፡፡ ዱላ እጃችሁ ላይ ስላለ ዜጎችን በመደብደብ፣ ጠመንጃ እጃችሁ ላይ ስላለ ዜጎችን በመግደል ከመገበዝ፣ እንደ መንግሥት የህዝብን ድምጽ ብትሰሙ መልካም ነው፡፡ ያ ካልሆነ ግን፣ ሌላው ቢቀር፣ ቢያንስ እኛ ሰላማዊ ትግላችንን በጽናት ከመቀጠል የማናፈገፍግበትን ምክንያት ብታውቁት መልካም ይመስለናል፡፡ አንድ መንግሥት በሚያስተዳድረው ሕዝብ ላይ በደልን ማብዛቱ ለውድቀት ይዳርገው እንደሁ እንጂ፣ ከቶም አሸናፊ አያደርገውም፡፡ እንደምን ይህን ሐቅ ማየት እንደተሳናችሁ ባይገባንም፣ በአንጎለ ቢስ ፖሊሶች እንዲህ እያስቀጠቀጣችሁንም ትግላችንን በጽናት የምንቀጥልበትን ምክንያት እንንገራችሁ፡፡
ትግላችንን በጽናት የምንቀጥለው ውሾቻችሁ ያለ ርኅራኄ ያሳረፉብን በመቶዎች የሚቆጠሩ በትሮች ስላልጎዱን፣ በአካላችን ላይ ጉዳት ስላልደረሰብን አይደለም፡፡ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሁለት እና ሦስት ወንድማማቾችን ጨምሮ በብዙ ሺህዎች የምንቆጠር ሙስሊም ዜጎች በጨካኞች በትር እንደ እባብ ተቀጥቅጠናል፡፡ ህይወታቸው በአስጊ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ወንድሞችም ጥቂት አይደሉም፡፡ እናም ዱላው አላሳመመንም፤ አካላችን አልተጎዳም አንልም፡፡ ነገር ግን፣ ምንም ዓይነት ጭካኔ የተመላበት ሕገ ወጥ ድብደባ፣ ብሎም እሥርና ግድያ፣ በገዛ አገራችን ሙስሊም በመሆናችን ብቻ እየተፈፀሙብን ካሉት የዜግነት መብት እና የሃይማኖታዊ ነፃነት ረገጣዎች በላይ አያሳምሙንም፡፡
የዚህች አገር ዜጎች እንደመሆናችን፣ መብቶቻችን እና ሃይማኖታዊ ማንነታችን ተከብሮ፣ በዜግነታችን ኮርተን፣ በሰላም ወጥተን በሰላም መግባት የምንሻ ሕዝቦች ነን፡፡ ካለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ ወዲህ ግን፣ መንግሥት ግልጽ ፀረ-ሙስሊም ፖሊሲ በመከተል በርካታ የዜግነት መብቶቻችንን እየገፈፈን እንደሚገኝ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ እነዚህ የመብት ገፈፋዎች በተለያዩ ዘርፎች (በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ) የሚገለፁ ሲሆን፣ ከትናንት በስቲያ ድምፃችንን ልናሰማባቸው ከነበሩ በደሎች አንዱ በሆነው የትምህርት ዘርፍ የሚፈፀምብንን በደል ለአብነት ያህል እናንሳ፡፡
ከስድሳ ዓመት በማይበልጠው የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ታሪክ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በሃይማኖታዊ እምነቱ/ቷ እና ተግባራቱ/ቷ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ለመፈናቀል ሲዳረጉ የታየው ባለፉት ሁለት ዓመታት ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸው ከዛሬ ነገ ተመርቀው ወደሥራ ዓለም በመግባት እኛንም ሆነ አገራቸውን ያገለግላሉ ብለው በተስፋ ሲጠብቋቸው የነበሩ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ሙስሊም የዩኒቨርሲቲ እና የኮሌጅ ተማሪዎች በሃይማኖታቸው ምክንያት ከትምህርት ለመፈናቀል ተዳርገዋል፡፡ በተጨማሪም ከተለያዩ የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች እምነታቸውን በቀናዒነት ለመተግበር የሚተጉ ሙስሊም ተማሪዎች ተለቅመው ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ተወርውረዋል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ከትምህርት መስተጓጎላቸው ሳያንስ፣ በ“አሸባሪነት” የሐሰት ክስ ተመሥርቶባቸው በትምህርት ሊያሳልፉት የሚገባ ወርቃማ ጊዜያቸው እና ዕድሜያቸው ከወህኒ ቤት ፍርድ ቤት በመመላለስ እንዲባክን ተደርጓል፤ እየተደረገም ነው፡፡
በማይምነት፣ በድህነት እና በኋላቀርነት በምትታወቀው አገራችን፣ በቀደምት ዘመናት ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ከዘመናዊ ትምህርት በስልታዊ መንገድ ሲገፋ ኖሯል፡፡ በአጠቃላይ በአገራችን ሠፍኖ በኖረው ኋላቀር አስተሳሰብ ሳቢያ በተለይ ሴቶቻችን የዚህ መገፋት ድርብ ሰለባ ሆነው እንደኖሩም ይታወቃል፡፡ ይህ ሁኔታ በሂደት እየተሻሻለ መጥቶ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ ጥቂት ሙስሊም ሴቶችን ማየት የተቻለበት ዘመን ላይ ከተደረሰ በኋላ፣ በስንት ድካም ለዚህ ደረጃ የደረሡ ሙስሊም ሴቶችን “ይህን ልበሱ፣ ይህን አትልበሱ” በሚል ተልካሻ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ማፈናቀል “ለሴቶች መማር ትልቅ ትኩረት እሰጣለሁ” በሚል መንግሥት ሲፈፀም ማየት በእጅጉ የሚያሳዝንና የሚያሳምምም ነው፡፡
“በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሶላት መስገድ እና ሃይማኖታችሁ በሚያዝዘው መሠረት መልበስ አትችሉም” በሚል የመማር መብትን መነፈግ፣ ከፖሊስ ዱላም፣ ከእስርም፣ ከግድያም በላይ ያሳምመናል፡፡ ይህ የዜግነት መብታችን እና ክብራችንን የሚነካ፣ በፍፁም ከመንግሥት የማይጠበቅ አሳፋሪ ተግባር ነው፡፡ ይህን መቼም ቢሆን ልንቀበለው አንችልም፡፡ ስለዚህም ነው፣ የቱንም ያህል ኢ ሰብአዊ በሆነ መልኩ በዱላ ብንቀጠቀጥም፣ ለራሳችን ክብር ያለን ዜጎች ነንና፣ በከፍተኛ 2ኛ ደረጃም ሆነ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሃይማኖት ነፃነታችን እና መብታችን፣ ብሎም የዜግነት ክብራችንን ለማስጠበቅ የምናካሂደውን ሰላማዊ ትግል እንቀጥላለን የምንለው፡፡
እነዚህን ከመንግሥት የተሳሳተ ፖሊሲ የመነጩ የተሳሳቱ እርምጃዎች ሕጋዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መቃወም፣ ለሕግ ተገዢ የሆኑ ዜጎች ሊያደርጉት የሚችሉትና የሚገባቸው አነስተኛ ነገር ነው፡፡ በአንጻሩ መንግሥት ይህን ሰላማዊ ተቃውሞ ኃይልን በመጠቀምና በእነዚህ ዜጎች ላይ ሕገ ወጥ እርምጃ በመውሰድ ለማስቆም መሞከሩ እጅግ ኃላፊነት የጎደለው፣ የወረደ አካሄድ ነው፡፡ ዜጎች ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ መንግሥት “እኔ ጉልበት ስላለኝ የፈለግሁትን ባደርግ ልትቃወሙኝ መብት የላችሁም” በሚል ዜጎቹን በጅምላ በፖሊስ ዱላ የሚያስደበድብ ከሆነ፣ ከተደብዳቢዎቹ ዜጎች ይልቅ ክብር እና ሞገሱን የሚያጣው መንግሥት ነው፡፡
የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት ኃይል እና ጉልበቱን በመመካት፣ በዜጎች ላይ የሚፈጽመው ቅጥ ያጣ ግፍ እና በደል ዋጋ የማያስከፍለው ከመሰለው በጣም ተሳስቷል፡፡ የታዘዙትን ‹አረረ መረረ› ሳይሉ የሚፈጽሙ አንጎለ ቢስ ፖሊሶች እና ወታደሮች አሰማርቶ ሰላማዊ ዜጎችን እንደ እባብ ማስቀጥቀጥ በምንም መለኪያ አገርን የመምራትና ሕዝብን የማሥተዳደር ጥበብ አይደለም፡፡ አንድ መንግሥት ለሕግ ተገዢ ከመሆን የበለጠ ከዜጎች የሚፈልገው ነገር ይኖራል ብለን አናምንም፡፡ በዚህም መንፈስ የአገርን ሰላምና የህዝብን ፀጥታ ሳናውክ፣ የዜጎችን መብትም ሳንነካ፣ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በእምነታችንና በሃይማኖታችን ምክንያት እየተፈፀሙብን ያሉትን በደሎች በሰላማዊ መንገድ እየተቃወምን እነሆ ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ዘልቀናል፡፡ የዚህች አገር ሕዝቦች፣ የዚህችም አገር ዜጎች ነን፡፡ እንደ ሕዝብ እና እንደ ዜጋ “ድምፃችን ይሰማ” እያልን ስንጮህ፣ በመንግሥት ልንሰማ ይገባናል፡፡ ይህን ማድረግ የመንግሥትነት ወግ ነው፡፡ በተቃራኒው፣ የጋራ ጥያቄዎቻቸውን በጋራ ለማሰማት የተሰባሰቡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ከቤተ አምልኳቸው ሰብስቦ በፖሊስ ካምፕ ውስጥ እንደ እባብ መቀጥቀጥ፣ በሰብአዊ ፍጥረታት ላይ ግልጽ ወንጀል መፈፀም ከመሆኑም ባሻገር፣ እጅግ በጣም ወራዳ የድንቁርና ተግባር ነው፡፡ ይህ ወራዳ የድንቁርና ተግባር “እውን በዚህ አገር መንግሥት ከነግርማ ሞገሱ አለን?” አሰኝቶናል፡፡
እርግጥ ነው፣ መንግሥት የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ብቸኛ የመረጃ ምንጫቸው ከሆኑ ዜጎች መካከል የተወሰኑ ወገኖቻችንን በፕሮፖጋንዳ ያታልል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በገጠርም ሆነ በከተማ ያለው አብዛኛው ሕዝብ ለተራዘሙ ጊዜያት በመታለል ይኖራል ብሎ ማሰብ፣ ያለጥርጥር ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን ጠብቆ፣ በመንግሥት ኃይሎች የሚፈፀሙበትን ሕገ ወጥ በደሎች ለሐቅና ለሰብአዊ ክብር የሚከፈል ተገቢ መስዋዕትነት መሆኑን ተገንዝቦ ትግሉን በጽናት ይቀጥላል፡፡ ሰላማዊ ትግሉ እስከቀጠለ ድረስ ደግሞ ጊዜ በገፋ ቁጥር እውነቱ ደምቆ እየወጣ ሐሰት መኮሰሷ የማይቀር ነው፡፡ ያኔ የግፍ በትር ያሳረፋችሁባቸው ዜጎች በከፈሉት መስዋዕትነት ኮርተው ቀና ሲሉ፣ እናንተ ግን ታፍራላችሁ፡፡
አንድ በጣም የምወዳቸው አንደበተ ርቱዕ ሸኽ አንድ ዕለት የተናገሯትን ድንቅ ንግግር ለጽሑፌ መደምደሚያ ላደርጋት እወዳለሁ፡፡ “በአላህ እና በተበዳይ መካከል ግርዶሽ የለም!!”