fredag 11. juli 2014

ወራቱ ረመዷን ነው! ፍቷቸው!


uncuff
ወራቱ ረመዷን ነው፡፡ በዚህ ወር ሰላም፣ ማርታ፣ ይቅርታ እና ምሕረት ነው የሚለመነው፡፡ አዲስ ሰው ለመሆን ነው ጥረት የምናደርገው፡፡ ባለፉት ሶስት ዓመታት ባሳለፍኳቸው ረመዳኖች የሚሰሩት ነገሮች ግን ከዚህ ቅዱስ ወር የምናገኘውን በረከትና ጸጋ በአግባቡ እንዳንቋደስ እና ቀልባችንን ሙሉ በሙሉ ወደ ፈጣሪያችን እንዳንመልስ ጋሬጣ እየሆኑብን ተቸግረናል፡፡
ወራቱ ረመዳን ነው፡፡ ትናንት ሰዎች ታስረዋል፡፡ ማን እንደታሰረም ስለሚታወቅ መግለጹ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ነገር ግን በየጊዜው ሰዎችን ማሰር የምንመኛት ኢትዮጵያ እንድትመጣ ለማድረግ አንዳች ጠቀሜታ የለውም፡፡ ገዥው ፓርቲ የሚያልመውን የኢትዮጵያ ራዕይን በ2020 ለማሳካትም ሆነ ሌሎች በተለየ መንገድ የሚመኟትን ለሁላችንም የምትሆነውን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ምንም አይፈይድም፡፡ በሰከነ መንፈሰ መደማመጥና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት መጣር ነው ለሁሉም የሚበጀው፡፡
ወራቱ ረመዷን ነው፡፡ ይህ የተቀደሰ ወር ሸይጣን የሚታሰርበት እንጂ የሰው ልጅ ወደ ወህኒ የሚወረወርበት ወር አይደለም፡፡ ስለዚህ ትናንት የታሰረውን አብረሃ ደስታን ጨምሮ አላግባብ የታሰሩት ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በአስቸኳይ ይፈቱ ዘንድ በሀያሉ ፈጣሪያችን ስም እንጠይቃችኋለን፡፡ ሌላም እስር በዚህ ወር እንዳይደገም ይደረግልን!!
ወራቱ ረመዷን ነው፡፡ ይህንን የእስር እርምጃ ተከትሎ በኢንተርኔት የሚካሄዱት አንዳንድ ልብ የሚነኩ ስድቦች እንዲቆሙም እንጠይቃለን፡፡ በተለይ የዘረኝነት ስድቦች እጅግ አሳፋሪና ደረጃችንን ዝቅ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሌላ ሌላውን መጻፍ እንጂ ስድቦቹን ማቆም ይገባል፡፡ “እምቢ!” ቢባል እንኳ እኛ ፈልገን ባላገኘነውና ከፈጣሪ በተሰጠን ዘር፣ ጎሳና ብሄረሰብ መሰዳደቡ ይቁምልን (በተለይ አንዳንዶች በተከበረው የትግራይ ህዝብ ላይ የሚያካሄዱት አስጸያፊ ስድብ በአስቸኳይ መገታት አለበት)፡፡
ወራቱ ረመዳን ነው! በአማን ጀምረነዋል፡፡ በአማን እንጨርሰው ዘንድ ነገሮች በጥንቃቄ ይያዙልን፡፡ አላህ ለሁላችንም ልቦና ይስጠን፡፡ አሚን!!
ወራቱ ረመዷን ነው!!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar