አንዳንዶች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አስከፊ ጭቆናና ፓይለቱ አውሮፕላኑን እንዲጠልፍ እንዳነሳሳው ሲገልጹ ሌሎች ወገኖች ደግሞ ጥገኝት ለመጠየቅ ተብሎ ከተደረገ ስህተት ፈጽሟል ብለው ይተቻሉ።
ባህርዳር አካባቢ ተወልዶ ያደገው ሃይለመድህን አበራ በአንጻራዊ መልኩ ሀብታም ከሚባል ቤተሰብ መምጣቱን የሚናገሩት ፓይለቱንም ሆነ ቤተሰቦቹንም እናውቃለን የሚሉ የባህርዳርና የአካባቢው ሰዎች፣ ፓይለቱ በትምህርቱ እጅግ ጎበዝ የሚባልና ታታሪ ሰራተኛ እንደሆነ ይገልጻሉ።
አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ ሰው ሃይለመድህን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ስላለው ቢሮክራሲና ዘረኝነት ደጋግሞ ይናገር እንደነበር ገልጿል።
ታናሽ እህቱ እንደሆነች የምትገልጽ ትንሳኤ አበራ በበኩሉዋ ሃይለመድህን ” የሰዎችን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል አይደለም እንስሳትን ለመጉዳት የሚፈልግ ሰው አለመሆኑን፣ ከአገር ውጭ ወጥቶ ለመኖር ፍላጎት እንዳልነበረውም ገልጻለች።
በብሄራዊ መልቀቂያ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ትምህረቱን ያጠናቀቀው ሀይለመድህን የጀመረውን የ አርክቴክቸር ትምህርት ትቶ ወደ ፓይለትነት የገባው ለሙያው ካለው ፍቅር የተነሳ መሆኑንም ገልጻለች።
“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህይወቱ ደስታ የራቀው መሰለ” የምትለው እህቱ፣ ስለሁኔታው ሲጠየቅ ” ጠላቶች እንዳሉ እንደሚያምን ፣ ስልኩን እንደጠለፉት እንደሚያስብ፤ በላፕቶፑ ካሜራ ሳይቀር ያዩኛል ብሎ ስለሚሰጋ ካሜራውን ሳይሸፍን እንደማይከፍት እንዲሁም፤ ወጥቶ እስኪገባ ቤቱን ሲበረብሩ የቆዩ ስለሚመስለው ካሜራ ጠምዶ መሄድ ሁሉ እንደጀመረ ገልጻለች።”
” ባጠቃላይ በታላቅ የመንፈስ ጭንቀት እየተሰቃየ ነው”፣ የምትለው እህቱ፣ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህንን ጉዳቱን ለኛ ለቤተሰቡንኳ አብራርቶ አለመናገሩ ነው ” ብላለች።
ሌሎች ጓደኞቹ በበኩላቸው ሃይለመድህን የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ የገባው አጎቱ ባለፈው ጥር ወር ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ከተገደሉ በሁዋላ ነው ይላሉ። አጎቱ ዶ/ር እምሩ ስዩም ባለፈው ጥር ወር ከስራ ሲወጡ ታክሲ ውስጥ ሞተው የተገኙ ሲሆን፣ ዶ/ሩን ማን እንደገደላቸው በውል ባይታወቅም፣ አንዳንድ ወገኖች ግን ግድያው ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በድረገጹ ላይ ባሰፈረው ሪፖርት የፕሮፌሰር እምሩ ስዩም ሞት አስገራሚ መሆኑን ገልጿል።
ሃይለመድህን ከአጎቱ ሞት በሁዋላ እርሱም በተመሳሳይ አደጋ ውስጥ እገኛለሁ ብሎ ሲሰጋ እንደነበር፣ በተለይም በአየር መንግዱ ውስጥ የተሰባሰቡት ካድሬዎች፣ ያሳድዱኛል ብሎ እንደሚያስብ ፓይለቱን ባለፈው ጥር ወር ላይ እንዳገኘው የሚገልጽ ወጣት ለኢሳት ተናግሮአል።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar