የካፒቴን ሃይለመድህን አበራ የጠለፋ ምክንያት በአየር መንገዱ ውስጥ የሚታየውን የአስተዳደር መበላሸት ለአለም ለማሳየት ነው ይችላል የሚለው ምክንያት አሳማኝ ነው ሲሉ አንድ የቀድሞው የድርጅቱ ሰራተኛ ገለጹ
በኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ደህንነት ስራ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ያገለገለውና በክትትልና ደህንነት ስጋት ከአመት በፊት ድርጅቱን ለቆ በስዊዘርላንድ ጥገኝነት የጠየቀው ሚካኤል መላኩ ከኢሳት ጋር ባደረገው ሰፊ ቃለምልልስ፣ በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ዘረኝነትና የአስተዳደር መበላሸት አጋልጧል።
ወጣቱ ፓይለት የተለያዩ አውሮፕላኖችን አብርሮ ልምድ ካካበተ በሁዋላ 767 የተባለውን አውሮፕላን በረዳት ፓይለትነት ለማብረር መቻሉን የገለጸው ሚካኤል፣ በዚህ ደረጃውም ከፍተኛ የሆነ ክፍያ የሚከፈለው በመሆኑ የገንዘብና የምቾት ችግር እንደማያጋጥመው ገልጿል። አብራሪው የ3 ሺ ሰራተኞችን ዋይታ ይዞ መምጣቱን የሚናገረው ሚካኤል፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎኑ ሊቆምለት ይገባል ብሎአል
የካፒቴን ሃይለመድህን የጠላፋ ምክንያት አወዛጋቢ ሆኖ በቀጠለበት ሁኔታ ፣ ካፒቴኑ ከአጎቱ ከዶ/ር እምሩ ስዩም ሞት ጋር በተያያዘ እየተረበሸ መምጣቱን አቶ አሳምነው መላኩ የተባሉ የካፒቴን ሃይለመድህንን አጎት በመጥቀስ በአሶሺየትድ ፕሬስና በክርስቲያን ሞኒተሪንግ ተዘግቧል። አዲስ አበባ የኑቨርስቲ በድረገጹ ባሰፈረው መረጃም የዶ/ር እምሩ አሟሟት መንስኤ እንግዳ እንደሆነ ጠቅሷል። ኢሳት በበኩሉ ከዘመዶቹ ባገኘው መረጃ መሰረት ዶ/ር እምሩ በሰዎች መገደላቸውን አንዳንድ የቤተሰብ አባሎች እንደሚያምኑና አጎቱን ማን ገደላቸው የሚለው ጥያቄ አለመመለሱን ዘግቧል።
ይሁን እንጅ የዶ/ር ስዩም ባለቤት ነኝ ያሉ ወ/ሮ አንጓች ቢተው ባለቤታቸው የሞቱት ታህሳስ ወር ላይ ጧት ፍላሚንጎ አካባቢ ተሳፍረው ቤተመንግስት አካባቢ ሲደርሱ ከጠዋቱ 2፡30 ላይ መሞታቸውን፣ የሞታቸውም ምክንያት በልብ ህመም ምክንያት መሆኑን በመግለጽ ሰው ገደለው ተብሎ የቀረበው ዘገባ ስህተት መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል። ወ/ሮ አንጓች ካፒቴን ሃይለመድህን በአጎቱ ምክንያት እንደተረበሸ ተደርጎ በሚሰጠውን አስተያየት ዙሪያም ምንም የሚያዉቁት ነገር እንደሌለ፣ ከካፒቴኑ ጋር በአመት በአል ወቅት ካልሆነ ብዙም እንደማይገናኙ ተናግረዋል።
ካፒቴን ሃይለመድህን ከአጎቱ ሞት ጋር በተያያዘ ይረበሽ ነበር በማለት መግለጫ የሰጡትን ሌላውን አጎት አቶ አሳምነውን ለማግኘትና ማብራሪያ ለመጠየቅ የተደረገው ሙከራ አልተሰካም። በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየቱን የጠየቅነው ዘጋቢያችን፣ ዶ/ር ስዩም በልብ ህመም መሞታቸውን ካፒቴን ሃይለመድህን የሚያውቅ ከሆነ፣ የሚጨነቅበት ምክንያት አይኖርም፣ ከአጎቱ ሞት ጋር በተያያዘ የሚሰጠው አስተያየትም ትክክል ላይሆን ይችላል ብሎአል።
ጠላፊው አውሮፕላኑን ወደ ጄኔቭ ከመውሰዱ በፊት ሮም ላይ ማረፉን የገለጸቸውን ዜና በተመለከተ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች አውሮፕላኑ ሮም ላይ እንዳላረፈ በመግለጽ አስተያየታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ኢሳት በድጋሜ ተሳፋሪዋን ባነጋገረበት ወቅት፣ በአቋሟ በመጽናት አውሮፕላኑ ሮም ላይ አርፎ ወደ ሚላን ሲያቀና መጠለፉን፣ የበረራ ትኬቱዋን ለኢሳት በመላክ ትክክለኛ መረጃ መስጠቱዋን በድጋሜ ተናግራለች።
ጉዳዩ እንዴት ሊሆን ይችላል ስንል ጥያቄ ያቀረብንለት ሚካኤል መላኩ አውሮፕላኑ ሮም ላይ አርፎአል በሚል የተላለፈው ዘገባ ትክክለኛ ነው ብሎ እንደሚያምን የአየር መንገዱን አሰራር በመግለጽ አስረድቷል
የመንግስት የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን አውሮፕላኑ ካርቱም ላይ ማረፉን ፣ ቀጥሎ ደግሞ ካርቱም ላይ ማረፍ የነበረበት ቢሆንም ተጠልፎ ማረፍ ሳይችል ቀረ ብለው የገለጹት የአየር መንገዱን አሰራር ሳይዉቁ የተናገሩት አሳፋሪ ንግግር ነው ብለዋል። በአየር መንገድ የበረራ ታሪክ አውሮፕላኑ በቀጥታ ከአዲስ አበባ ወደ ሮም እንደሚያርፍ በመግለጽ ካርቱም ላይ ማረፍ ነበረበት የሚለውም ትክክል አይደለም ብሎአል።
አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ፓይለቱ አውሮፕላኑን ይዞ ጄኔቫ ላይ በመሽከርከር ለማስፈራራት ሙከራ አድርጎ ነበር በማለት ዘገባዎችን አቅርበዋል። ይሁን እንጅ እንደ ሚካኤል ገለጻ ማንኛውም አውሮፕላን ከማረፉ በፊት ነዳጅ ማቃጠል ስለነበረበት ፓይለቱ ይህን ማድረጉን እንዲሁም ለ10 ደቂቃ ጉዞ ብቻ የሚበቃ ነዳጅ ነበረው ተብሎ በመገናኛ ብዙሃን የቀረበውም ትክክል ያልሆነና በአየር መንገዱ ህግ መሰረት ለ2 ሰአት በረራ የሚያበቃ መጠባበቂያ ነዳጅ እንደሚይዝ ገልጿል።
የኢትዮጵያን አየር መንገድ የውስጥ አሰራርና ችግሮች በተመለከተ ከሚካኤል መላኩ ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለምልልስ ነገ የምናቀርብ መሆኑን እንገልጻለን;
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar