torsdag 20. februar 2014

ረዳት ፓይለት ሃይለ-መድህን አበራ ብቃት ያለው አብራሪ ነው ተባለ


የኢትዮጵያን አየር መንገድ ንብረት የሆነውን ቦይንግ 767 አውሮፕላን  በመጥለፍ ጄኔቫ ያሳረፈው ሃይለመድህን አበራ፣ ከጸባዩ በተጨማሪ ብቃት ያለው አብራሪ መሆኑን ግለሰቡን የሚያውቁ ሰዎች ለኢሳት ተናግረዋል።
ከስልጠና ጀምሮ የሚያውቁት ጓደኞቹ እንደተናገሩት ሃይለመድህን ለሰዎች ህይወት የሚጨነቅና ጥንቃቄ የሚያደርግ፣ አውሮፕላኑን ከጠለፈ በሁዋላ ተሳፋሪዎች ሳይቸገሩ እንዲያርፍ ማድረጉ የፓይለቱን ብቃት ያሳያል ብለዋል። ምንም እንኳ በረዳት አብራሪነት ደረጃ ቢመደብም፣ ብቃቱና እውቀቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አለመሆኑን ባልደረቦቹ ተናግረዋል።
ኢሳት ባደረገው ማጣራት ደግሞ አውሮፕላኑ ከተጠለፈበት ከሱዳን የአየር ክልል ጀምሮ፣ ፓይለቱ ህዝቡን የሚያስደነግጥ ወይም እንዳይረጋጉ ለማድረግ የተናገረው ነገር አልነበረም። መጸዳጃ ቤት ሄደው የነበሩት ጣሊያናዊው አብራሪ ተመልሰው አውሮፕላኑ እንዲከፈትላቸው በጠየቁበት ጊዜም ቢሆን፣ ፓይለቱ አውሮፕላኑን ጉዳት ላይ የሚጥል ነገር አለመናገሩን ለማወቅ ተችሎአል።
የስዊስ ፖሊስ የጠለፋውን ሂደት በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን እስካሁን አልሰጠም።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar