mandag 3. mars 2014

12 ሺ ቶን ቡና በተጭበርበረ ሰነድ ወደ ውጭ አገር መላኩ ታወቀ

የስነምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በቅርቡ በቡና አስተዳደር ላይ የሚታየውን ችግር አስመልክቶ ያወጣውን ሪፖርት ተከትሎ 12 ሺ ቶን ወይም  1 መቶ 20 ሺ  ኩንታል ቡና በተጭበረበረ ሰነድ ወደ ውጭ ተልኮ መሸጡን አመልክቷል። ኮሚሽኑ ቡናው በማን በኩል ተሰርቆ እንደተላከ እያጣራ መሆኑን የዘገበው ሪፖርተር፣ የሽያጩ ገንዘብም ወደ አገር ውስጥ አለመግባቱን ገልጿል።
ዛሬ ባለው የአለም የቡና የመሸጫ ዋጋ 120 ሺ ኩንታል ቡና ከ16 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይም ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያወጣል። ይህን ያክል ገንዘብ በአንድ ጊዜ በተጭበረበረ ሰነድ መዝረፍ የሚቻልባት አገር ሆናለች የሚለው ዘጋቢያችን፣ ድርጊቱ መንግስት አለ ወይ ያሰብላል ሲል ሃሳቡን አሰፍሯል።
አቶ መለስ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት 10 ሺ ኩንታል ቡና መጥፋቱ ይታወቃል። ስለዚሁ ጉዳይ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ መለስ መንግስታቸው እያጣራ መሆኑን ተናግረው ነበር። ይሁን እንጅ የምርመራው ውጤት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የታወቀ ነገር የለም።
ዘጋቢያችን እንደሚለው ጸረ ሙስና ኮሚሽን እየመረመርኩ ነው ቢልም፣ የምርመራው ውጤት ታፍኖ ሊቀር የሚችልበት እድሉ ሰፊ ነው። በጉዳዩ ዙሪያ የንግድ ሚኒስቴር ባለስልጣናትን ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar