mandag 10. mars 2014

አንድነት ፓርቲ 2ኛውን ዙር የሚሊዮኖችን እንቅስቃሴ በተለያዩ ከተሞች ሊጀምር ነው



ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ለሦስት ወራት በሚካሄደው ክፍል ሁለት “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ሪፎርም” በሚለው ዘመቻ፣ በዋነኛነት በተመረጡ 14 ከተሞች እና በሦስት ተጓዳኝ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ ይካሄዳል።
የመሬትን አጀንዳ የሁለተኛው ዙር የመታገያ አጀንዳ ለምን እንዳደረገ ፓርቲው ሲያብራራ፣ “በባለሃብት ስም ገበሬው ከይዞታው መፈናቀሉ፤ በከተሞች በልማት ስም ዜጎች እየተፈናቀሉ ለጎዳና ላይ ኑሮ መዳረጋቸው፤ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መበቶቻቸው እየተጣሱ ለማህበራዊ ቀውስ መዳረጋቸውው ዛሬም ተጠናክሮ መቀጠሉንና በተበጣጠሰ ትንንሽ የመሬት ይዞታ ላይ በኃይል የመፈናቀል ተራቸው እስከሚደርስ እየተጠባበቁ ያሉትም ቢሆኑ ዛሬም በዶማ እና በበሬ አፈር እየገፉ ከአቅማቸው በላይ በሆነ የማዳበሪያ እዳ ተቀፍድደው አንገታቸውን ደፍተው በሰቀቀን ለመኖር ተገድደዋል” ብሎአል።
“መሬትን ዋነኛ የሙስና ማዕከል ያደረገውን ሥርዓት በመቃወም የህዝብ የለውጥ ፍላጎት እንዲከበር አደባባዮች በለውጥ ፈላጊ ሰላማዊ ታጋይ ህዝብ እንዲሞሉ እንዲሞሉ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀስ የሚገልጸው አንድነት፡ አምባገነናዊ ሥርዓቱ በሰላማዊ ትግል ተሸንፎ ዜጎች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት እንዲሆኑ፤ ሃብት የማፍራት፤ የመያዝ እና የማስተላለፍ መብታቸው እንዲጠበቅ፤ በኮሚኒቲ /በማህበረሰብ/ በጋራ ከተያዘ፤ በመንግስት ይዞታነት ከተከለለ እና በተቋማት ይዞታነት ከታወቀ መሬት በቀር በዜጎች የተያዘ መሬት የግል ይዞታ ሆኖ እንዲከበር ለማድረግ እንደሚታገል አስታውቋል።
በህዝባዊ ንቅናቄው የአደበባይ ህዝባዊ ስብሰባ እና ሰላማዊ ሰልፍ የሚደረግባቸው ቦታዎች አዲስ አበባ፣ ደሴ፣ ሐዋሳ፣ አዳማ/ናዝሬት/፣ መቀሌ፣ ደብረታቦር፣ ደብረማርቆስ፣ ድሬዳዋ፣ ጂንካ፣ ቁጫ፣አሶሳ፣ ነቀምት፣ ለገጣፎ፣  ወልዲያ፣ ጋምቤላ፣ ምዕራብ አርማጭሆ/ አብርሃ ጅራ/፣ይሆናሉ ብሎአል።
አንድነትና መኢአድ ፓርቲዎች በቅርቡ በባህርዳር በብዙ ሺዎች የሚቀጠር ህዝብ ለተቃውሞ እንዲወጣ አድርገዋል። ፓርቲው በመጀመሪያ ዙር የሚሊዮኖች ድምጽ በተለያዩ ከተሞች የተሳካ የተቃውሞ ሰልፎችን ማድረጉ ይታወቃል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar