የኦሮሚያ ክልል እና የኦህዴድ ፕሬዚዳንት የነበሩትና ሰሞኑን ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የአቶ አለማየሁ አቶምሳ የሞት መንስኤ እንዲጣራ የኦህዴድ መካከለኛና ዝቅተኛ ካድሬዎችና አባላት በየመድረኩ ጥያቄ እያነሱ መሆኑ ከፍተኛ አመራሩን ጭንቀት ውስጥ እንደጣለው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገለጹ፡፡
አቶ አለማየሁ ለሞታቸው መንስኤ የሆነው ከምግብ ጋር የተሰጣቸው መርዝ ነው የሚሉ መረጃዎች ኢሳትን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ይፋ መሆኑን ተከትሎ አብዛኛዎቹ መካከለኛና ዝቅተኛ የድርጅቱ አባላትና ካድሬዎች የአቶ አለማየሁ ሞት በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ እንዲቀርብ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ጥያቄ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡
በተለይ ከአቶ አለማየሁ ሞት ጀርባ የቀድሞ የኦሮሚያ ፕሬዚደንት አቶ አባዱላ ገመዳ እጅ አለበት መባሉና ጉዳዩም ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን ጠራርጎ ለማጽዳት አቶ አለማየሁ የጀመሩት እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ነው በሚል መገለጹ አብዛኛውን የድርጅቱን አባላት ቁጭት ውስጥ ጥሏል፡፡
በዚህም ምክንያት አቶ አለማየሁ የጀመሩትን የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን የሚሉ መፈክሮች በየወረዳውና በየቀበሌው በስፋት በመስተጋባት ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡
አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ላቸው የኦህዴድ አባል ለዘጋቢያችን እንደገለጹት የአቶ አለማየሁ ሞት እንዲጣራ ጣያቄ ሲቀርብ ከፍተኛ አመራሩ ይሄ የጸረ ሰላም ሃይሎች አሉባልታ ነው በሚል ምላሽ ለመስጠትና ለማጣጣል ሙከራ እንደሚያደርጉ አስታውሰው የሁሉን አመኔታ ለማግኘት ግን ፍረጃ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ነገሩን በገለልተኛ ወገን ማጣራቱ ይቀል ነበር በማለት ነቀፌታውን አጣጥለውታል፡፡
አብዛኛው አባላት የአቶ አለማየሁ ሞት መንስኤ እንዲጣራ እየወተወተ መሆኑንና የዚህ ጥያቄ መመለስና አለመመለስ በድርጅቱ ቀጣይ ህልውና ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊም ሆነ አሉታዎ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡
ይህ የኦህዴድ አባላትና ካድሬዎች ጥያቄ በተለይም የኦህዴድ ስራ አስፈጻሚ ኮምቴ አባላትን አስጨንቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቅርቡ የሰልጣን ሽግሽግና አዲስ ሹመት ያገኙትን ጨምሮ ኦህዴድን በመምራት ላይ የሚገኙት ስራ አስፈጻሚዎች አቶ ሙክታር ከድር ሊቀመንበር፣ወ/ሮ አስቴር ማሞ ምክትል ሊቀመንበር፣አቶ ዘላለም ጀማነህ፣አቶ ግርማ ብሩ፣አቶ አባዱላ ገመዳ፣አቶ ኩማ ደመቅሳ፣አቶ ሶፊያን አህመድ፣አቶ ድሪባ ኩማ፣አቶ አብዱልአዚዝ አህመድ አባላት መሆናቸው ይታወቃል፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar