torsdag 13. mars 2014

በምእራብ አርማጮ የሽፍታ ቤተሰቦች ናችሁ በሚል ብዙ ነዋሪዎች ታስረው በመሰቃየት ላይ ናቸው


በኢትዮ-ሱዳን ድነበር አካባቢ ነዋሪ የሆኑ የምእራብ አርማጭሆ ነዋሪዎች እና በሽፍታ ቤተሰብነት የተጠረጠሩ ከ20 ያላነሱ ቤተሰቦች ታስረው እንደሚሰቃዩ ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የሽፍቶቹ ቤተሰቦች ለእስር የሚዳረጉት ሽፍቶችን አሳምነው እጃቸውን ለመንግስት እንዲሰጡ ወይም ገድለው እንዲያቀርቡ ለማድረግ ነው። ይሁን እንጅ አብዛኞቹ ሽፍቶች እጃቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰው እንግልት እየጨመረ ነው። በእስር ላይ ከሚገኙት የሽፍታ ቤተሰቦች መካከል መልካሙ አዛናው፣ መልካሙ መንግስቱ፣ ብርሃኔ ደምለው፣ ወ/ሮ አረቄ መላሽ፣ ዳኙ ካሴ፣ ደስታ ካሳ፣ ገብሬ አዳነ፣ ሁናቸው እና ሌሎች ከ20 በላይ ቤተሰቦች በእስር ላይ ይገኛሉ። በእስር ላይ ከሚገኙት በተጨማሪ ሌሎች ደግሞ አፈናውን በመስጋት ጫካ ለማደር ተገደዋል።
ጭንቋና በሚባል ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አረቄ መላሽ ሙቀት የተባለው ልጃቸው በቅርቡ በዚህ ስርአት ውስጥ መኖር አልችልም በሚል መሸፈቱን ተከትሎ፣ ቀሪ ልጆቻቸውን በትነው መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሎአል። ግለሰቡዋ የሸፈተው ልጃቸው እጁን እስካልሰጠ ድረስ በእስር እንደሚማቅቁ በፖሊስ ተነግሮአቸዋል።
ከ5 አመታት በፊት የሸፈተውና እስካሁን የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ሊያውሉት ያልቻሉት የአበራ ጎባው  ቤተሰቦች በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሎአል። አበራ ጎባው  ስርአቱን በመቃወም ከሸፈተበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ወጣቶች እየተቀላቀሉት መምጣቱን የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ።
ጉዳዩን በማስመልከት በሰሜን አርማጭሆ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆነውን ወጣት አባይ ዘውዱን አነጋግረነው ነበር። አባይ እንደሚለው ፓርቲያቸው የሽፍታ ቤተሰቦች ተብለው የሚያዙ ሰዎች መኖራቸውን ማረጋገጡንና ብዙ ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑንና መንግስት ለምን በጸጥታ ሃይሎች ሊይዙዋቸው እንዳልቻሉ ገልጿል
ለሽፍትነት ያበቃቸውን ምክንያትም በስርአቱ በመማረር መሆኑን ወጣት አባይ ይናገራል በሌላ በኩል ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ የምእራብ አርማጭሆ ወጣቶች ” ለሱዳንና ለውጭ ኩባንያዎች መሬት እየተሰጠ እኛ ግን የምናርሰው መሬት አጥተናልና መሬት ይሰጠን” የሚል ጥያቄ አንስተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ከወጣቶች አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ለመረዳት ተችሎአል። ወጣቶቹ ጥያቄቸውን ከወረዳ እስከ ዞን ላሉ ባለስልጣናት ቢያመለክቱም ምላሽ አላገኙም። በዛሬው እለትም ለክልል ባለስልጣናት አቤት ለማለት ከ50 በላይ ተወካዮች ወደ ባህርዳር አቅንተዋል።
ለሱዳን በተሰጠው መሬት አካባቢ በሱዳኖችና በኢትዮጵያውያን መካከል ግጭት እየተከሰተ መሆኑንም የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ። በቅርቡ አብዱ የሚባል የሱዳን ባለሀብት በኢትዮጵያውያን መገደሉን ተከትሎ ሱዳኖች በወሰዱት እርምጃ ሚካኤል የተባለ የአብረሃ ጅራ ነዋሪ መገደሉን የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ኢትዮጵያና ሱዳን ድንበሮቻቸውን በጋራ ወታደሮች ለመጠበቅ በቅርቡ አዲስ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar