በሀረር በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለ2ኛ ጊዜ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ ህዝቡ መንግስትን ተጠያቂ ሲያደርግ፣ መንግስት በበኩሉ ድብቅ የፖለቲካ አላማ ያላቸው ሀይሎችን ያደረሱት ቃጠሎ ነው ይላል።
ቅዳሜ ምሽት ሲጋራ ተራ እተባለ በሚጠራው የንግድ ማእከል ላይ በተነሳው እሳት በርካታ ንብረት ወድሟል። ከሳምንት በፊት መብራት ሃይል እየተባለ በሚጠራው የንግድ ማእከል በደረሰው ቃጠሎ ደግሞ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚቆጠር ሀብት ወድሟል።
በመጀመሪያው ቃጠሎ ወቅት ብስጭታቸውና ቁጣቸውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ የወጡ የሃረር ወጣቶች በፖሊሶች ተደብድበው ሲበተኑ ከ40 ያላነሱ ወጣቶች ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለው እስከ ዛሬ አልተፈቱም።
ባለፈው ቅዳሜ የተነሳውን እሳት ሰበብ በማድረግ ዝርፊያ ሊፈጽሙ ሲሉ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መታሰራቸውን የመስተዳድሩ ሹማምንት ለመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ሲገልጹ፣ ነዋሪዎች በበኩላቸው ከፍተኛውን ዝርፊያ ሲፈጽሙ የነበሩት ፖሊሶች ናቸው ይላሉ። እነዚህ ሰዎች እንደሚሉት ፖሊሶች በተለይም የሞባይል ስልኮችን ሲያሸሹ ነዋሪው በትዝብት ያያቸው ነበር።
አብዛኛው የሃረር ህዝብ እሳት አደጋው መንስኤ መስተዳደሩ ነው ብሎ ያምናል። የመስተዳድሩ ባለስልጣናት ቦታዎችን ለሚፈለጉ ሰዎች ለመስጠት በማሰብ ቃጠሎውን እንደሚያስነሱ ይገልጻሉ
የሃረሪ መስተዳድር የኮሚኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ ” ከደረሰው አደጋ ጋር በተያያዘ ህዝብና መንግሥትን ለማጋጨትና ድብቅ የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማራመድ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ከመንግሥት ጎን በመሆን እንታገላቸዋለን ” በማለት የእሳቱን መንስኤ በስም ያልተጠቀሱት ድብቅ ሃይሎች ያስነሱት ነው በማለት በመስተዳድሩ ላይ የሚሰነዘረውን ወቀሳ ለማስተባበል ሞክሯል።
እንደ ታዛቢዎች ከሆነ ሀረር ከተማ ከመቼውን ጊዜ በላይ በሃዘን ድባብና በቁጭት ተሞልታለች። ህዝቡ ምን ማድረግ እንደሚገባው ግራ ተጋብቶ እንደሚገኝ ታዛቢዎቹ ይገልጻሉ።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar