fredag 14. mars 2014

የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ መልኩ ወጣት የሰማያዊ ሴት አመራሮችና አባላት አለማቀፉን የሴቶች ቀን አስመልክቶ በተዘጋጀ ሩጫ ላይ የመብት ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ፍትህ ጥያቄዎችን በማንሳት መንግስት አፋጣኝ መልስ እንዲሰጥ በተቃውሞ ድምጽ ማቅረባቸውን ተከትሎ በቁጥጥር ስር ውለው ለአምስት ቀናት በእስር ካሳለፉ በሁዋላ ዛሬ በድጋሜ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ፖሊስ በእስረኞቹ ላይ የማደርገው ምርመራ አልተጠናቀቀም በሚል ተጨማሪ የ7 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ቢጠይቅም፣ የእስረኞቹ ጠበቃ የሆኑት አቶ አለሙ ጎቤቦ ” ደንበኞቼ ፈጸሙ የተባለው ወንጀል በአደባባይ የተደረገ በመሆኑ ምንም አይነት ምርመራ አያስፈልገውም፣ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ የዋስትና መብታቸው ይከበርልኝ” ሲሉ ተቃውሞ አሰምተዋል።
የሁለቱንም ክርክር ያዳመጡት ዳኛ፣ የፖሊሶችን ጥያቄ በመቀበል የ4 ቀናት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥተዋል። ችሎቱን የተከታተሉት የሰማያዊ ፓርቲ ሊ/መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ሂደቱን በተመለከተ ላቀረብንላቸው ጥያቄ ፖሊሶችም ሆኑ አቃቢ ህጉ እየተንቀጠቀጡና እየፈሩ ይሰሩ እንደነበር ተናግረዋል።
ሴቶቹ በሩጫው እለት የለበስነውን ቲሸርት ለብሰን እንወጣለን በማለታቸውና ፖሊስ ደግሞ አትለብሱም በማለቱ በተፈጠረው ውዝግብ ችሎቱ ዘግይቶ እንዲጀመር አድርጎታል። በወጣቶቹ ላይ የተወሰደው የእስር እርምጃ ሰማያዊ ፓርቲን ለማዳከምና እንቅስቃሴውን ለመግታት መሆኑን ሊቀመንበሩ ይናገራሉ ። ወጣቶች በከፍተኛ የመንፈስ ጥንካሬ ውስጥ እንደሚገኙ ኢ/ር ይልቃል ተናግረዋል ።
የሰማያዊ ፓርቲ ሴት አመራርና አባላት ሰሞኑን ያሰሙት ተቃውሞ የብዙ ኢትዮጵያውያን መነጋገሪያ ሆኗል። ወጣቶቹ የኑሮ ውድነቱና የመብት አፈናው እንዳስመረራቸው እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ፣ ርእዮት አለሙ፣ እስክንድር ነጋና ሌሎችም ፖለቲከኞች ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቀዋል

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar