አሁን በስራ ላይ የሚገኘውን የይቅርታ ስነስርዓት አዋጅ ቁጥር 395/1996 አዋጅ የሚያሻሻልና የኢትዮጵያን ፕሬዚደንት ስልጣን የሚቀንስ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡
በፍትህ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ም/ቤት ታይቶ ወደፓርላማ የተመራው ረቂቅ አዋጅ እንደሚያሳየው አሁን በስራ ላይ ባለው አዋጅ የፍትህ ሚኒስቴር ይቅርታ ቦርድ ጽ/ቤት ይቅርታ የጠየቁ ታራሚዎችን ጉዳይ መርምሮ የውሳኔ ሃሳብ ለፕሬዚደንቱ ሲቀርብ በፕሬዚደንቱ ውሳኔ ይቅርታው ሲሰጥ የቆየ ሲሆን በአዲሱ ማሻሻያ አዋጅ ግን ይህ ተሽሮ ፕሬዚደንቱ ቦርዱ መርምሮ የሚያቀርብለትን የማጽደቅ ስራ ብቻ እንዲኖረው ደንግጓል፡፡
በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ 1 እንደተመለከተው “ፕሬዚደንቱ የይቅርታ ቦርድ የውሳኔ ሃሳብን መሰረት በማድረግ ይቅርታ ይሰጣል” ይላል።ይቅርታ በሚሻርበት ወቅትም ፕሬዚደንቱ ማየት ሳያስፈልገው በቦርዱ ውሳኔ ብቻ እንዲፈጸም በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ተደንግጎአል፡፡
በክልል የሚገኙ ታራሚዎችን ጉዳይ በአጭር ለመቁዋጨት ሲባል ፕሬዚደንቱ ስልጣኑን በውክልና ለክልሎች እንደሚሰጥ ተደንግጎአል፡፡ በዚህ ማሻሻያ ህግ መሰረት ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች በሰጡት ውሳኔ መሰረት ፍርደኞች ይቅርታ ከጠየቁ በዚህ ሕግ እንደሚዳኙ ተመልክቶአል፡፡
የይቅርታ ቦርዱ አባላት ካልነበሩ አካላት መካከል የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ምክትል ዳይሬክተር እና ሚኒስትር ዴኤታ በቦርዱ እንዲካተቱ አዋጁ ይፈቅዳል፡፡
ሸብርተኝነት፣ በመሰረተ ልማት አውታር ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ሙስና፣ግብረሰዶማዊነት፣የመድፈር ወንጀል እና የመሳሰሉት ይቅርታ የማያሰጡ ተብለው ከተዘረዘሩት ወንጀሎች መካከል ይገኙበታል።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar