የ2007ቱ ምርጫ ሊካሄድ የቀረው አንድ ዓመትና የጥቂት ወራት ጊዜ ብቻ ነው። ለምርጫው የሚቀረው ጊዜ አጭር እንደመሆኑ መጠን በፓርቲዎች፣ በቦርዱ በሲቪል ማኅበረሰቡና በሚዲያው በኩል ልዩ ልዩ ቅድመ ዝግጅቶች የሚጀመርበት ወቅት ነው።
ቦርዱ ለ2007ቱ ምርጫ እያደረገ ስላለው ጉዳይ ለመጠየቅ ወደ ሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ ደውለን ነበር። ሕዝብ ግንኙነቱ ደግሞ ወደ ጽ/ቤት ኋላፊው ቢመሩንም፤ የጽ/ቤት ኃላፊው ደግሞ መልሰው ወደ ሕዝብ ግንኙነቱ መርተውናል። በመካከሉ የህዝብ ግንኙነቱ አላገኘናቸውም። ይህ መመላለስ በራሱ ለምርጫው ያለውን የዝግጅት ፈዛዛነት የሚጠቁም ቢመስልም ሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2006 ዓ.ም የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና በአዲስ ዘመን የፊት ገፅ ላይ “የምርጫ ቦርድ ዝግጅቱን አጠናክሯል” በሚል የሰጡትን መረጃ በመጠኑ ለመጠቀም ተገደናል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ለጋዜጣው እንደገለፁት፤ ቦርዱ የ2002ቱን ምርጫ መገምገሙንና ከግምገማውም ውጤት መገንዘብ የተቻለው ቦርዱ የሰው ኃይልን በማጠናከርና አቅሙን በማጎልበት ረገድ ድክመት መታየቱን ገልፀዋል። ያንን ክፍተት ለመሙላት ቦርዱን በሰው ኃይል ከማጠናከር ባሻገር ለፓርቲዎች፣ ለሲቪል ማኅበራትና ለመገናኛ ብዙሃን ሰፋ ያለ ስልጠና መስጠት መጀመሩን ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት 51 ክልል አቀፍ እና 24 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች መኖራቸውን ገልፀው ቀደም ሲል 75 የነበረው የፓርቲዎች ቁጥር ወደ 74 ዝቅ ማለቱን ገልፀዋል። ቦርዱም የራሱን የሰው ኃይል ለማጠናከር በክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት 350 ሰራተኞች ይቀጥራል ብለዋል። በ40 ያህል የሀገሪቱ ቋንቋዎች ለሕዝቡ የምርጫ ትምህርት መሰጠቱን ገልፀዋል። ምክንያቱን በግልፅ ባይጠቅሱትም ሴት ጋዜጠኞችን ለብቻ እናሰለጥናለንም ብለዋል።
ፈዛዛው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅድመ-ዝግጅት
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የ2007ቱን ምርጫ በተመለከተም አመርቂ ዝግጅት እያካሄደ አይመስልም። የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባልና የሕዝብ ግንኙነት አባል አቶ ጥላሁን እንዳሻው ግን መድረክ “የዝግጅት ችግር የለበትም” ይላሉ። የመድረክ መሰረታዊ ችግር የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብና ዜጎችን አንድ ለአምስት የሚጠረንፈው የገዢው ፓርቲ “የምርጫ ሠራዊት” የምርጫ ስትራቴጂ ነው ብለዋል።
መድረክ እንደ መድረክ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ገዢው ፓርቲ ውጤታማ ሆኜበታለሁ የሚለውን “የምርጫ ሠራዊት” ስትራቴጂ ሊያስለውጥ ወይም ሊፈትን የሚችል አዲስ ስትራቴጂ ይዞ መቅረብ አልቻለም። ፓርቲው ምርጫው ሊካሄድ የአንድ ዓመት ጊዜ ያህል ቢቀረውም በፓርቲ ደረጃ የምርጫ ስትራቴጂና እቅድ አላዘጋጀም። ከዚህ ይልቅ አቶ ጥላሁን ቀደም ሲል ይነሱ የነበሩ አቤቱታዎችን አሁንም የማስተጋባትን ስልት ቅድሚያ የሰጡት ይመስላል። በአቶ ጥላሁን ገለፃ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና የተወዳዳሪነት መንፈስ እንዲኖረው ገዢው ፓርቲ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል። የአቶ ጥላሁን አቤቱታ (Old Complain new election) እንደሚባለው የ2007ቱ ምርጫ በሀገሪቱ የምርጫ ታሪክ ለአምስተኛ ጊዜ ቢካሄድም ምርጫውን በተመለከተ መድረክ አዲስ ነገር መፍጠር እንዳልቻለ አመላካች ሆኗል። በመድረክ በኩል የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ረገድ እንደ ፓርቲ የቀየሰው ስልት እንደሌለም ከአቶ ጥላሁን ገለፃ መረዳት ይቻላል። በእሳቸው አገላለፅ ኢህአዴግ የዘጋውን የፖለቲካ ምህዳር ለማስከፈት ከፓርቲው ይልቅ በአግባቡ ያልተደራጀው ሕዝቡ እንዲወጣው የሚፈልጉ ይመስላል።
ከዚህ በተጨማሪ “የሕዝብ ድጋፍ ችግር የለብንም” የሚሉት አቶ ጥላሁን ሕዝብ መድረክን በደፈናው ይደግፋል ከማለታቸው ባለፈ የሚደግፋቸውን ሕዝብ በአግባቡ ስለማደራጀታቸው የሰጡት ማረጋገጫ የለም። መድረክ እንደ መድረክ ሕዝብን ከማደራጀት ይልቅ የብሶት ጋጋታ በገዢው ፓርቲ ላይ ከማጧጧፍ ባለፈ ጠንካራ ሕዝባዊ መደላደል የፈጠረ አይመስልም። የሕዝባዊነት መደላድል ለመፍጠር የሄደበት እርቀት ገዢውን ፓርቲ ለመውቀስ ከሄደበት እርቀት አንፃር ሊመጣጠን የቻለ አይመስልም። ገዢው ፓርቲ በስልጣኑ ለመቀጠል ሲል ይፈጥራቸዋል የሚባሉትን የአስተዳደር፣ የፖለቲካ የሕግና አልፎ አልፎ ሕገወጥ የኃይል እርምጃዎችን በማጋለጥ ብቻ የፖለቲካ ትግል ማድረጉ ውጤታማ እንደማያደርግ በቂ ግንዛቤ የተያዘ አይመስልም።
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ፓርቲ (አዴፓ) መድረክና ሌሎች ፓርቲዎች የሚያነሱዎቸውን አቤቱታዎች ያነሳል። አቤቱታዎቹን የሚያነሳባቸው የአገላለፅ መጠን (tone) እንደሌሎቹ ፓርቲዎች አይደለም። ይሄ ፓርቲ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ከሌሎች ተቃዋሚዎች ዘንድ የተአማኒነት ጥያቄ ስለሚነሳበት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከሰጠው ሕጋዊ እውቅና በተጨማሪ ከሌሎች ፓርቲዎች ዘንድ የፖለቲካ እውቅና ይፈልጋል።
የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ወጣት ኤርምያስ ባልከው የሚያረጋግጡትም ይሄንኑ ነው። ፓርቲያቸው በቅርቡ ጉባኤ አድርጎ አዲስ አመራር በመረጠበት ወቅት ጉባኤው ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል በ1997ቱ ምርጫ የተፈጠሩ ስህተቶችን በማረምና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለአዴፓ የፖለቲካ እውቅና የሚሰጡ ከሆነ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁነት መኖሩን አስታውቀዋል።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ፓርቲው ቀደም ሲል በየክልሉ የነበሩ መዋቅሮቹን ለማጠናከር በሰሜን፣ በምስራቅና በደቡብ የሀገሪቱ አንዳንድ ክፍሎች መጠነኛ እንቅስቃሴ ከማድረጉ ባለፈ፤ አንድ ዓመት ለቀረው የ2007 ምርጫ አመርቂ እንቅስቃሴ እያደረገ አለመሆኑን ከፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ገለፃ መረዳት ይቻላል። በቀጣይ ጊዜአት የ2007 ምርጫ ማኒፌስቶ ዝግጅትና የዕጩ ምልመላ ስራዎች ለማካሄድ ገና በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አቶ ኤርሚያስ ሳይገልፁ አላለፉም።
የ2007ቱ ጠቅላላ ምርጫ ስርዓትን የመለወጥ አቅም ይኖረዋል ብሎ ለመገመት አስቸጋሪ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኤርሚያስ ፓርቲያቸውን ግን ኅብረተሰቡ ውስጥ ካሉ ስር የሰደዱ ችግሮች አንፃር ሕዝቡ በገዢው ፓርቲ ላይ ካለው ቅሬታ አንፃር ጠንካራ ተፎካካሪ የመሆን እድል እንዳለው ገልፀዋል። ፓርቲው የመራጬን ልብ ለመግዛት የሚያዘጋጀው ማኒፌስቶ እንዳለውም አቶ ኤርሚያስ የጠቀሱ ሲሆን፤ በተለይ ፓርቲያቸው ኢህአዴግን ጨምሮ አዴፓ በሚሳተፍበት የጋራ መድረክን ደንብ በማሻሻል ጭምር በ2007 ምርጫ የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።
ለምርጫው አጀንዳ የሚሆኑ በርካታ የኅብረተሰቡ ችግሮች መኖራቸውን ያወሱት አቶ ኤርሚያስ የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም፣ የኑሮ ውድነቱ፣ የኢኮኖሚ ጥያቄዎችና የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመከበር ጨምሮ በርካታ አጀንዳዎች ተዘርዝረው የሚቀርቡበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
በ2007ቱ ምርጫ የአባይ ግድብ ለምርጫ ፍጆታ መዋል የለበትም ሲሉ አጠንክረው የተከራከሩት ደግሞ የመድረክ ተወካይ አቶ ጥላሁን ናቸው። ግድቡ የኢህአዴግ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን የባንዲራ ፕሮጀክት ነው ብለዋል። መድረክ በ2001 ባዘጋጀው ማኒፌስቶ ውስጥ አባይን እና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ተፋሰሾችን ለመገደብ አቅዶ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
መድረክ ከኢህአዴግ የሚለይባቸው ሌሎች የፖሊሲ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ዋነኛ አጀንዳው የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መክሸፉን፣ በኑሮ ውድነቱ ሳቢያ በኅብረተሰቡ ላይ እያደረሰ ያለው ጫና እንዲሁም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ማኅበራዊ ችግሮች እንዲሁም በየደረጃው ያሉ አስከፊ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን አጉልቶ እንደሚያወጣ ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ ያሉትም የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ገቢና ጥቅም ጋር እየተገለፁ አለመምጣታቸው፤ በዚያው መጠን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እያስከተሉ መሆኑን ሕዝቡ እየተገነዘበ የመጣበት በመሆኑ የመድረክ ትኩረት በሕዝቡ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ማኅበራዊ ችግሮች ላይ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። ለሁሉም የምርጫ ሂደቱ ስኬታማና ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ግን ኢህአዴግ የዘጋውን የፖለቲካ በር ሲከፍት እና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ታማኝ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው ብለዋል። “ተዘግቷል” ያሉትን የፖለቲካ በር ለማስከፈት ግን ፓርቲያቸው የነደፈው ስልት እንደሌለ በደፈናው “ሕዝቡን ይዘን” ከማለት ባለፈ ምንም አይነት ዝግጅት እንደሌለ ከአጠቃላይ ገለፃቸው መገንዘብ ይቻላል።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትም (መኢአድ) በአሁኑ ወቅት በክልል፣ በዞንና በወረዳ ያሉ መዋቅሮቹን መልሶ የማጠናከር (revisit) ከማድረግ ባለፈ ለ2007ቱ ጠቅላላ ምርጫ የተለየ የምርጫ ሰትራቴጂ አለማዘጋጀቱን የገለፁት ደግሞ የፓርቲው ፕሬዚደንት አቶ አበባው መሐሪ ናቸው። አቶ አበባው እንደ ሌሎቹ የፓርቲ አመራሮች የቀጣዩ ዓመት ምርጫ ዴሞክራሲያዊነት ሊለካ የሚችለው ገዢው ፓርቲ በሚከፍተውና በሚያጠበው የፖለቲካ ምህዳር ብቻ የተወሰነ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ አቶ አበባው ገለፃ፤ ፓርቲያቸው ሙሉ በሙሉ ወደ ምርጫ ሲገባ አባላቱ ከስራ እንዲፈናቀሉ፣ ገበሬዎችም መሬታቸውን የሚነጠቁበት ሁኔታ በመሆኑና በምርጫው ውስጥ ከሚደረገው የተሳትፎ ጥረት ጎን ለጎን አባላቱ ላይ የሚደርሰውን ማዋከብ ዋነኛውን የምርጫ ጊዜአቸውን እንደሚሻማ ነው ያስረዱት።
በአቶ አበባው እምነት፤ በምርጫው ጠንካራ ዝግጅት ለማድረግ በቅድሚያ የፖለቲካ ምህዳሩ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ አበባው፣ የፖለቲካ መድረክ ነፃ እስኪሆን ድረስ ሕዝቡን ለማንቀሳቀስ እንኳ አስቸጋሪ እንደሆነ ነው ያስረዱት።
በአሁኑ ወቅት ተዋህዶ በጋራ የመስራት እና በክልል ያሉ መወቅሮችን የማጠናከር ስራ ጎን ለጎን እየተካሄደ እንደሆነ አቶ አበባው የጠቀሱ ሲሆን፤ የፓርቲው የምርጫ ማኒፌስቶ ወቅታዊ ከማድረግ ባለፈ በመሰረታዊነት የሚለወጥ አለመሆኑን ነው የገለፁት። ዋናው ችግር ምርጫው መምጣቱን ተከትሎ አባሎቻችን ላይ የሚደርሰው ማዋከብ ነው ብለዋል።
የ2007ቱ ጠቅላላ ምርጫ ሥርዓት የመለወጥ አቅም ይኖረዋል የሚል ግምት ለመያዝ ከወዲሁ አስቸጋሪ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አበባው፤ የፖለቲካ ለውጥ ተለዋዋጭ በመሆኑ ጊዜውን መጠበቅ ነው ብለዋል። ለአሁኑ ግን ፓርቲያቸው ለምርጫው ሲል የተለየ ዝግጅች እያደረገ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ይልቁኑ ኢህአዴግ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መጠናከር ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት መክረዋል።
በአሁኑ ወቅት እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት ችግር፣ ሥራ አጥነትና ውስብስብ የሆነው የማኅበራዊ አገልግሎት ችግሮች ስር እየሰደዱ በመምጣታቸው የራሱ የኢህአዴግ ካድሬዎች በማጉረምረም ላይ መሆናቸውን አቶ አበባው አስረድተዋል። አሁን ካለው የተባባሰ ችግር አንፃር በ2007ቱ ምርጫ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ ሊቀጥል የሚችለው ምርጫውን በዱላ ወይም በኃይል ከተጠቀመ ብቻ በመሆኑ ሁሉም ነገር በገዢው ፓርቲ እጅ ነው ብለዋል።
የአንድነት ለዴሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ አንድነት በተመለከተ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነቱ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው በበኩላቸው ተጠይቀው በቅድሚያ ፓርቲያቸው በምርጫ የሚያምን ፓርቲ እንደመሆኑ ሕዝቡ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ተጠቃሚ መሆን አለበት ብሎ እንደሚያምን ገልፀዋል። ለ2007ቱም ምርጫ ፓርቲያቸው የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች እያደረገ መሆኑን፣ የመጀመሪያው ፓርቲው የቆመለትን ፖሊሲ ለሕዝብ ለማቅረብ በሚመች መልኩ የአማራጭ ፖሊሲ ትንተና እየተሰራ መሆኑን፣ የፓርቲው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ክለሳም ከምርጫው እና ወቅቱ ከሚጠይቀው ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ተብራርቶ ተዘጋጅቶ በቅርቡም ለሕዝቡ ለውይይት እንደሚቀርብና ጎን ለጎንም ማኒፌስቶ የሚያዘጋጅ ኮሚቴ ተዋቅሮ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል።
የፓርቲውን ድርጅታዊ አቅም በማጎልበት በኩል አዲሱ የፓርቲው አመራር ከተመረጠ በኋላ በቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ በመላ ሀገሪቱ 34 ጽ/ቤቶች ይከፍታል ያሉት አቶ ሀብታሙ በቅርቡም በአዳማ፣ በሻሸመኔ፣ በሐዋሳ፣ በአዴት እና በደብረ ማርቆስ ከተሞች ላይ አዳዲስ ጽ/ቤት ተከፍተዋል ብለዋል። በአዲስ አበባም የፓርቲው የአዲስ አበባ ም/ቤት መቋቋሙን የጠቀሱት ሕዝብ ግንኙነቱ የአዲስ አበባው ም/ቤት 138 መቀመጫ እንዲኖረው በማድረግ ለአዲስ አበባ አስተደደር አቻ ቁጥር ም/ቤት መቋቋሙን ገልፀዋል። ከ23 ወረዳዎች ስድስት አባላት ተወክለው ም/ቤቱ መሰየሙን አስረድተዋል። በተመሳሳይ 24 ወረዳዎች ተመሳሳይ ም/ቤቶች ተመስርተው ወደ ቀበሌ ደረጃ እየወረድን ነው ብለዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የዳያስፖራው ተሳትፎ አግባብ ባለው ሁኔታ እንዲመራና ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዲሰፍን አዳዲስ የድጋፍ ቻፕተሮችን ይከፍታል ብለዋል። በቅርቡም የፓርቲው ልዑክ ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን አሜሪካ እንደሚያቀና ገልፀዋል። ጎን ለጎን ከዲፕሎማሲው ማኅበረሰብ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ልዩ የመረጃ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ድረገፅ መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል። በተያያዘም የምርጫ ሂደቱ አካል ነው ያሉት ፓርቲዎችን ወደ ውህደትና ትብብር የማምጣት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል። የፓርቲውንም ልሳን ወደ ሕትመት ለመመለስ የማተሚያ ማሽን ተገዝቶ ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ሕትመት ይገባልም ብለዋል።
አንድነት ፓርቲ የቤት ስራውን ሳይሰራ በገዢው ፓርቲ ተፅዕኖ ላይ ስንፍናውን አያላክክም የሚሉት አቶ ሀብታሙ ፓርቲያቸው ከወዲሁ የዕጩ ምልመላና ታዛቢዎችን ማደራጀት መጀመሩን ጠቅሰው ነገር ግን ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ምህዳሩን ማጨለሙን መቀጠሉ ግን ያሳስበናል ብለዋል። ገዢው ፓርቲ የአውራ ፓርቲ ሚናነቱን በመተው ወደ መድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲመጣ አሳስበዋል።
በቀርቡም የተጀመረው “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባለቤትነት” የሚለውን ሕዝባዊ ንቅናቄ ለማካሄድ በ14 ዋና ዋና ከተሞች እንዲሁም በሦስት ተጓዳኝ አነስተኛ ከተሞች የምናደርገው እንቅስቃሴ ከወዲሁ ለመግታት እንቅፋቶች እየተፈጠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። በዚሁ ሕዝባዊ ንቅናቄ ላይ በአዲስ አበባ ሕዝባዊ ውይይት ለማድረግ በኢትዮጵያ ስብሰባ ማዕከልና በመብራት ኃይል አዳራሽ ሕዝባዊ ውይይት ለማድረግ ከፍተኛ ችግር ማጋጠሙን ጠቅሰዋል። ይህም የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብና የጉልበት ፖለቲካ መቀጠሉን ማሳያ ነው ብለዋል።
የሀገሪቱ ስርዓት በምርጫ መለወጥ አለበት የሚለውን ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌ አክብረው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሀብታሙ፤ ፓርቲያቸው ለምርጫው በሙሉ አቅሙ ተዘጋጅቶ ሲያበቃ ገዢው ፖርቲ አፈናውን ከቀጠለ በዓለም ላይ ያሉትን ከ150 በላይ የሰላማዊ ትግል ስልቶች አሙዋጦ እንደሚጠቀሙ ገልፀዋል። ገዢው ፓርቲ የአፈና ስርዓቱን ከቀጠለ በሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እናስገድዳለን ብለዋል። ይህንንም ከምርጫው ዝግጅት ጎን ለጎን ገዢው-ፓርቲ በሕገ-መንግስቱ በተቀመጠው መልኩ ስልጣን በምርጫ መያዝ ያለበት የሚለውን ድንጋጌ እየሻረ የአፈና ስልት የሚጠቀም ከሆነ ሕዝቡ እምቢ እንዲል በማድረግ የኢትዮጵያ አደባባዮች በሰላማዊ ታጋዮች እንዲሞሉ እናደርጋለን። ከዚህ ሁሉ በፊት ግን እኛ የውስጥ የቤት ስራችንን በመስራት ላይ ነን ብለዋል፡፡ በቀጣይ ሳምንት የኢህአዴግን ጨምሮ የሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የቅድመ-ምርጫ ዝግጅት ለመቃኘት እንሞክራለን።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar