søndag 31. mars 2019

አዲስ አበባ የጽንፈኝነት ሒሳብ ማወራረጃ መሆን የለባትም!

31 March 2019

የአዲስ አበባ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጥያቄ የማንሳትም ሆነ የመፍትሔ ሐሳብ የማቅረብ መብት አለው፡፡ በአዲስ አበባ ጉዳይ የሚደረግ ንግግርም ሆነ ውይይት፣ ክርክርም ሆነ ድርድር ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆን ይኖርበታል፡፡ ስለመላዋ ኢትዮጵያም ሆነ ስለአዲስ አበባ የሚነሱ ጥያቄዎችም ሕጋዊ፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖራቸው ሲደረግ የጽንፍ ግብግቦች ይወገዳሉ፡፡ ከዴሞክራሲ የጨዋታ ሕግ ያፈነገጡና የአንድ ወገን የበላይነትን ለመጫን የሚደረጉ መውረግረጎች የማያስፈልጉትን ያህል፣ በስሜታዊነት እየተነዱ ለፍጥጫ የሚዳርጉ ደመነፍሳዊ እንቅስቃሴዎችም ለማንም አይጠቅሙም፡፡ የአዲስ አበባም ሆነ የመላ አገሪቱ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በጉልበት ሳይሆን፣ በጨዋነትና በሠለጠነ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ‹አዲስ አበባ የማን ናት?› የሚለው አሰልቺ ጥያቄ ከኢትዮጵያውያን አዕምሮ ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ ይህ የስግብግብነት መገለጫ የሆነ ጥያቄ ለአርቆ አሳቢዎቹና አስተዋዮቹ ኢትዮጵያውያን አይመጥናቸውም፡፡ አዲስ አበባ ከመላ ኢትዮጵያውያን አልፋ ልክ እንደ ኒውዮርክ፣ ጄኔቫና ብራሰልስ የዓለም ከተማ መሆኗ መታወቅ አለበት፡፡ የኋላቀሩ የጽንፈኝነት ሒሳብ ማወራረጃ መሆን የለባትም፡፡
ኢትዮጵያውያን በአዲስ አበባም ሆነ በመላ አገሪቱ የሚያሳስቧቸው በርካታ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ከሰብዓዊና ከዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ጀምሮ፣ እስከ መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ድረስ ከመጠን ያለፉ ችግሮች አሉ፡፡ ከድህነት ወለል በታች በሆነ ኑሮ በርካታ ሚሊዮኖች ይማቅቃሉ፡፡ የባሰባቸው ደግሞ በአደገኛ የጉዞ መስመሮች አገር ለቀው ይሰደዳሉ፡፡ እንደ ሰደድ እሳት በሚፋጅ የኑሮ ውድነት የሚጠበሱ ዜጎች ቁጥር አታካች ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ በተቃርኖ የተሞላው ፖለቲካ የአቅጣጫ መጠቆሚያ እንደሌላት መርከብ በከንቱ ይባዝናል፡፡ ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦችና ስብስቦች በእያንዳንዱ ጉዳይ ቅራኔ ሲፈበርኩ ውለው ያድራሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ቅደም ተከተልና ዋና ሥራችንን መለየት ካልቻልን፣ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች የምንፈጥራቸው ችግሮች ተያይዘን እንድንጠፋ ያደርጉናል፡፡ በኢትዮጵያ የዛሬ ዓመት የተጀመረውን ለውጥ እያደናቀፉ ያሉት ፋይዳ ቢስ ተቃውሞዎችና ጥርጣሬዎች ናቸው፡፡ አንድ ላይ መቆም ሲቻል በተቃርኖ መለያየት መዘዙ የከፋ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ጉዳይ ሲነሳ ‹‹ልዩ ጥቅም›› የሚባለውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በመጥቀስ፣ ሁሉንም ነገር ለማጋበስ ማሰብ ዕብደት ነው፡፡ አዲስ አበባ በውስጧ አቅፋ የያዘቻቸው ነዋሪዎቿ (ከመላ አገሪቱ የተሰባሰቡ መሆናቸው ታሳቢ ሆኖ)፣ በዙሪያዋ ያሉ አርሶ አደሮች፣ ብዙ ነገሮችን የሚመጋገቡ ዙሪያዋን ያሉ ከተሞች፣ ወደፊት አዲስ አበባ መጥተው ለመኖር የሚያስቡ ዜጎች፣ ወዘተ. እንዳሉ መረሳት የለበትም፡፡ ስለዚህ የሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገ ሕጋዊ፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ አሠራር እንዲሰፍን የሁሉም ድርሻ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ መተሳሰብን፣ ሰጥቶ መቀበልንና ሰብዓዊነትን እየገፉ በጉልበት እንሞካከር ማለትም ሆነ ቅራኔ መዝራት ለማንም የማይጠቅም ኋላቀርነት ነው፡፡ በየትም ዓለም እንደሚታወቀው ከተማ ይሰፋል፣ ያድጋል፣ ይዘምናል፡፡ ከገጠርና ገጠር ቀመስ ከሆኑ ከተሞች የሚመጡ ሰዎችን ይቀበላል፡፡ የግብርና ምርቶችን ከአካባቢው አርሶ አደሮች ሲወስድ፣ ለአርሶ አደሮች የኢንዱስትሪ ምርቶችን ያቀርባል፡፡ ሁለቱ በበርካታ ጉዳዮች እየተገናኙ ጥቅሞቻቸውን በፍትሐዊነት ያስከብራሉ፡፡ በዚህ ሒደት ደግሞ አንዱ ሌላውን እንዳይበድል ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ በዚህ መንፈስ ተከባብሮና ተባብሮ መሥራት ሲቻል መቃረን ፋይዳ ቢስ ይሆናል፡፡
በአሁኑ ጊዜ እጅግ በጣም አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ለውጡን የሚመራው ቡድን ላይ ጥርጣሬና ተቃውሞ ማየሉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለውጡ ተደናቅፎ ወደ ኋላ መመለስ ከተጀመረ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ይገባል፡፡ አሁን ዋነኛው ጉዳይ ዴሞክራሲ የሚፈልጋቸውን መሠረታዊ ነገሮች ማመቻቸትና ማበልፀግ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ንጣፍ የሆኑት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበር፣ የዴሞክራሲ መደላድሎችን ማመቻቸት፣ በሚለያዩ ጉዳዮች ላይ በጨዋነትና በሥርዓት መነጋገር፣ በሐሰተኛ መረጃዎች ላይ በመንጠልጠል ለፀብ አለመፍጠንና ንቃተ ህሊናን ማጎልበት ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህንን የዴሞክራሲ ጅምር በጥያቄዎችና በጫጫታዎች ጋጋታ እንዲቀጭ ዕድል ከመስጠት ይልቅ፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ መፍትሔ ለመስጠት መትጋት ይሻላል፡፡ ከዚህ በፊት ያጋጠሙ መልካም ዕድሎች በተደጋጋሚ እንዴት እንዳመለጡ ይታወቃል፡፡ አሁንም ሌላ ዕድል ይኖራል በማለት ይኼንን ዕድል ማበላሸት የማይወጡት ችግር ውስጥ ይከታል፡፡ አዲስ አበባን የሁላችንም ናት ብሎ የበለጠ ማሳደግና ማስዋብ በታሪክ ያስከብራል፡፡
የአዲስ አበባ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ መገንዘብ ያለባቸው፣ ከጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍና ኪሳራ በመለስ ያለው የጋራ ጥቅም እንደሚበልጥ ነው፡፡ በተለይ የፌዴራል መንግሥት፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከወገንተኝነት የነፃ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህ ኃላፊነት ከወገንተኝነት ነፃ እንዲሆን የሚጠየቀው እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የመሰለውን ካርድ እየመዘዘ ሲመጣ፣ የማይወጡበት ቅርቃር ውስጥ ስለሚከት ነው፡፡ በግል፣ በመንግሥት ወይም በፓርቲ የተለያዩ አቋሞችን እያንፀባረቁ ማደናገር አይገባም፡፡ ሕዝብም ይህንን ግልጽነት ይጠይቃል፡፡ በሌላ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ የፖለቲካ አቀንቃኞች ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል፡፡ ሕዝብን ለጋራ ዕድገት ከማሠለፍ ይልቅ ለማቃረን ነገር መቆስቆስ ውጤቱ ተያይዞ መጥፋት ነው፡፡ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆኗን በመገንዘብ ለጋራ ጥቅም በአንድነት መሥራት እየተቻለ፣ መሰሪ ድርጊት ውስጥ መገኘት የታሪክና የትውልድ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ለነፃነት፣ ለፍትሕና ለእኩልነት ታግለናል እየተባለ አምባገነንነትን መልሶ የሚያቋቁም ድርጊት ውስጥ መገኘት ያሳፍራል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አሳፋሪና ከንቱ ድርጊት ውስጥ በፍጥነት መውጣት የግድ ይላል፡፡ አዲስ አበባን የጽንፈኝነት ሒሳብ ማወራረጃ ማድረግ ተገቢ አይደለምና!

lørdag 30. mars 2019

Lema Megerssa: ለማ መገርሳ 👉ስለ ከተማ ዲሞግራፊ 👉 ስለ ተቀነባበረ የስም ማጥፋት ዘመቻ 👉ስለ ኢትዮጵያዊነት 👉ስለ ኦሮሞና አማራ ህዝብ

የኦሮሚያ ክልል ዋና አስተዳዳሪ ለማ መገርሳ  
👉ስለ ከተማ ዲሞግራፊ
👉 ስለ ተቀነባበረ የስም ማጥፋት ዘመቻ
👉ስለ ኢትዮጵያዊነት 
👉ስለ ኦሮሞ እና የአማራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት  

👉ስለ ስለ ኦዲፒ-አዴፓ ግንኙነት

onsdag 13. mars 2019

አርበኞች ግንቦት 7 በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ አጠቃላይ ጉዳዮችን በተመለከተ ያወጣው አስቸኳይ መግለጫ

አርበኞች ግንቦት 7 በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ አጠቃላይ ጉዳዮችን በተመለከተ ያወጣው አስቸኳይ መግለጫ
ለዘላቂው የሚበጀንን ለዘብተኛውን መንገድ ትተን ዋልታ ለረገጡ አጥፊ ጽንፈኞች አገራችንን እንዳናስረክብ እንጠንቀቅ !

Image may contain: text

Image may contain: text

Image may contain: text

Image may contain: text
Image may contain: text

søndag 10. mars 2019

ዛሬ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ ነች ሲባል ሁሉም ጥያቄ በአንድ ይመለሳል ማለት አለመሆኑን ለመገንዘብ የሚያቅተን ከሆነ ነገን የተሻለ ነገር ማግኘት አንችልም፡፡

ሰላም ለሁሉም ፍላጎታችን መሳካት መሠረት ነው፡፡ ያለ ሰላም ዕቅዶቻችንንም አገራዊ ራዕያችንንም ከግብ ለማድረስ አንችልም፡፡ ሰላም ማጣት የሚያስከፍለው ዋጋ እንደዘበት አይታይም፡፡ ሕይወትና ንብረትን በማሳጣት ብቻ አይወሰንም፡፡ ሰላም ያጣ ሕዝብና አገር ማንነቱንና ክብሩን ያጣል፡፡ የውርደት ማቅ የለበሰ፣ ለተመጽዋችነትና ለእንግልት የተዳረገ እንደሚሆን የእኛው የኋላ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ 
ለሰላም ሳንካ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመነጋገርና በመደማመጥ መፍትሔ ማግኘት ሲቻል በበሬ ወለደ ወፈ ሰማይ ወሬዎች ሳቢያ ኢትዮጵያ እየተፈተነች ነው፡፡ እንኳንና ለግጭት ለጭቅጭቅ በማያበቁ አጀንዳዎች አንዱ ሌላው ላይ ጦር እንዲያነሳ የሚደረግበት ነውረኛ ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደምናየው የግጭቶች ምንጭ ተብለው የሚጠቀሱ ጉዳዮች አንገታችንን ያስደፋሉ፡፡ እንደ ሕዝብ፣ እንደ አገር እንዲህ ያለውን ክፋትና ነውር ከየት ተማርነው የሚያሰኙ ጸያፍ ድርጊቶች በጓዳችን እያየን ነው፡፡ ነገን የማያስመኙ፣ ተስፋን የሚያሳጡ ክፋቶች የዕለት ዜና እወጃ ሆነዋል፡፡ 
ነገሩን ጠለቅ ብለን ስናየው አንዱ በሌላው ወገኑ ላይ እንዲነሳበት ጥቂት ክፉ ጠንሳሾች የሚያራግቡት ወሬ ለዚህች አገር አደጋ እየሆነ ነው፡፡ ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› የሚለው የአበው አባባል እኛው ላይ የተተረተ እስኪመስል ድረስ በወሬ የሚነዳው፣ ማን አለ፣ ለምን አለ፣ እንዴት ተባለ፣ በምን ተፈልጎ ተባለ ወዘተ. የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በማነሳትና በመመርመር ምላሽ ከማግኘት ይልቅ ነሲበኞች ዋጋ ከፍለው ሌላውንም እያስከፈሉ ነው፡፡ 
መልካም አጋጣሚዎችን በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ እኔ ብቻ ከሚል እሳቤ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› እንዳለችው እንስሳ በየቦታው በተቧድኖ የሚደረጉ ግርግሮች ሰላምን በማወክ ለውድቅት እያንደረዱን ነው፡፡ ጨዋነትን በመቃረን የራስ ፍላጎትን ለመጫንና ለማስተግበር ማሴር እየተበራከተ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ችሎና ተጋግዞ፣ ያለችውን ተቃምሶ ይኖር የነበረውን የኅብረተሰብ ክፍል፣ ያለፍላጎቱ በመጎትጎትና በማስገደድ ጭምር የሚፈጸም ጥቃት እየባሰበት ሲመጣ እያየንም እየሰማንም ነው፡፡ አንዳንዴም በጋራ መኖር ጥቅማችንን ይነካናል የሚሉና አሻግሮ ነገን የመመልከት አቅም ያነሳቸው ጥቂት ግለሰቦች በማንነት ስም የሚለኩሱት የጥፋት ክብሪት መልሶ ራሳቸውን እንደሚፈጃቸው አያውቁም፡፡ ወይም ደግሞ አውቀውም አጥፍቼ ልጥፋ ያሉ ይመስላሉ፡፡ 
በታሪኳ የተፈናቀሉትን የምታስጠልለው፣ የተሰደዱትን የምታስጠጋው ኢትዮጵያ የዓለም ቁንጮ ተፈናቃዎች ምንጭ ሆና መገኘቷ እንደ ሕዝብ ለእኛ ከውርደት በላይ የሕልውናችን ማክተም ምልክት እየቀረበ የመምጣቱ ፍንጭ እንዳይሆን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ 
በግጭት ያተረፉ ይኖራሉ፡፡ የግጭት ነጋዴዎች ግን ለልጆቻችን ነገን ለሚያስናፍቁን እንቦቅቅላዎቻችን፣ ለወጣቶችና ጎምሶቻችን፣ ለቅርሶቻችንና ለመከበሪያ ማንነታችን ቦታ የሌላቸው በሰው ቁስል እንጨት የሚሰዱ፣ በሰው ሲቃ የሚንደላቀቁ የደም ከበርቴዎች እንደሆኑ ብንገነዘብ የሚያጣላን ችግር ምንኛ ኢምንት እንደሆነ በተረዳን ነበር፡፡ 
ተወደደም ተጠላ በለውጥ መንገድ ላይ በኩራት ለማራመድ የኢትዮጵያችን ሰላሟ መጠበቁ ግድ ነው፡፡ ጥያቄ አለኝ፣ ችግር ደርሶብኛል ተጎድቻለሁ የሚለው አካል ሁሉ ለሚያነሳው ጉዳይ ምላሽ መስጠት የሚጠበቅበት አካል ኃላፊነቱን በሐቅና በአግባቡ በመመለስ ከግርግርና ካለመተማመን የፀዳ ማኅበረሰብ በመፍጠር ችግሮችን የመፍታት አቅም ማዳበር አለበት፡፡ ለዚህ መተባበርና መነሳት የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡ 
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዳየነው የአገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት አባቶች አባገዳዎች ያበረከቱዋቸው አስተዋጽኦ እንደ ምሳሌ የሚወሰድና ሽማግሌ አያሳጣን ብለን እስከማወደስ የደረስንባቸውን የመረጋጋት ሥራ ተሠርተዋል፡፡
ነገር ግን ካለው ችግር አንፃር አሁንም በየባህሉና በየሃይማኖቱ አንቱ የተባሉ ሽማግሌዎች ተግባር የተገኘው መረጋጋት በአግባቡ መጠቀም ካልቻልንና በሰበብ አስባቡ ለግጭትና ለልዩነት በር የሚከፍቱ አጀንዳዎችን ይዞ በመምጣት አንፃራዊን ሰላም መልሶ የሚበርዝ ከሆነ የሽምግልና ትርጉሙ አልገባንም ማለት ነው፡፡ ደግሞም  እዚህም እዚያ ለሚከሰቱ ግጭቶች ሁሉ ሽማግሌዎችን እያፈላለጉ መዝለቅ አይቻልም፡፡ ዜጎች ራሳቸውን መግራት፣ እንዴት ተባብሮ መኖር እንደሚገባን በማሰብ ካልተራመድን አገርን በጋራ ለማራመድ ይቸግራል፡፡  
ስለሰላም የሚያስተምር አባት እንዴት እናጣለን፡፡ የሰላምን አስፈላጊነት ለመረዳት ከእልቂታችን መማር አይጠበቅብንም፡፡ እንደሞኝ ከራሳችን ሳይሆን ከሌሎች ለመማር የሚያበቁ በርካታ እልቂቶችን በዚያችን አይተናል፡፡ እያየንም ነው፡፡ ስለዚም የሰላም አስተማሪዎች ሊበራከቱልን ይገባል፡፡ በልጆቻችን ዘንድ ስለፍቅርና አንድነት፣ መልካምነትና መተሳሰብን በማስረጽ የነገ ሕይወታቸው እንዲያበራ በማድረግ በኩል ወላጆች፣ ጎረቤትና ሰፈር አድባሩ አለሁ ይመለከተኛል ሊል ይገባዋል፡፡
ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት ነው የሚባለው አውቀንም ሆነ ሳናውቅ በፈጠርነው ግጭት በሚፈሰው ደም በመውደድ የግልና የአገር ሀብት እንዳይባክን ማድረጉ ብቻ አይደለም፡፡ ሰላም ከሌለ ነግዶ ማትረፍ የለም፡፡ እያንዳንዷ ግጭት ኢኮኖሚው ላይ የሚማረረው ተፅዕኖ ሁሉንም ይጎዳል፡፡ ጉዳቱን ለማካካስ ደግሞ የበለጠ ያደክማል፡፡ ጠባሳውንም መሻር ለየቅል ይችላል፡፡
ስለዚህ በሰበብ በአስባቡ እየተነሱ ሰላምን የሚያናጉ ተግባሮችን መፈጸም የማይሽር ጠባሳ ከህሊና የማይወጣ ፀፀትም ያስከትላል፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ ነች ሲባል ሁሉም ጥያቄ በአንድ ይመለሳል ማለት አለመሆኑን ለመገንዘብ የሚያቅተን ከሆነ ነገር የተሻለ ነገር ማግኘት አንችልም፡፡ ሁሉም ተነስቶ አዋቂና ፈራጅ ላለመሆን የሚሻ ከሆነም ለውጥ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡
በለውጡ የተገኘውን መልካም ጅምር ለማስቀጠል ከተፈለገ ሰላም ወሳኝ እንደመሆኑ ሁሉ ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም እንዳይችል እንቅፋት መሆን ነገን ማበላሸት ነው፡፡ 
ነገሮችን ረጋ ብሎ ማመዛዘን የሚኖርብን ጊዜ ላይ ነን፡፡ በየፌስቡኩ የሚዥጎደጎደውን ክፉ ክፉ ነገር እየለቀሙ እሱንም እያራገቡ ነገር ማቀጣጠሉ የሚመረጥ ከሆነ ይህችን አገር እያበጀናት አይደለም፡፡ ዛሬ ለውጡን የሚመሩ አካላት የእስካሁን ጉዞ ብዙ ተስፋ እየሰጠ የመሆኑን ያህል ይኼንን ተስፋ ለማጉበጥ የሚደረጉ ጥረቶች የተሻለ ነገር እንደሚያመጡ እየታወቀ ጥቂቶች የሚያራምዱት አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ቆም ተብሎ ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ ሰላም እያሳጡ ሰላም ማምጣት እንዳልተቻለ አድርጎ ማንፀባረቅም በጎ አይደለም፡፡ 
በተለይ አግባብም ይሁን አግባብ ስለመሆኑ የማይታመንባቸው ጥያቄዎችን የሚያቀርቡ አካላት ፈራጅም ሆነው መታየታቸው ነገር ብዙ የሚያነጋግር ቢሆንም ሁሉም እንደ ዜጋ ባለበት ኃላፊነት አቋሙን ያንፀባርቅ እንጂ እኔ ብቻ አይሆንም፡፡
በአጠቃላይ የዚህች አገር የሰላም መጓደል ዕድሜ በተራዘመ ቁጥር ለሥርዓት አልበኝነትም በር እየከፈተ ስለሚሄድ ብዙ ነገር ሊያሳየን ይችላል፡፡ ስለዚህ አሁንም የሕግ ማስከበር ሥራ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ዛሬ ዝም ብለን የለቀቅነው ነገር ለሕግ ተገዥ የሆነ ኅብረተሰብ በእኩልነት የሚያምን ትውልድ ሊኖረን ይገባል፡፡
10 March 2019