mandag 1. april 2019

የአዲስ አበባ ዱካ


‹‹እንጦጦ ላይ ሆኜ አዲስን ሳያት
ባለፈርጥ ኮከብ መስላ አገኘኋት፡፡››
የዚህ መንቶ ግጥም ደራሲ በእምነት ገብረ አምላክ ናቸው፡፡ ሐያሲው እንዳለው ደራሲው የአዲስ አበባ፣ የሚያውቃት አዲስ አበባ ውበት በድንገት ያነቃው ያነሆለለው ባለቅኔ ነው፡፡
የሥነ ግጥም መምህሩ፣ የሥነ ግጥም ፈካሪው ነፍስ ኄር ብርሃኑ ገበየሁ እንደተረጎመውም ‹‹የገጣሚው አድናቆት የመነጨው ከምሽት ትዕይንት ነው ማለት ይቻላል፤ ለምን ቢሉ አንድም ለአድናቆቱ ማንጸሪያ፣ ለአድናቆቱ መያዣ የመረጠው ምስል ባለፈርጥ ኮከብ ነውና፤ አንድም ኮከብ በምናባችን የሚከሰተው የብርሃን ምስል ነውና፡፡ አገላለጹ ውብ ነው፤ ምስሉም የተባና ሳይሆን ለተደራሲውም አዲስ ውበት ትሆናለች፡፡››
ገጣሚው በአጭሩ ‹‹አዲስ›› ያላት፣ ሌሎችም ድምፃቸውን ረገጥ አድርገው ‹‹አዲሳባ›› የሚሏት አዲስ አበባ ከተመሠረተች 132 ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡
በ19ኛው ምዕት ዓመት መገባደጃ ላይ የተቆረቆረችው አዲስ አበባ የፖለቲካ፣ የሕግና የንግድ ማዕከል ሆና የዘለቀችው፣ ለአፍሪካ መዲናነት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ልዩ ተቋማት መናኸሪያነት በመብቃት ነው፡፡ ይልቁንም አዲስ አበባ በውስጧ ያላቀፈቻቸው የኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች ተናጋሪ ብሔረሰቦች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ የየብሔረሰቡ ባህላዊ መገለጫ እስከሆኑት ምግባ ምግብ ድረስ፡፡
አንድ የመዲዪቱ የሚሌኒየሙ ድርሳን እንደሚያመለክተው፣ የመዲናዪቱን ሁል አቀፍ ገጽታ/ሞዛይክነት ያስተዋሉ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ማዕከል ብቻ ሳትሆን የባህልና የቋንቋ ሙዚየም ነች፡፡
በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ምሥረታ እውን ከሆነበት በተለይ ከሁለት ሺሕ ዓመት ወዲህ ጎልተው ከሚታወቁት መዲናዎች አክሱም ከላሊበላና ጎንደር ከተሞች በመቀጠል የምትወሳው አዲስ አበባ ናት፡፡
ከተማዋ በተመሠረተች በሃምሳኛ ዓመቷ በፋሺስት ጣሊያን አገዛዝ ለአምስት ዓመታት ከመተዳደሯ በስተቀር ለ127 ዓመታት በአገሬው አስተዳደር ሥር የተለያዩ አደረጃጀቶችን አሳልፋለች፡፡
የአዲስ አበባ ዱካ

ዘመናዊ የከተማ አስተዳደር ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት›› የተመሠረተው በ1909 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ሲሆን አስቀድሞ መጠሪያው የነበረው የከተማው ማኅበር ቤት (Municipality) ነው፡፡ ማዘጋጃ ቤት የሚለውን ስያሜ ያገኘችው በ1920 ዓ.ም. መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በ1928 ዓ.ም. ሚያዝያ 27 በኢትዮጵያና ጣሊያን ሁለተኛ ጦርነት ፋሺስቶች አዲስ አበባ ከተማን ሲቆጣጠሩና ለአምስት ዓመታት ሲቆዩ የራሳቸውን አስተዳደር መሥርተው ነበር፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ጣሊያን ግዛትን መሥርተው ኤርትራና ሶማሊያን (የሞቃዲሾ) ያካተተ ስድስት ግዛቶች ሲመሠርቱ፣ አንደኛውና ማዕከላዊው ግዛት በአዲስ አበባ ስም የተቋቋመ ነበር፡፡ 
ፋሺስት ጣሊያን ከተወገደ በኋላ በግማሽ ምዕት ዓመት ውስጥ በተለያዩ አስተዳደራዊ መዋቅሮችና አስተዳደሮች ከተማዋ አልፋለች፡፡ ከዘውዳዊው ሥርዓት የጠቅላይ ግዛት አከፋፈል በኋላ በዘመነ ደርግ ስያሜው በክፍለ ሀገር ሲተካ ከ14ቱ ክፍላተ ሀገር አዲስ አበባን እንደ 15ኛ ትታሰብ እንደነበር ይወሳል፡፡
በ1980 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ሲመሠረት አከላለሉ በ25 አስተዳደር አካባቢና በ5 ራስ ገዞች የነበረ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ራሷን የቻለች የአስተዳደር አካባቢ ሆናለች፡፡ መልክዓ ምድራዊ ገጽታዋም ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ እንደ ጫንጮ፣ አቃቂ፣ ሆለታና ሌሎች የአዲስ አበባ አካባቢ ገጠር አውራጃዎች ተብለው እንደነበረ ይታወቃል፡፡
ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ሲመጣና የሽግግር መንግሥት በ1984 ዓ.ም. ሲመሠረት አዲስ አበባ ‹‹ክልል 14›› በሚል የራሷ አስተዳደር የነበራት መዲና ስትሆን፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) በ1988 ዓ.ም. ዕውን ሲሆን ክልልነቷ ቀርቶ የፌዴራል መዲና ሆናለች፡፡
ቅድመ አዲስ አበባ
አዲስ አበባ ከተማ በ132 ዓመታት ውስጥ ካስተዳደሯት ሠላሳ ከንቲባዎች ሃያ ሁለተኛው ከንቲባ ዘውዴ ተክሉ (ኢንጂነር) ከዓመታት በፊት ከሪፖርተር መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ስለ ከተማዪቱ ጥንተ ታሪክ ከተለያ መነሻዎች በመነሳት እንዲህ ተርከውታል፡፡
‹‹አዲስ አበባ እንዴት ነው የነበረችው? ማን ነው የቆረቆራት? የሚለው ነገር ሁለት መነሻዎች አሉት፡፡ በታሪክ ውስጥ የመጀመርያው መነሻ 14ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን የአፄ ዳዊት ሦስተኛ ከተማ ነበረች ነው የሚባለው፡፡ ነገር ግን እንደገና በታሪክ ወደኋላ ሲኬድ ማለትም በአራተኛው ክፍለ ዘመን የአክሱም ነገሥታት መጥተው ነበር፡፡ በአራተኛውና በአምስተኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት አብርሃና አጽብሃ መቀመጫቸውን እዚህ አድርገው ነበር የሚል ታሪክ አለ፡፡ በዚያን ጊዜ የቀረው ማስታወሻ ለአዲስ አበባ ከተማ የየካው ዋሻ ሚካኤል ነው፡፡ አብርሃና አጽብሃ የመሠረቱት ዋሻ ነው፡፡ ዋሻው በመቆየቱ የተነሳ ስላረጀ ነው በአሁኑ ጊዜ ያለው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን መሠረቱ የተሠራው፡፡ ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ ዙሪያ ሲታይ ለረጅም ጊዜ በኤረር ተራራ አካባቢ በርካታ ነገሥታት ነግሠዋል፡፡ ከተማቸውም አድርገዋታል፡፡ ስለሆነም ኤረርና በዚሁ አካባቢ በርካታ የአክሱም ነገሥታትን ጨምሮ 30 የሚሆኑ የሰሎሞናዊ ነገሥታት ነግሠዋል፡፡ 
‹‹እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ታሪክ ከነገሥታት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በመሆኑም የ237 ነገሥታት ሒደት አንድ ጊዜ ከአክሱም ወደ ላሊበላ ሸዋ፣ ከሸዋ ደግሞ ወደ ጎንደር እንደገና ደግሞ ከጎንደር ወደ ሸዋ ነው የመጣው፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን እንደገና ኤረር የአፄ ልብነ ድንግል ከተማ ነበር፡፡ ከኢማም አሕመድ (ግራኝ) በኋላ ደግሞ ወደ ሰሜን ሲያፈገፍጉ በመሀሉ ረጅም ጊዜ ያልፋል፡፡ ከዚህ በኋላ ማዕከላዊ መንግሥት ሲረጋጋ አዲስ አበባ እንደገና በአፄ ምኒልክ ዘመን ዋና ከተማ ሆነች፡፡ 
‹‹አፄ ምኒልክ ከተማቸውን ሌላ ዘንድ ለመቆርቆር ሲያፈላልጉና ጥረት ሲያደርጉ በሰሜን ሸዋ የምትገኘውን ‹‹ሊቼን› ከተማ አድርገዋት ነበር፡፡ በኋላ ግን የአያቶቼን ከተሞች ባገኝ በሚል ፍለጋ ላይ ስለነበሩ ፋሪ ላይ ከተማ ለማድረግ ሞክረው ነበር፡፡ መጨረሻ ግን ሱሉልታ አካባቢ እንዳሉ ‹እንጦጦ ላይ የአፄ ዳዊት የጥንቱ ከተማ መሠረቱ ተገኘ› የሚል መልዕክት ተላከባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ አስቆፍረው ሲያዩት እውነትም የከተማ ቅሪት ነበር፡፡ 
‹‹አዲስ አበባ የእንጦጦ ተከታይ ነች፡፡ ይህም የሆነው በመሬቱ ምቹነት ምክንያት ነው፡፡ አዲስ አበባ ልዩ ልዩ ስሞች ያላቸው በርካታ አካባቢዎችም ነበሯት፡፡ እነሱም ኮልፌ፣ ጉለሌ፣ ፊንፊኔ፣ ወዘተ. የሚባሉ ናቸው፡፡ ፊንፊኔ የሚባለውም ፍል ውኃ አካባቢ ነው፡፡ የሚመነጨው ፍል ውኃው ወደ ላይ ‹‹ፊን›› የሚል ስለሆነ ይህንኑ ተመሥርቶ የተሰጠው ስም ነው፡፡ አዲስ አበባ አጠቃላይ ስሟ ግን ‹‹ሸገር›› በሚል ነበር የሚጠራው፡፡ ይህንንም በልጅነቴ በወሬ ሲነገርና በኦሮሚኛ ሲዘፈን እሰማ ነበር፡፡ ሁለት መሠረቶች አሉ፡፡ በ1876 አዲስ አበባ ተመሠረተች የሚል መጽሐፍ አለ፡፡ ነገር ግን ትክክሉ በ1879 ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ‹የመጀመርያው ቤት በእቴጌ ጣይቱ ተሠራ፡፡ ከተማዋንም አዲስ አበባ አሏት› የሚል መጽሐፍ አለ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው እንግዲህ የአሁኑ ከተማነቷ ዋና ታሪክ ያለው፡፡ 
አቶ አማረ ሽፈራው ለአዲስ አበባ ዘመናዊት በር ከፋቾች በሚል ርዕስ ባዘጋጁት መጣጥፍ ‹‹አዲስ አበባ መቼ? የት? እንዴት? ለምን ተቆረቆረች?›› የሚለውን ጥያቄ ‹‹የአፄ ምኒልክ ግቢ ጥናታዊ ዘገባ›› በሚል ርዕስ በባህል ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ መምሪያ በነሐሴ 1976 ዓ.ም. የተዘጋጀውን ጥናታዊ ሰነድ በመጥቀስ የሚመልስ ዳሰሳ አድርገዋል፡፡ 
ሰነዱ እንደሚያስረዳው፤ በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን አፄ ምኒልክ የሸዋ ንጉሥ በነበሩበት ወቅት ቀደም ሲል በኦሮሞ ብሔረሰብ ንቅናቄና ቀጥሎም በኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም (ግራኝ) ሳቢያ የአገሪቱ መዲና ከሸዋ ወደ ጎንደር በተሻገረበት ዘመናት ከማዕከላዊ መንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሆኖ የቆየውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍልና አስተዳደር ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ወታደራዊ ኃይላቸውን ለማጠናከር የሚችሉበት አመች ዋና ከተማ በመሀል ሸዋ ለመመሥረት ያስባሉ፡፡ 
‹‹በ1877 ምኒልክ ከፍል ውኃ በስተሰሜን ከሚገኘው የእንጦጦ ተራራ ላይ ከነሠራዊታቸው ሠፈሩ›› ይልና ሰነዱ ይህም ሥፍራ ቀደም ሲል የአፄ ልብነ ድንግል መቀመጫ እንደነበር ዝዋይ ሐይቅ በሚገኘው ደሴት ብራና ላይ የተጻፈ ‹‹ትንቢት›› መገኘቱንና ምኒልክም ይህንን መሠረት በማድረግ መዲናቸውን ከወጨጫ ወደ እንጦጦ ማዛወር መሻታቸውን ያስረዳል፡፡ ከዚህ በኋላ በንጉሥ ዳዊት 1381-1410 ዘመነ መንግሥት የተሠራ ነው ተብሎ የሚታመን የጥንት ከተማ ፍርስራሽ ከእንጦጦ 15 ኪሎ ሜትር በስተሰሜን ምሥራቅ ሱሉልታ ከተባለው ሥፍራ መገኘቱንም ሰነዱ ጠቅሶ ምኒልክም ቦታውን ከጎበኙ በኋላ ‹‹እኛም ይህንን መስለን መገንባት አለብን›› በማለት በተናገሩት መሠረት እንጦጦ በዋና ከተማነት መቆርቆሯን ያስረዳል፡፡ 
‹‹በሌላ በኩል ደግሞ በጊዜው በነበረው የመከላከል ስልት እንጦጦ የአካባቢው ገዥ መሬት በመሆኑ ሌላውን ግዛት ለመቆጣጠር በጣም አመች እንደነበር ሰነዱ አልሰወረም፡፡ ዳሩ ግን እንጦጦ በተቆረቆረች በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በአካባቢው የማገዶና የውኃ ችግር ከመፈጠሩም በላይ የአየር ጠባዩም ነፋሻማና በጣም ቀዝቃዛ፣ እያደገ ለሚሄድ ከተማ ደግሞ አመችነት የሌለው በመሆኑ፣ ከዚህ የተሻለ ሌላ ቦታ ላይ አዲስ ከተማ መመሥረት ማስፈለጉን ሰነዱ ይገልጻል፡፡ 
‹‹የእንጦጦ ለከተማ አመች አለመሆን ከግርጌዋ ወደሚገኘው ለምለም ረባዳማ ሥፍራ ለተደረገው መንቀሳቀስ ምክንያት ሆነ›› የሚለው ጥናታዊው ሰነድ፣ ምኒልክና ጣይቱም በፍልውኃ ጠበል በመማረክ በ1876 ዓ.ም. ከክረምት ወራት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ከነአጃቢዎቻቸው ከእንጦጦ ወደ ፍልውኃ በመውረድ በድንኳን መቀመጣቸውን ጠቅሷል፡፡ 
ከዚህ በኋላ ጣይቱ በአካባቢው የተፈጥሮ ውበት በመማረክ ምኒልክን ቤት የሚሠሩበት መሬት እንዲሰጧቸው ጠየቁ፡፡ ምኒልክም ፈቀዱላቸው፡፡ ፍል ውኃንም እንደጠበልና እንደመዝናኛ በመጠቀም ብዙውን ጊዜ የአካባቢው ሰዎች እየመጡ እንደሚያርፉበት አስረድቷል፡፡ 
በተለይም ምኒልክ በተለያየ ወቅት ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በሚሄዱበት ጊዜ በፍል ውኃ (ፊንፊኔ) አካባቢ ለማረፋቸው የተለያዩ ማስረጃዎች መኖራቸውን አመልክቷል፡፡ 
በሌላ በኩል ደግሞ አፄ ምኒልክ ጥቅምት 4 ቀን 1879 ዓ.ም. ሠራዊታቸውን በፍል ውኃ ሜዳ ላይ አሰባስበው ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ሲሄዱ፣ እቴጌይቱ በበኩላቸው ከአንዳንድ የምኒልክ መኳንንት ተፅዕኖ ነፃ ለመሆን ‹‹ጠበል እጠመቃለሁ›› በሚል ሰበብ ከቤተ መንግሥቱ ውጭ በፍል ውኃ አካባቢ መቆየቱን በመምረጣቸው መኳንንቱ ለእቴጌይቱ በሥፍራው አንድ እልፍኝና ማዕድ ቤት እንዳሠሩላቸው ይኸው የባህል ሚኒስቴር ጥናታዊ ሰነድ ይተርካል፡፡ 
እቴጌ ጣይቱ በ2ኛ ደረጃ ከእንጦጦ አካባቢ ነዋሪዎችና ከደጃዝማች ወልደ ገብርኤል አባ ሰይጣን አፈንግጦ የተመለሰው የቁጥር ደሞዝተኛ ጦር አደጋ እንዳያስከትል በመሥጋት ምኒልክ ከሐረር እስከተመለሱ ድረስ በጊዜያዊነት በፊንፊኔ በተሠራላቸው እልፍኝና ማዕድ ቤት መቆየታቸውንም ሰነዱ ያወሳል፡፡ 
‹‹በመጨረሻ በንጉሡ ፈቃድና ትዕዛዝ ፊንፊኔ በዋና ከተማነት እንድትቆረቆር ተወሰነ፡፡ የንጉሡም ግቢ በአካባቢው ካለው ከ‹‹ቱሉ ፊንፊኔ›› ኮረብታ በአንድ ጋሻ (400 ሺሕ ካሬ ሜትር) መሬት ላይ ተሠራ፡፡ ዙሪያውንም ብዙ ቤቶች የምኒልክን ቤተ መንግሥት እየከበቡ መሥራት ተጀመረ፡፡ ፊንፊኔም ‹‹አዲስ አበባ›› በሚል ስያሜ የኢትዮጵያ መዲና ለመሆን በቃች፡፡
ከ1983 ዓ.ም. በኋላ በሽግግር መንግሥት ዘመን ክልልነትን፣ በኢፌዴሪ ውስጥፌዴራላዊ ግዛት የሆነችው አዲስ አበባ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ራሷን በራሷየማስተዳደር ሥልጣኗ የሚተገብረበት ሕግ የወጣላት 1989 .ሲሆን፣በሕገ መንግሥቱም በአዲስ አበባ ቻርተርም መሠረት የከተማዋ ስምና ስያሜአዲስ አበባ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የአማርኛ ሥነ ግጥም መምህር አልፎም በመሔስ ይታወቅ የነበረው አቶ ብርሃኑ ገበየሁ እንደጻፈው፣ በአማርኛ ሥነ ግጥም የአዲስ አበባ ምስል ተደጋግሞና ተዘውትሮ የሚገኘው በትዝታና ናፍቆት ግጥሞች ውስጥ ነው፡፡ የሰው ልጅ ገነትም ሆኖ የትውልድ ቀየውን፣ በተራዛሚውም አገሩንና ወንዙን አይረሳም፤ የአማርኛ ገጣምያን ባሕር ማዶ ለትምህርት ወይ ለሥራ በስደት ሲኖሩ፤ ቃሉ ይለያይ እንጂ የዝማሬያቸው ቃና የቅኔያቸው መንፈስ፤ ‹‹ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
   አገርም እንደሰው ይናፍቃል ወይ›› የሚል ነው