onsdag 26. februar 2014

የአዲስአበባ የ24 ሰዓታት የቴሌቭዥን ስርጭት እቅድ ተግባራዊ መሆን አልቻለም


የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የመገናና ብዙሃን ኤጀንሲ የመረጃ ውጤቶችን ለሕዝብ ተደራሽ ያደርግልኛል በሚል ከፍተኛ በጀት በመመደብ ባለፉት ዓመታት በአዲስአበባ ማዘጋጃ ቤት ሕንጻ ውስጥ ዘመናዊ ስቱዲዮና መሳሪዎች ግንባታና ግዥ ቢያከናውንም የ24 ሰዓታት ቴሌቪዥን አገልግሎት ዕቅዱን በአቅም ማነስ ምክንያት ማሳካት ሳይችል ቀርቷል፡፡
የኦሮሚያ፣ የአማራ እንዲሁም የሶማሌ ክልሎች በዓረብ ሳተላይት ላይ ጭምር የክልሎቻቸውን ዜናዎችና መረጃዎች በቴሌቪዥን እያሰራጩ ሲሆን የአዲስአበባ አስተዳደርም በተመሳሳይ መንገድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ስርጭቱን ከ6፡30 ሰዓት ወደ 24 ሰዓታት ፣ራዲዮ ፕሮግራሙን ስርጭት ከ18 ሰኣታት ወደ 24 ሰዓታት ለማሳደግ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥረት ሲያደረግ መቆየቱን የአስተዳደሩ ምንጮች አስታውሰዋል፡፡
የመሳሪያዎች ግዥና ተከላ፣ የቢሮ ዝግጅት፣ የሰው ሃይል ቅጥር ቢጠናቀቅም በታህሳስ ወር በ2006 ይጀመራል ቢባልም በይፋ ባልተገለጸ ምክንያት ስራው ሳይጀመር ቀርቷል፡፡
የአስተዳደሩ ምንጮች እንደሚናገሩት የቴሌቪዥንና የራዲዮ ስርጭቱን ማሳደግ ያልቻለው ኤጀንሲውን የሚመሩ ሙያው የሌላቸው ካድሬዎች አቅም ማነስ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ኤጀንሲው በያዝነው ኣመት ዕቅዱ የ2007 ዓ.ም ሃገር አቀፍ ምርጫን ዴሞክራሲዊ እና የህዝብ ተሳትፎን ለማረጋገት የሚያስችሉ የኮምኒኬሽን ስራዎች በብቃት እንዲተገበሩ ማድረግ፣ በዋና ዋና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በህዝቡና በከተማ አስተዳደሩ መካከል መግባባትና መተማመን የሚፈጥሩ የኮምኒኬሽን ስራዎችን ማከናወን ከያዛቸው ዕቅዶች ግንባር ቀደሞቹ ነበሩ፡፡
በአሁኑ ወቅት በ1991 ኣ.ም የወጣው የብሮድካስት አዋጁ የራዲዮና ቴሌቭዥን ጣቢያ በግል ማቋቋምን የፈቀደ ቢሆንም ኢህአዴግ መራሹ መንግስት “የሕዝቡ ንቃተ ሕሊናው አላደገም” በሚል አዋጁን ካለመተግበሩም በላይ ኢቲቪን የተለያዩ ፕሮግራም አልባ ቻናሎች እንዲከፍት በማድረግ እንዲሁም ክልሎች በዓመት ከሚመደብላቸው አነስተኛ በጀት ቀንሰው ለቴሌቪዥን የሳተላይት ስርጭት የኪራይ ክፍያና የማሰራጫ መሳሪያዎች ግዥና ተከላ ከፍተኛ ወጪ እንዲያወጡ እያበረታታቸው መሆኑና ክልሎችም በፉክክር ውስጥ መግባታቸው ታውቋል።
በሌላ ዜና ደግሞ  በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤት ቅጥር ግቢ የሚሰሩ የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞች በግቢው የጸጥታ ዴስክ በኩል ከፍተኛ ፍተሻ እየተደረገባቸው ነው፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የሚሰሩ የተለያዩ የዕለት ከዕለት ፖለቲካዊ ተግባራት በመኖራቸውና ከህዝቡ ልማታዊ እንቅስቃሴ ጋር የሚተሳሰሩ ቀጥተኛ መረጃዎች ሲያጋጥሙ በተደጋጋሚ ለኢሳት መረጃ በመድረሱና ህዝቡ እንዲያውቀው መደረጉን ተከትሎ ከተማ አስተዳደሩ ያልወደደው በመሆኑ የመረጃ ልልውጡን ለማስቀረት በሚያመች መልኩ በሚመስል ሁኔታ ከቁልፍ ባለስልጣናት በስተቀር፣ ወደ ግቢ የሚገቡ ሰዎች፣  የውስጥ ሰራተኛችን፣የውጭ የከተማ አስተዳድሩ ሰራተኞችን፣ ለተለያየ ጉዳይ የሚመጡ ባለጉዳዮችና ሌሎችም ሰዎች ጭምር ወደ ግቢው ሲመጡ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ መታወቂያቸው በጥንቃቄ ታይቶ መኪኖቻቸው ጭምር በሚገባ ተፈትሾ እንዲገቡ እየተደረገ ነው፡፡
የተለያዩ መረጃዎች እየወጡብን ነው የሚለውን ስጋት ለማስቀረት ተብሎ በር ላይ በፈረቃ በሚቆሙ የጥበቃ ፖሊሶች የሚሰሩ ሲሆን የፍተሻውን ምክንያት ተከትሎ በተለይ የውስጥ ሰራተኞቻቸው ጧት ለስራ ሲገቡ ብዙ ሰዓት ስለሚቆሙ በከፍተኛ ምሬት ውስጥ ናቸው፡፡
ከዚህ በፊት በግቢው ውስጥ ከሚገኘው የሰራተኞች መመግቢያ አዳራሽ ብዙ ሰራተኛች ወደ ግቢው መጥተው ምሳ ላይ ለመጠቀም ይፈቅድላቸው የነበሩት የከተማ አስተዳድሩ የውጭ ሰራተኞች የፍተሻውን ስራ ጫና ለመቀነስ ሲባል እንዳይገቡ ተደርጓል፡፡
የጥበቃ ፖሊሶች የውስጥና የውጭ ሰራተኞችን መለየት ባለመቻላቸው ና ማንም ሳይፈተሽ መግባት እንደማይችል ስለተነገራቸው የመስተዳድሩ ሰራተኞች ጧት ከቤታቸው ሲወጡ መርሳት ከሌለባቸው ዋነኛ ነገር መታወቂያ ሆኗል፡፡

በኦሮምያ የክልል ፐሬዚዳንት ለመሾም የሚደረገው ሽኩቻ ቀጥሎአል

የክልሉ ምክር ቤት ሳያቀውቀው በስራ አስፈጻሚው እውቅና ከስልጣን የተነሱትን አቶ አለማየሁ አቶምሳን ማን ይተካቸው የሚለው አጀንዳ የአቶ አባ ዱላ ገመዳንና የአቶ አለማየሁ አቶምሳን ቡድኖች እያወዛገበ ነው። አቶ አለማየሁ አቶምሳ ወደ ስልጣን እንደመጡ የአቶ አባዱላን ቡድኖች በመምታት ከስልጣን ውጭ ያደረጉዋቸው ሲሆን፣ አባ ዱላ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ተመልሰው የእርሳቸውን ሰዎች ለማሾም እየሰሩ ነው።
እስካሁን ድረስ የክልሉ ምክር ቤት ስበሰባ አለመጠራቱም ታውቋል። አንዳንዶች እንደሚናገሩት ህወሃት ለዘብተኛ የሆነ መሪ እንዲመጣ ፍላጎት በሚያሳየው ፍላጎት የሁለቱም ሰዎች ደጋፊዎች ላይሾሙ ይችላሉ ፡፡ አቶ አለማየሁ የመሰረቱት አስተዳደር በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙትን መለስተኛ ከተሞችን ለመስተዳድሩ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የ10 በ90 ፕሮጀክት እንዲደናቀፍ ማድረጋቸውን በማንሳት  እርሳቸውን የሚተካው ሰው ለዘብተኛ ሆኖ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ተግባብቶ የሚሰራ እንዲሆን እንደሚፈለግ እኝሁ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ሰዎች ይናገራሉ።
በአባ ዱላ ዙሪያ የተሰባሰቡ ሰዎች ከሙስና ጋር በተያያዘ ድርጅቱን አደጋ ውስጥ በመጣላቸው በፌደራሉ መንግስት በዙም አይደገፉም። ከሁለቱም ቡድኖች ወጣ ያለ አዲስ ሰው ለማገኘት ኦህዴድ ፈተና እንደሆነበትና ምናልባትም ሽኩቻው በዚህ ከቀጠለ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ስልጣኑን ተረክበው ሊቀጥሉ ይችላሉ የሚለውን ግምት እያጠናከረው መምጣቱን ይገልጻሉ።

ብአዴን ባህርዳር ላይ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ እንዳይሳካ ለማድረግ የቀየሰው ስትራቴጂ ሳይሳካ መቅረቱን የውስጥ ምንጮች ገልጹ

አቶ አለምነው መኮንን የአማራን ህዝብ መዝለፋቸውን ተከትሎ አንድነት ፓርቲና መኢአድ የጠሩተን ሰልፍ ለማደናቀፍና ህዝብ በሰልፉ ላይ እንዳይገኝ የተቀየሰው ስትራቴጂ ሳይሳካ መቅረቱን የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ለኢሳት ገልጸዋል።
በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የሚገኘው ብአዴን ሰላማዊ ሰልፉን ለማጨናገፍ ከተጠቀመባቸው ዘዴዎች አንዱ በአንጻራዊነት የተሻለ ተሰሚነት ያላቸውን ወደ አዲስ አበባ ከመጡት የክልሉን ተወላጅ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮችን መካከል መርጦ በመላክ ወጣቶችን እንዲያረጋጉና እንዲያሳምኑ ማድረግ ነበር። የተሻለ የፖለቲካ አፈጻጸም አላቸው የተባሉ በሲቪል ሰርቪስና በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚገኙ አመራሮች ወደ ባህርዳር ተንቀሳቅሰው ወጣቱን ለማረጋጋት ቢሞክሩም ሳይሳካ ቀርቷል።
የተለያዩ የፖሊስ ኮማንደሮችን ከአዲስ አበባ ወደ ከተማዋ በማስገባት የስነ ልቦና ጫና መፍጠር ይህ ካልተሳካም የፌደራልና የክልሉ ፖሊሶችን በማንቀሳቀስ ፍርሃት በመፍጠር ወጣቱ ወደ አደባባይ እንዳይወጣ የተቀየሰው ስትራቴጂ ውጤት አልባ ሆኗል።
በተቃውሞው ማግስት ብአዴን ነባር አመራሮችን በአስቸኳይ ወደ ባህርዳር በመጥራት ዝግ ስብሰባ እያካሄደ ነው። ንቅናቄው እስካሁን ድረስ በሰልፉ ዙሪያ ወይም በአቶ አለምነው ንግግር ላይ የአቋም መግለጫ አላወጣም።
በባህርዳር የተካሄደው ሰልፍ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩንም ዘጋቢያችን ገልጻለች። አንዳንድ የብአዴን አባላት ሳይቀሩ ህዝቡ ባሳየው ተሳትፎ ከሁሉም በላይ ስለነጻነቱ፣ ስለ ኢኮኖሚውና ፍትህ አንግቦ የተነሳው ተቃውሞ እንዳስደሰታቸው ለዘጋቢያችን ገልጸውላታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ አለምነው መኮንን የአቶ መለስ ዜናዊ ጭፍን አምላኪ ተደርገው እንደሚቆጠሩ ጓዶቻቸው ለኢሳት ተናግረዋል። አቶ አለምነው በባህርዳሩ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ብቸኛ የርእዮት አለም ሰው መለስ ዜናዊ እንደነበርና ሌላው ሁሉ ተከታይ መሆኑን መናገራቸው የአቶ መለስ ፍልስፍና አራማጅ መሆናቸውን እንደሚያሳይ ገልጸዋል። ” ቢቀዳ ቢጨለጥ አንድ የርእዮት አለም ሰው የነበረው መለስ ዜናዊ ነው” የሚሉት አቶ አለምነው፣ ሌላው ሁሉ ተከታይ” ነው በማለት የኢህአዴግን አባላት ሳይቀር ከላይ እስከታች ተከታዮች አድርገው ፈርጀዋቸዋል። ” ሱፍ ለብሶ በመሄድ” አይደለም ሲሉም በአገሪቱ ባሉ ምሁራንና በኢህአዴግ መሪዎች ላይ ሳይቀር ተሳልቀውባቸዋል።
ኢህአዴግ ከአቶ መለስ ሞት በሁዋላ አዳዲስ ሃሳቦች የሚያመነጭ የርእዮት አለም ሰው ሰው የለውም ማለት ነው ሲሉ በስብሰባው ላይ የተሳተፉ አንዳንድ የብአዴን አባላት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከ 6 ሚሊዮን የኢህአዴግ አባላት መካከል እንዴት አንድ ሰው እንኳ አዲስ ሃሳብ የማመንጨት ብቃት የሌለው ይጥፋ በማለት አባላቱ ጠይቀዋል።
አቶ አለምነው አማራውን በተመለከተ የተናገሩት አቶ መለስ በተደጋገሚ ሲጽፉትና ሲናገሩት የነበረውን ያሉት አንዳንድ አመራሮች፣ ብአዴን በአማራው ስም የተደራጀ የህወሃት ጉዳይ አስፈጻሚ ድርጅት ነው እየተባለ የሚነገረው እውነት በመሆኑ፣ ድርጅቱን ከህወሃት ፈልቅቆ ለማውጣት የውስጥ ትግል እየተካሄደ መሆኑንም አክለዋል።

tirsdag 25. februar 2014

መንግስት ኢማሞችን በመሾም በኩል ጣልቃ መግባቱን የሚያሳይ መረጃ ይፋ ተደረገ


በማህበራዊ ድረገጾች የተለቀቀው ይህ መረጃ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አዲስ አበባ ምድብ ወንጀል ችሎት የቀረበ ነው።  ወንጀል ዝርዝር በሚለው ክፍል ውስጥ ” 2ኛ ተከሳሽ መንግስት በሾመው ኢማም ቦታ ላይ በመቆም፣ ሳይፈቀድለት የነሱን ተከታዮች በማሰገድ ሰላማዊ ሙስሊም እንዳይሰገድ በማድረግና መስኪዱ በመታወቁ በወና ወንጀል አድራጊነት ተከሷል” ይላል
ምንም እንኳ መንግስት በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ እንደማይገባ ህገመንግስቱን በመጥቀስ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቢቆይም፣ ሰነዱ መንግስት የሃይማኖት መሪዎችን እስከመሾም የሚደርስ እርምጃ መውሰዱን ሰነዱ ያመለክታል።

ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ በአባይ ግድብ ግንባታ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ሪፖርተር ዘገበ


ጋዜጣው በእሁድ እትሙ እንደገለጸው ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ” በህዳሴው ግድብ ላይ 60 ከመቶውን የትራንስፖርት፣ ሎጂስቲክና አፈር የማንሳት ሥራዎችን ከሳሊኒ በተቋራጭነት በመውሰድ እየሠራ እንደሚገኝም ባለፈው አመት ኩባንያው በቀድሞው ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን የእህት ልጅ በወ/ሮ አቲኮ ስዩም አምባየ መመስረቱን ፣  በግልገል ጊቤ አንድ እና ግልገል ጊቢ ሁለት የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች ስሚንቶ እና የግንባታ እቃዎችን እንዲሁም ከፍተኛ ማሺነሪዎችን በማቅረብ መሳተፉን ዘግቦ ነበር። ይህ ኩባንያ በአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ከሳሊኒ በመቀጠል ከፍተኛውን ድርሻ መያዙን በወቅቱ ኢሳት ዘግቧል።
“ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ፣ በደረጃ አንድ ተቋራጭነቱ በአየር ማረፊያ፣ በመንገዶች፣ በሕንፃ ግንባታ፣ በነዳጅ ቁፋሮ ሥራዎችና በሌሎችም መስኮች መሰማራቱን የገለጸው ሪፖርተር፣  በእህት ኩባንያዎቹ በኩል በአበባ እርሻ፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መስኮች ሲሠራ የቆየ አገር በቀል ኩባንያ ነው፡፡ ” ብሎአል ሪፖርተር።
ወ/ሮ አቲኮ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ከአንድ አነስተኛ የኪራይ መኪና ውጭ ይህ ነው የሚባል ሃብት አልነበራቸውም። ግለሰቡዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ የናጠጡ ሀብታም ለመሆን የቻሉት በወ/ሮ አዜብ መስፍን ድጋፍ እንደሆነ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ፡
ጋዜጣው እንደዘገበው ወርኪድ ከጀርመኑ ባወር ኩባንያ ጋር በመነጋገር ከባድ ማሽነሪዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ከአባይ ግድብ እስከ ነዳጅ ፍለጋ ስራዎች ያሉ ቁፋሮዎችን ያካሂዳል።

የስዊስ አቃቢ ህግ የረዳት ሃይለመድህን አበራን ሰብአዊ መብቶች ያከብራል ሲሉ ቃል አቀባዩዋ ተናገሩ


የሰዊስ አቃቢ ህግ ቃል አቀባይ ሚስ ያኔት ባልመር በረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ ዙሪያ ከኢሳት ለቀረበላቸው ጥያቄ የምርመራ ሂደቱ ያልተጠናቀቀ በመሆኑ ዝርዝር መረጃዎችን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ገልጸው፣ የሰብአዊ መብቱን በመጠበቅ በኩል ለተነሳው ጥያቄ ግን ስዊዘርላንድ የሰብአዊ መብቶችን በጠበቅ በኩል ታዋቂ አገር መሆኑዋን በመግለጽ የሃይለመድህንን የሰብአዊ መብቶች እንደሚያከብሩ ገልጸዋል።
ሃይለመድህን ጠበቃ ተቀጥሮለት ጉዳዩን በመከታተል ላይ ነው። የሃይለመድህንን የፍርድ ቤት ጉዳይ መከታተል ይቻል እንደሆን የተጠየቁት ቃል ሚስ በርነር፣ በአሁኑ ሰአት ስለፍርድ ቤት ሂደት ለማውራት ባይቻልም በስዊዘርላንድ አብዛኛውን ጊዜ ፍርድ ቤቶች በግልጽ ችሎት ጉዳዮችን እንደሚያዩ ተናግረዋል።
የሚቀጥለው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ቀን ይታወቅ እንደሆን ሲጠየቁም ” እዛ ደረጃ ላይ ገና አልተደረሰም” በማለት መልሰዋል። የምርምራው ሂደት መቼ እንደሚጠናቀቅ ሲጠየቁም፣ የስዊስ የፍትህ አሰራር መረጃዎችን በሚስጢር መያዝን ስለሚያዝ፣ ምንም አይነት መግለጫ መስጠት እንደማይቻል አክለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ስዊዘርላንድ ለረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ ጥገኝነት እንደትሰጥ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ የፊታችን አርብ ፌብሩዋሪ 28 በበርን እንደሚካሄድ በስዊዘርላንድ የ ዲሞክራሲ ለውጥ በኢትዮጵያ የስውዘርላንድ የድጋፍ ኮሚቴ ገልጿል።

mandag 24. februar 2014

በኒውዚላንድ የኢሳትን የኔነው ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ ተካሄደ

ባለፈዉ ቅዳሜ የካቲት 15፣ 2006 ዓም በ ኒዉዚላንድ አገር በኦክላንድ ከተማ  ተዘጋጅቶ የነበረዉ የኢሳት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።
በሂደቱ በርካታ ችግሮች ተጋርጠውበት የነበረ ቢሆንም፣ ለአገራቸዉ ነፃ መዉጣትና ኢሳትን አሁን ካለበት እጥፍ አድጎ ማየት በሚፈልጉ ቀናኢ ኢትዮጵያዉያን ጥረት የገንዘብ ማሰባሰቡ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አስተባባሪዎች ገልጸዋል።
በርካታ ኢትዮጵያን የነበረዉን መሰናክል በማለፍ በቦታዉ የተገኙ ሲሆን ከ ዌሊንግተንና ክራይሰት ቸርች የመጡ የ ኢሳት ደጋፊዎችም እንዲሁ የዝግጅቱ ተካፋይ ለመሆን በሺ ኪሎ ሜትር ተጉዘዉ ተገኝተዋል። ቤተሰብ ለመጠየቅ ከአዉስትራሊያና አሜሪካ የመጡ ኢትዮጵያዉያኖችም በዝግጅቱ ላይ ተሳትፈዋል።
በዚህ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ዝነኛዉ አርበኛ አርቲስት ሻምበል በላይነህ ከ አገራዊ እና ባሕላዊ ዘፈኖቹ ጋር በመቅረብ ዝግጅቱን በልዩ ሁኔታ አድምቆታል።
ቀደምት አባት አርበኞችን ባቀፈዉ የኢትዮጵያ ካርታ ምስል  በርካቶች በኢትዮጵያ ጀግኖች ስም ተጫርተው፣ጨረታውን አቶ አረፈ አይኔ የተባሉ ሰው አሸንፈዋል። በዚህ የኢሳት ገንዘብ ማሰባሰቢያ ምሽት ላይ የኒዉዚላንድ የኢሳት ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ ጊዜያዊ ሰብሳቢ አቶ መላኩ በገንዘብ አሰባሰቡ ላይና አዲስ በተከፈተዉ የ አዉስትራሊያ ባንክ እንዴት ገንዘቡን ማስገባት እንደሚቻልና ቋሚ አባል መሆን እንደሚገባ ዘርዝረዉ በማስረዳት ኢሳትን በቋሚነት መርዳት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን  አንዱአለም ሃይለማርያም ከኒውዚላንድ ዘግቧል።

“የባህርዳር ህዝብ አንግቦ የተነሳው በአገሪቱ እየጨመረ የመጣውን የለውጥ ጥያቄ ነው” ሲሉ ነዋሪዎች ገለጹ

የ28 አመቱ ሙላት የመሸንቲ ነዋሪ ነው፤ በተቃውሞ ሰልፉ ላይ የተገኘሁት በአገዛዙ ተማርሬ ነው ይላል። ለምን ተማረርክ በማለት ዘጋቢያችን ላቀረበችለት ጥያቄ፣ “ምን የማያስመርር ነገር አለ፣ ሁሉም ነገር እየተበላሸ እንጅ እየተሻሻለ ሲሄድ አታይም፣ ይህም አልበቃ ብሎ ይዘልፉናል” በማለት በሰልፉ ላይ የተገኘበትን ምክንያት ገልጿል።
የባህርዳር ነዋሪዎች አንድነትና መኢአድ በጋራ በጠሩት ሰልፍ ላይ በነቂስ ወጥተዋል። “ህዝብን እያዋረዱ መግዛት አይቻልም፣ብአዴን ኢህአዴግ የአማራን ህዝብ የመግዛት የሞራል ልእልና የለውም፣ ህዝብ ከእርስት ማፈናቀል ይቁም፣ ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል፣ ነጻነት የሌላት አገር ጨለማ ናት፣ ገበሬው በገዛ መሬቱ ስደተኛ አይሆንም” የሚሉና ሌሎችም መፈክሮች ተስምተዋል።
ዛሬ ታላቅ ደስታ ተስምቶኛል፣ የአመታት ህመሜ ተፈውሷል” ሲል የተናገረው የቀበሌ 7ቱ ነዋሪ ማሙሽ፣ ሰልፍ እንደሚደረግ ከሰማበት ጊዜ ጀምሮ ሲቀሰቅስ መቆየቱን ተናግሯል።
አቶ አለምነው መኮንን የአማራን ህዝብ መዝለፋቸውን ተከትሎ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የባህርዳር ነዋሪዎች በኢትዮጵያ ባንዲራ፣ አንዳንዶችም ጥንታዊት ኢትዮጵያን በሚወክሉ የጀግንነት ማጌጫዎች ተውበው በአደባባይ ተይተዋል።
ይሄ ህዝብ ማስፈራሪያዎችን ሁሉ ጥሶ፣ የቀን አበል ሳይሰጠው ለነጻነቱ በፍላጎቱ የወጣ ህዝብ ነው ያለው መኮንን፣ ገዢው ፓርቲ ይህንን ሰልፍ ለማውገዝ ሌላ ሰልፍ ሊያዘጋጅ እንደሚችል ይናገራል።
“ወጣቱ ፣ ሽማግሌው ሴቱ ወንዱ ተነስቷል” የሚለው ሌላው ነዋሪ፣ ህዝቡ ለነጻነቱ ሲጠይቅ መዋሉን ገልጿል።
“ከሰለፉ ማግስት ባህርዳር እንዴት ናት?’ በማለት ሲጠየቅም፣ ” ህዝቡ ደስ ብሎት በእየቤቱ እየተወያየ ነው” ብሎአል ። ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ በሰልፉ ላይ የታየውን ዲሲፒሊን አድንቋል።
የአቶ አለምነው መኮንን ጉዳይ የተቃውሞ ሰልፉን ለማድረግ እንደ መነሻ ሆነ እንጅ ዋናው ጥያቄ የዲሞክራሲ፣ የነጻነት እና የኢኮኖሚ መሆኑን ገልጿል። ”ኢህአዴግ እንደተናካሽ ውሻ በድንጋጤ ያገኘውን ሁሉ ለመንከስ ቢሞክርም፣ ትግሉ ግን ወደ ሁዋላ የሚቀለበስ አይመስለኝም ሲል አስተያየቱን አክሏል።

søndag 23. februar 2014

አንድነት – የባህር ዳር ሰልፍን በተመለከተ የዛሬ የካቲት 15 ዉሎ


-          የባህር ዳር፣\ ሰልፍ ተሟሙቆ ዋለ
-          የአመራር አባላትን በሆቴል ቤታቸዉ እንገድላችኋለን እየተባሉ ነው
-           ከባህር ዳር አካባቢ ያሉ እንቅስቃሴውን እየተቀላቀሉ ነው
-          10 ድርጅቶች ስብስብ የሆነው የትብብር አመራሮች መኢአድ እና አንድነት ተቀላቅለው እየቀሰቀሱ ነው
 የባህር ዳር ሰልፍ ነገ የካቲኡት 16 ቀን ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀመሮ ይደረጋል። « ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል» በሚል የተዘጋጀው ፍላየር ሰልፉ  የሰልፉ መነሻ፡- ግሽ አባይ/ ቀበሌ 12 የሚገኘው አንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ የሰልፉ የጉዞ መስመር፡- ከግሽ አባይ/ ቀበሌ 12 ተነስቶ  በድብ አንበሳ ዞሮ ወደ ክልሉ መስተዳድር ጽ/ቤት ነው።
 በባህር ዳር አጎራባች ይልማና ዴነሳ ወረዳ፣  የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢና ሁለት አመራሮች ለእሁዱ የተቃውሞ ሰልፍ በማስተባበራቸው ታሰሩ፤ ሌሎቹን አመራሮችም ለማሰር አሰሳ እያደረገ ነው፡፡
 ነገ የካቲት 16 በባህር ዳር ከተማ ብአዴንንና አመራሮቹን በመቃወም በሚደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የባህር ዳር አጎራባች አካባቢ ነዋሪዎችም ለመሳተፍ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት፣ የአንድነት ፓርቲ የይልማና ዴንሳ ወረዳ አመራሮች ህዝቡን በማስተባበርና አስፈላጊውን መረጃ ሲያደርሱ ሰንብተዋል፡፡
ህዝቡ በብአዴን ላይ እያሳየ የመጣው ቁጣ ያሳሰባቸው የአዴትና የአካባቢው ባለስልጣናትም ሁሉም የወረዳው የአንድነት አመራሮችን በሙሉ ለማሰር እርምጃ ጀምረዋል፤ በዚሁም መሰረት የወረዳው የአንድነት ሰብሳቢ አቶ ይሁኔ ዘለቀ ትላንት ማታ የታሰሩ ሲሆን፣ ዛሬ ደግሞ አቶ ጌታቸው መስፍን እና አቶ ብሩክ ትዕዛዙ ታስረዋል፡፡
 እስሩን ከምንም ያልቆጠሩት የአንድነት አመራሮችም ህዝቡን ለሰልፍ ማስተባበራቸውን ቀጥለዋል፤ የባህር ዳር ዙሪያ ወረዳዎች ነዋሪዎችም ለሰልፉ መዘጋጀታቸውን እየገለፁ ነው፡፡
 ወደ ባህር ዳር ከተማ ስንመለ፣ የአንድነት፣የመኢአድ እና የትብርር ለዲሞክራሲ አመራሮች ቀስቃሽ ወረቀት በመበተን ላይ ናቸው፤ ህዝቡን አጅቧቸው ቅስቀሳውን አድምቆታል፡፡
የአንድነት ፕሪዝዳንት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፣ የመኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ አበባው መሃሪ እንዲሁም የትብብር ለዴሞክራሲ ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ፣ እንዲሁም የአንድነት ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር ኃይሉ አርአያን ጨምሮ ወደ ስፍራው የተንቀሳቀሱ የፓርቲው የስራ አስፈፃሚ አባለት፣ በባህርዳር ጎዳናዎች ላይ የቅስቀሳ ወረቀቶችን በመበተን በዚያ ለበርካታ ቀናት ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ አባላትን እና ደጋፊዎች ጎን የቅስቀሳ ተግባራት ላት ተሰማርተዉ ነበር።
 ብሕአዴን/ኢሓዴግ ግን የነገዉን ሰልፍ ለማጨናገፍ እያደረገ ያለውን ወከባና እንግልት ግን አላቆመም። በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 11 በሚገኘው ሰን ራይዝ ሆቴል ያረፉት የአንድነት እና የመኢአድ የቅስቀሳ ቡድን አባላት እና አመራሮች በመንግስት የደህንነት አባላት ወከባ እየደረሰባቸው ሲሆን፣ መሳሪያ የታጠቁ ስድስት የመንግስት ደህንነቶች የታጠቁትን መሳሪያ በማውጣት እንገላችኋለን በማለት የቅስቀሳ ቡድኑን አባላት ለማዋከብና ልከማስፈራራት ትረት አደርገዋል።
 የሆቴሉን ሰራተኞችንም፣ አልጋ የያዙ ግለሰቦችን መታወቂያ አምጡ በማለት ግርግር ለማስነሳት ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ለፖሊስ በመደወልም «በአንድነት አባላት ተደብድበናል፤ ፎቶም ተነስተናል» በማለት ሀይል እንዲጨመርላቸው ጠይቀዋል።
 ትብብር ለዲሞክራሲ አመራሮች ከመኢአድ እና አንድነት ጋር በባህር ዳር እየቀሰቀሱ ናቸው
========================================================================
 የአሥር ድርጅቶች ስብስበ የሆነው ትብብር ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ አመራር አባላት ከመኢአድ እና አንድነት ጋር በመሆን በባህር ዳር ቅስቀሳ እያደረጉ እንደሆነ የደረሰን ዘገባ ያመልክታል።
 የትብብሩ መስራች ድርጅቶች ዉስጥ የሐዲያ ብሔር አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ፣የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ፣ የሶዶ ጎርደና ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የከምባታ ሕዝቦች ኮንግሬስ ፣ የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት፣ የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፣የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት፣ የጌዴኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ፣የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ይገኙበታል።
 የባህር ዳሩን ሰልፍ መኢአድ እና አንድነት በጋራ ከመስራታቸውም ባሻገር ፣ ሌሎች ድርጅቶችን ማሳተፋቸው ፣ በራሱ ትልቅ ዉጤት መሆኑን የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም። በተለይም ድርጅቶች በወረቀት ላይ ሳይሆን፣ በሥራ ትብብራቸውን ማሳየታቸዉ ሕዝብ በተቃዋሚዎች ላይ ያለዉን አመኔታ የበለጠ እንዲጨምር የሚያደርግ ነው።

ባህር ዳር በሰልፈኞች ተጥለቅልቃለች – ፎቶዎች ይመልከቱ

አስደናቂ ሰልፍ ነዉ በባህር ዳር የተደረገዉ። ከቃላት ምስል የበልጠ ስለሚያስረዳ ፣ የነጻነት፣ የዲሞክራሲ፣ የኢትዮጵያዊነት ድምጹኝ ያስተጋባዉን ጀግናዉ የባህር ዳር ሕዝብ ይመልከቱ !!!!

pic19
pic18
pic17
pic16
pic12
pic13
pic14
pic15
pic11
pic10
pic9
pic8
pic7
pic6
pic5
pic4
pic3
pic2
pic1
bahir_dar1
bahir6
bahir5
aeup

የአንድነት ፓርቲ በነ ዶር በየነ ከመድረክ ታገደ


pic17

የአንድነት አመራር አባላት በባህር ዳር ህዝቡን እየቀሰቀሱ ባለበት ወቅት፣ መድረክ የተሰኘው ስብስብ፣ ዛሬ ባደረገው ስብሰባ፣ የአንድነት ፓርቲን እንዳገደ ፍኖት ዘገበ። መድረክ በአሁኑ ወቅት አራት ድርጅቶ ብቻ ያሉት ሲሆን እነርሱም፣ አንድነት፣ አረና፣ በዶር መራራ ጉዲና የሚመራዉ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፣ በዶር በየነ ጴጥሮስ የሚመራዉ የኢትዮጵያ ማህበረ ዲሞክራሲ ደቡብ ህዝቦች አንድነት ፓርቲ ናቸው።
አረናዎች ጠንካራ ተቃዉሞ በማሰማታቸው እንጂ እነ ዶር መራራ እና ዶር በየነ ሙሉ ለሙሉ አንድነትን ከመድረክ ማበረር ፍላጎት እንደነበራቸው ዘገባው አክሎ ያትታል።
የዶር በየነ ሆነ የዶር መራራ ፓርቲዎች፣ እንደግፈዋለን በሚሉት ህዝብ ዘንድ በምሄድ ምንም አይነት ስብሰባዎችን ሆነ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አድርገዉ የማያውቁ ሲሆን፣ ምን ያህል የፓርቲ አባላት እንዳላቸውም አይታወቅም።
በአንጻሩ አረና ትግራይ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ በሽሬ፣ በማይጨዉ፣ በተንቤን፣ በአዲግራት፣ በሁመራ ለማድረግ የተንቀሳቀስ ሲሆን፣ የአንድነት ፓርቲ በዛሬው ቀን በሜዳ ላይ ከሕዝብ ጋር እየሰራ እንደሆን በስፋት እየትዘገበ ነዉ።
የፍኖትን ሙሉ ዘገባ እንደሚከተለው ያገኛሉ!

ፍኖት – አንድነት ለትግል በወጣበት ቀን የመድረክ አባል ፓርቲዎች አገዱት
——————————-
“አንድነትን በመግፋት መድረክን ወደ አክራሪ ብሔረተኛ ስብስብነት ለመግፋት የተደረገ ስልታዊ ውሳኔ ነው” የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ም/ፕሬዝደንት አቶ ተክሌ በቀለ
——————-
መድረክ በከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ ውጤት ያመጣ ስራ እየሰራ የሚገኘውን አንድነት ፓርቲን ማገዱ ትዝብት ላይ የሚጥል ውሳኔ ነው፡፡” የአንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ አባል ፓርቲዎች አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ማገዳቸውን ዛሬ የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ.ም በተደረገው የመድረኩ 9ኛ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ አሳውቀዋል፡፡ በጉባኤው አንድነትን ወክለው የተሳተፉት መካከል የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ም/ፕሬዝደንት እንዲሁም የመድረክ ም/ሊቀመንበርና የውጪ ግንኙነት ኃላፊ ሆኑት አቶ ተክሌ በቀለ ለፍኖተ ነጻነት እንዳስታወቁት የመድረክ አባል ፓርቲ የሆኑት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስና በፕ/ር በየነ የሚመራው የኢትዮጵያ ማህበረ ዲሞክራሲ ደቡብ ህዝቦች አንድነት ፓርቲ አንድነት ከመድረክ እንዲባረር ቢጠይቁም አረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ለዴሞክራሲ አንድነት ላልተወሰነ እንዲታገድ የሚል ሞሽን አቅርቦ በጉባኤው ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
አቶ ተክሌ በቀለ የመድረክ አባል ፓርቲዎች አንድነትን ለማገድ የወሰኑባቸው ምክንያዎች አስገራሚ መሆናቸውን ጠቅሰው “የመድረክ አባል ፓርቲዎች አንድነትን ለማገድ የወሰኑት በቅርቡ በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ አንድነት መድረክ ውስጥ ካሉ ፓርቲዎች ጋር ውህደት እንዲፈፀም መወሰኑን፣ አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮችም ውህደት እንደሚያስፈልግ በተለያዩ ሚዲያዎች መናገራቸውን፣ የአንድነት ፓርቲ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ድጋፍ ሰጪዎች በመድረክ ስም የፋይናንስ ድጋፍ እንዲደረግ ትብብር አያደርጉም በሚልና ከመድረክ ዕውቅና ውጪ መስከረም 19(ሰላማዊ ሰልፉ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ህዝባዊ ንቅናቄ የማጠቃለያ መርሀ ግብር ነው፡፡) በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂዷል፡፡” የሚሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ አክለውም አንድነትን በመግፋት መድረክን ወደ አክራሪ ብሔረተኛ ስብስብነት ለመግፋት የተደረገ ስልታዊ ውሳኔ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ አቶ ተክሌ መድረክ የራሱን ዕቅድ አውጥቶ በቁርጠኝነት የማይሰራ በመሆኑ አንድነት በተናጠልና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የተለያዩ ስራዎችን መስራቱን ጠቅሰው “በተደጋጋሚ ለመድረክ በዕቅድ የተደገፉ እንቅስቃሴዎችን በማቅረብ በጋራ እንዲሰራ ቢጠይቅም ቀና ምላሽ አግኝቶ አያውቅም፡፡ ይልቁኑም የራሱን ጥፋት በአንድነት ላይ ለማላከክ ይሞክራል ” ብለዋል፡፡
ነገ አንድነትና መኢአድ በባህር ዳር የሚያደርጉትን ሰላማዊ ሰልፍ በማስተባበር ላይ የሚገኙት የአንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው የመድረክን ውሳኔ አስመልክተው ለፍኖተ ነፃነት እንደገለፁት “ መድረክ በከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ ውጤት ያመጣ ስራ እየሰራ የሚገኘውን አንድነት ፓርቲን ማገዱ ትዝብት ላይ የሚጥል ውሳኔ ነው፡፡” ካሉ በኋላ “አንድነት የታገደው ውጤታማ ስራ ስለሰራና በሚሊዮኖች ድምፅ ንቅናቄ እና በተመሳሳይ ስራዎች የተቀዛቀዘውን የሰላማዊ ትግል በማነቃቃት ትግሉን ወደ ህዝብ ስላወረደ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ አክለውም “መድረክ ውስጥ ካሉት ፓርቲዎች የተሻለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርገው አረና ብቻ ነው፤ የዛሬው ውሳኔ አረናም በቅርቡ የአንድነት እጣ እንደሚገጥመው አመልካች ነው፡፡” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ “መድረክ እንደዚህ ያለ እገዳ ከመወሰን ይልቅ አንድነትና አረና የጠየቁትን ውህደት ተቀብሎ ፖለቲካውን በአንድ ላይ ማንቀሳቀሱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ ውጤት እንደሚያስገኝ አንድነት ያምናል፡፡ ስለዚህ መድረክ የወሰነውን ውሳኔ እንደገና አጢኖ የሀገራችንን ፖሊቲካ በውህደት አብረን እንድንመራ እንዲያደርግ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

lørdag 22. februar 2014

ሰበር ዜና!! አንድነት ለትግል በወጣበት የመድረክ አባል ፓርቲዎች አገዱት- ፍኖተ ነጻነት

አንድነትን በመግፋት መድረክን ወደ አክራሪ ብሔረተኛ ስብስብነት ለመግፋት የተደረገ ስልታዊ ውሳኔ ነው” የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ም/ፕሬዝደንት አቶ ተክሌ በቀለ
መድረክ በከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ ውጤት ያመጣ ስራ እየሰራ የሚገኘውን አንድነት ፓርቲን ማገዱ ትዝብት ላይ የሚጥል ውሳኔ ነው፡፡” የአንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ አባል ፓርቲዎች አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ማገዳቸውን ዛሬ የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ.ም በተደረገው የመድረኩ 9ኛ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ አሳውቀዋል፡፡ በጉባኤው አንድነትን ወክለው የተሳተፉት መካከል የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ም/ፕሬዝደንት እንዲሁም የመድረክ ም/ሊቀመንበርና የውጪ ግንኙነት ኃላፊ ሆኑት አቶ ተክሌ በቀለ ለፍኖተ ነጻነት እንዳስታወቁት የመድረክ አባል ፓርቲ የሆኑት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስና በፕ/ር በየነ የሚመራው የኢትዮጵያ ማህበረ ዲሞክራሲ ደቡብ ህዝቦች አንድነት ፓርቲ አንድነት ከመድረክ እንዲባረር ቢጠይቁም አረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ለዴሞክራሲ አንድነት ላልተወሰነ እንዲታገድ የሚል ሞሽን አቅርቦ በጉባኤው ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
አቶ ተክሌ በቀለ የመድረክ አባል ፓርቲዎች አንድነትን ለማገድ የወሰኑባቸው ምክንያዎች አስገራሚ መሆናቸውን ጠቅሰው “የመድረክ አባል ፓርቲዎች አንድነትን ለማገድ የወሰኑት በቅርቡ በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ አንድነት መድረክ ውስጥ ካሉ ፓርቲዎች ጋር ውህደት እንዲፈፀም መወሰኑን፣ አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮችም ውህደት እንደሚያስፈልግ በተለያዩ ሚዲያዎች መናገራቸውን፣ የአንድነት ፓርቲ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ድጋፍ ሰጪዎች በመድረክ ስም የፋይናንስ ድጋፍ እንዲደረግ ትብብር አያደርጉም በሚልና ከመድረክ ዕውቅና ውጪ መስከረም 19(ሰላማዊ ሰልፉ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ህዝባዊ ንቅናቄ የማጠቃለያ መርሀ ግብር ነው፡፡) በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂዷል፡፡” የሚሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ አክለውም አንድነትን በመግፋት መድረክን ወደ አክራሪ ብሔረተኛ ስብስብነት ለመግፋት የተደረገ ስልታዊ ውሳኔ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ አቶ ተክሌ መድረክ የራሱን ዕቅድ አውጥቶ በቁርጠኝነት የማይሰራ በመሆኑ አንድነት በተናጠልና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የተለያዩ ስራዎችን መስራቱን ጠቅሰው “በተደጋጋሚ ለመድረክ በዕቅድ የተደገፉ እንቅስቃሴዎችን በማቅረብ በጋራ እንዲሰራ ቢጠይቅም ቀና ምላሽ አግኝቶ አያውቅም፡፡ ይልቁኑም የራሱን ጥፋት በአንድነት ላይ ለማላከክ ይሞክራል ” ብለዋል፡፡
ነገ አንድነትና መኢአድ በባህር ዳር የሚያደርጉትን ሰላማዊ ሰልፍ በማስተባበር ላይ የሚገኙት የአንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው የመድረክን ውሳኔ አስመልክተው ለፍኖተ ነፃነት እንደገለፁት “ መድረክ በከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ ውጤት ያመጣ ስራ እየሰራ የሚገኘውን አንድነት ፓርቲን ማገዱ ትዝብት ላይ የሚጥል ውሳኔ ነው፡፡” ካሉ በኋላ “አንድነት የታገደው ውጤታማ ስራ ስለሰራና በሚሊዮኖች ድምፅ ንቅናቄ እና በተመሳሳይ ስራዎች የተቀዛቀዘውን የሰላማዊ ትግል በማነቃቃት ትግሉን ወደ ህዝብ ስላወረደ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ አክለውም “መድረክ ውስጥ ካሉት ፓርቲዎች የተሻለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርገው አረና ብቻ ነው፤ የዛሬው ውሳኔ አረናም በቅርቡ የአንድነት እጣ እንደሚገጥመው አመልካች ነው፡፡” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ “መድረክ እንደዚህ ያለ እገዳ ከመወሰን ይልቅ አንድነትና አረና የጠየቁትን ውህደት ተቀብሎ ፖለቲካውን በአንድ ላይ ማንቀሳቀሱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ ውጤት እንደሚያስገኝ አንድነት ያምናል፡፡ ስለዚህ መድረክ የወሰነውን ውሳኔ እንደገና አጢኖ የሀገራችንን ፖሊቲካ በውህደት አብረን እንድንመራ እንዲያደርግ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡UDJ

fredag 21. februar 2014

መኢአድና አንድነት በጋራ የጠሩት የባህርዳር የተቃውሞ ሰልፍ ቅስቀሳ በተሳካ ሁኔታ እየተካሄ ነው ሲሉ አስተባባሪዎች ገለጹ


ከሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት የመኢአድ ሰሜን ቀጠና አደራጅና የተቃውሞ ሰልፉ ግብረሃይል ለኢሳት እንደገለጹት የተቃውሞ ሰልፉን ለመከልከል መንግስት የተለያዩ መንገዶችን ቢጠቀምም፣ አስፈላጊውን መስዋትነት በመክፍል ቅስቀሳቸውን እያደረጉ ነው። የክልሉ መስተዳደር ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና ፈቃድ መስጠቱንም አቶ ሽፈራው ተናግረዋል።
የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አለምነው መኮንን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው ለማስተባበል የሞከሩት ህዝቡን ይበልጥ ማስቆጣቱንም አቶ ሽፈራው ተናግረዋል። በሌላ በኩል መንግስት በእለቱ ተመሳሳይ ተቃውሞ ለማድረግ ማሰቡ ታውቋል። ተቃዋሚዎችን የሚያውግዙ መፈክሮችን በማስጻፍ የከተማው ነዋሪ በእለቱ እንዲወጣ እና ተቃውሞውን በተቃዋሚዎች ላይ እንዲያሰማ ስራ እየሰራ መሆኑን የኢሳት የባህርዳር ወኪል ገልጻለች።
የብአዴን ሹሞች የባጃጅ መኪኖች ሾፌሮችን በመሰብሰብ በተቃውሞው ቀን ድጋፋቸውን እንዳይገልጹ ለማግባባት ሞክረዋል።
አቶ አለምነው መኮንን የአማራውን ህዝብ የሚያንቋሽሽ ዘለፋ የብአዴን ካድሬዎች በተሰባሰቡበት መድረክ ላይ መናገራቸው ይታወሳል። ም/ል ፕሬዚዳንቱ ትናንት በሰጡት መግለጫ ንግግሬ ተቆራርጦ ቀርቦብኛል በማለት ለማስተባበል ሞክረዋል።

torsdag 20. februar 2014

በሱዳን በጎረምሶች የተደፈረችው ኢትዮጵያዊት በድንጋይ ተወግራ ልትገደል ትችላለች ተባለ


ዘጋርድያን እንደዘገበው የ18 አመቷ ወጣትና ነፍሰጡሩዋ ኢትዮጵያዊት በዝሙት ተግባር በመከሰሷ በድንጋይ ተወግራ ልትገደል እንደምትችል የምስራቅ አፍሪካ የሴቶች ስትራቴጂክ ኔትወርክ ወይም ሲሃ የተባለውን ድርጅት በመጥቀስ ዘግቧል። የ9 ወር ነፍሰ ጡሩዋ ወጣት በእስር ቤት ውስጥ ያለምንም ምንጣፍ በባዶ ኮንክሪት ላይ እንደምትተኛ ጋዜጣው ዘግቧል።
ኢሳት ከወር በፊት ዜናውን ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ መንግስት የሱዳን ኢምባሲ የዲያስፖራ ዘርፍ ሃላፊ ሆኑት አቶ….ወጣቱዋ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ገልጸው ነበር።
ይሁን እንጅ ጋርዲያን እንደሚለው ፣ ወጣቱ የ3 ወር ነፍሰጡር እያለች በ7 ጎረምሶች መደፈሩዋን ወዲያውኑ ለፖሊስ ብታመለክትም፣ ፖሊስ ግን የኢድ አል ፈጥርን በአል ሰበብ በማድረግ አቤቱታዋን ሳይቀበላት ቀርቷል።
ወጣቱዋ ዝሙት አለመፈጸሙዋንና ተገዳ መደፈሩዋን ብትናገርም ተሰሚነት አላገኘችም። የሱዳን ፍርድ ቤት የአገሪቱን ፖሊስ ገጽታ ለመጠበቅ ሲል እንዲሁም ጥፋተኞችም ለመታደግ ሲባል ንጹዋን ወንጀለኛ አድርጎ ማቅረቡ አሳሳቢ መሆኑን ሲሃ መግለጹን ዘጋርድያን ዘግቧል።

የፌደራል ፖሊስ አባላት በአያያዛቸው ላይ ቅሬታቸውን አሰሙ።


ቀን አንድ ዳቦ እና ሁለት ጭልፋ ወጥ ለእራትም በተመሳሳይ ሁኔታ የሚቀርብላቸው የመከላከያ ስራዊት አባላት፣  የቀን የምግብ ፍጆታ በጀታቸው ከህግ ታራሚዎች ያነሰ ነው። ወታደሮቹ  በቀን ስምንት ብር ከሃምሳ ሳንቲም በሆነ የምግብ በጅትየሚተዳደሩ ሲሆን፣ የሚቀርብላቸውን ዳቦ እንኳን  ለመብላት እንደሚቼገሩ እና ለምግብ እየተባለ በየወሩ ከደሞዛቸው የሚቆረጠው ገንዘብ እንዳስመራረቸው ተናግረዋል፡፡
“እንደ ኢትዩጵያዊ አማፂ የለም ፣ “የፌድራል ፖሊስ ስኬት በእጁ ላይ ባለው ጥይት የተመሰረተ ነው እንጅ ከመሳሪያ ውጭ የተገኘ ስኬት አይደለም” የሚሉት አንዳንድ ፖሊሶች፣ ህዝቡ መሳሪያ ቢኖረው የሚያቆመው የለም ሲሉም አክለዋል ፡፡
ፖሊሶች ለሚያነሱዋቸው ቅሬታዎች መንግስት የሰጠው መልስ የለም።

ረዳት ፓይለት ሃይለ-መድህን አበራ ብቃት ያለው አብራሪ ነው ተባለ


የኢትዮጵያን አየር መንገድ ንብረት የሆነውን ቦይንግ 767 አውሮፕላን  በመጥለፍ ጄኔቫ ያሳረፈው ሃይለመድህን አበራ፣ ከጸባዩ በተጨማሪ ብቃት ያለው አብራሪ መሆኑን ግለሰቡን የሚያውቁ ሰዎች ለኢሳት ተናግረዋል።
ከስልጠና ጀምሮ የሚያውቁት ጓደኞቹ እንደተናገሩት ሃይለመድህን ለሰዎች ህይወት የሚጨነቅና ጥንቃቄ የሚያደርግ፣ አውሮፕላኑን ከጠለፈ በሁዋላ ተሳፋሪዎች ሳይቸገሩ እንዲያርፍ ማድረጉ የፓይለቱን ብቃት ያሳያል ብለዋል። ምንም እንኳ በረዳት አብራሪነት ደረጃ ቢመደብም፣ ብቃቱና እውቀቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አለመሆኑን ባልደረቦቹ ተናግረዋል።
ኢሳት ባደረገው ማጣራት ደግሞ አውሮፕላኑ ከተጠለፈበት ከሱዳን የአየር ክልል ጀምሮ፣ ፓይለቱ ህዝቡን የሚያስደነግጥ ወይም እንዳይረጋጉ ለማድረግ የተናገረው ነገር አልነበረም። መጸዳጃ ቤት ሄደው የነበሩት ጣሊያናዊው አብራሪ ተመልሰው አውሮፕላኑ እንዲከፈትላቸው በጠየቁበት ጊዜም ቢሆን፣ ፓይለቱ አውሮፕላኑን ጉዳት ላይ የሚጥል ነገር አለመናገሩን ለማወቅ ተችሎአል።
የስዊስ ፖሊስ የጠለፋውን ሂደት በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን እስካሁን አልሰጠም።

የብአዴን ድንጋጤና የእሁዱ የተቃውሞ ሰልፍ


በአማራ ክልል የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አለምነው መኮንን በአማራ ህዝብ ላይ የሰነዘሩትን ዘለፋ ተከትሎ የተነሳውን ተቃውሞ ለማብረድ የብአዴን የወጣቶች ሊግ ለአባለቱ  የስልጠና እና የግምግማ ስራ በባህር ዳር ፤ ደሴ እና ጎንደር እያከናወነ ነው።
የካቲት 16  አንድነትና መኢአድ በጋራ የጠሩትን ሰልፍ ተከትሎ በባህር ዳር ከተማ ባሉ ዘጠኝ ክፍለ ከተሞች 12 የገጠር ቀበሌዎች ብአዴን አባላቱ እና አባል ያልሆኑ  ወጣቶችን በግዳጅ በማስጠራት ባቀረበው የውይይት ሃሳብ እና መመሪያ በማህበራዊ ድረ ገፆች በሚተላለፉ ሃሰተኛ መረጃዎች ማንም ተወናብዶ ሰልፉን መቀላቀል እንደሌለበት አሳስቧል።
የጥፋት ሃይሎች የሚያስወሩት ሴራ ነው የሚለው ብአዴን፣ ሰልፉን ለማጨናገፍ ና ማህበረሰቡ በሰልፉ ላይ እንዳይገኝ ወጣቶች አስፈላጊውን ስራ መስራት እንዳለባቸው መክሯል።
የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት ሃላፊ ወጣት ጌታቸው ብርሃኑ ባቀረበው ጽሁፍ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማምጣት ህዝብ እና መንግስትን የማለያየት ስራ እየሰሩ በማለት ለወጣቶች ተናግሯል፡፡
የብአዴን ጽ/ቤ ሃላፊ የሆኑት አቶ እሱባለው መሰለ በበኩላቸው “የማህበራዊ ድህረ ገጾችን አትመልከቱ ችግር አለባቸው የሚያስተምሩት  ጥላቻ እና አመጽን ነው” በማለት ምክራቸውን ለግሰዋል።
“በማህበራዊ ድረ ገፆች በሚተላለፉ ሃሰተኛ መረጃዎች አንታለልም” የሚል መሪ ቃል ይዞ እየተከናወነ  ያለው ይህ ስልጠና ፣ ኢሳትንና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ማእከል አድርጎ የሚካሄድ ነው።
አንዳንድ ተሰብሳቢዎች ” በድምጽ የሰማነውን ጉዳይ አይን ባወጣ ውሸት እንዴት ይክዱናል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአቶ አለምነውን ንግግር ሳያስተባብሉ ” የብአዴን የወጣት ሊግ እና ታች ያሉ አመራሮች ወጣቱን ለማሳሳት መመኮራቸው ብዙ ተሰብሳቢዎችን አስደምሟል።”
አንዳንድ ወጣቶች ” መረጃውን ለምን ማህበራዊ ሚዲያ እና ኢሳት አቀረበው ብሎ ከመጥላት ለምን አቶ አለምነው ከ22 ሚልየን  በላይ የሚሆነውን ህዝብ ተሳደበ ብሎ” ውይይት አይከፈትም ነበር ሲሉ ተደምጠዋል።  ብአዴን ከህዝብ ይልቅ ግለሰብ ይበልጥብኛል በማለት ጉዳዩን እየሸፋፈነው ነው በማለት አንዳንድ አባሎቹ ለዘጋቢያችን ነግረዋታል።  የጎንደር መሬት ለሱዳን ተቆርሶ መሰጠቱን በተመለከተም ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን በመሳደብ  ስታራቴጅ ችግሩን ለማድበስበስ እየሞከረ መሆኑን ወታጦች መናገራቸውን ሪፖርተራችን ከባህርዳር ዘግባለች።
አቶ አለምነው የአማራው ህዝበ የትምክህት ለሃጩን ማራገፍ አለበት በማለት መናገራቸው ይታወቃል
አንድነትና መኢአድ እሁድ ለሚካሄደው ተቃውሞ በባህርዳር ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ሲሆኑ፣ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ተቃውሞውን እንዲገልጽም ጠይቀዋል።

onsdag 19. februar 2014

ከአርብ ሃገራት የተመለሱ ኢትዩጵያውያን ለዘርፈ ብዙ ችግር መጋለጣቸው ተገለፀ፡፡


የአዕምሮ ቸግር ፤ ዘገምተኝነት ፤ ሱስ ፤ ራስን መጣል ፤ የስነ ልቦና ችግር ፤ድብርት ፤ ከሰው መገለል፤ተስፋ መቁረጥ ፤ እራስን ማጥፋት ፤ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች፤ አሰገድዶ መደፈር ችግር የጣላባቸው ጠባሳ በህይወታቸው ላይ ከባድ ተጽኖ ሁኖ ይሰተዋልባቸዋል ሲል የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስጠናው ጥናት አመልክቷል፡፡
ከአርባ ሃገራት ሰደተኛቸ ተመላሺ ኢትዩጵያውያን የኢትዩጵያን መሬት በረገጡ በሳልስቱ ጀምሮ  የማቋቋሚያ 1800 ብር ይዘው በሱዳን ገዳሪፍ በኩል በህገ ወጥ መጉረፍ የጀመሩት ተይዘው በድጋሜ የተመለሱት እንዳሉ በፖሊስ መረጃ ሚኒስተሩ አረጋግጫለሁ ብለዋል፡፡የመተማ ፖሊስም ሊጠፉ ሲሉ 3 ሺ 242 ተመላሺ ሰደተኞች መያዙን በማየት ቦሌ አየር ማረፊያ አርፈው መተማ ለመሄድ ትኬት ሲቆርጡ እንዴት ዝም ተባሉ ሲል ይጠይቃል።
በመተማ እየሱስ የሃገር ውስጥ ድህነትን ፈርተው በመሸሺ ወደ ሱዳን እና አረብ ሃገራት የሚሰደዱት ቁጥር በቀን 1ሺ 800 የሚገመት ሲሆን ራሳቸውን ስተው በእብደት ደረጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንዳሉ እንዲሁም ባዶ እጃችንን አንመለስም በማለት በሴተኛ አዳሪነት የድንበር ከተማዋን ከበው በቀን በ10 ብር እና 20 ብር ገንዘብ የሴተኛ አዳሪ ህይዎት በሱዳናዊያን ዜጎች እየተደፈሩ እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
3 ከስደተኝነት የተመለሱ ኢትዩጵያውያን በተስፋ መቁረጥ ሃገር ቤት በገቡ በቀናት ጊዜ ውስጥ እራሳቸውን ማጥፋታቸው ታውቋል፡፡

77ኛው የኢትዮጵያ ሰማእታት ቀን ተከብሮ ዋለ


ኢትዮጵያውያን በጣሊያን ወራሪ ሃይል በግፍ የተጨፈጨፉበት ቀን በመላው አለም በሚገኙ ኢትዮጵያውያን እየተዘከረ ነው።
በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰምአታት ሃውልት ጀግኖች አባት አርበኞች በተገኙበት በአሉ ተከብሯል።
የካቲት 12፣ 1929 ዓም አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ኢትዮጵያውያን ግራዚያኒን ለመግደል የጣሉትን ቦንብ ተከትሎ፣ የጣሊያን ወራሪ ሰራዊት በወሰደው እርምጃ  ከ30 ሺ በላይ ኢትዮጵያውን መገደላቸው ይታወቃል።
በ5 አመቱ የጣሊያን ወረራ  ወቅት አእላፍ አእላፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች ወረራውን በመቃወም ሲዋጉ በጀግንነት መውደቃቸው ይታወቃል።

በጠለፋው ዙሪያ ልዩ ጥንቅር



የካፒቴን ሃይለመድህን አበራ የጠለፋ ምክንያት  በአየር መንገዱ ውስጥ የሚታየውን የአስተዳደር መበላሸት ለአለም ለማሳየት ነው  ይችላል የሚለው ምክንያት አሳማኝ ነው ሲሉ አንድ የቀድሞው የድርጅቱ ሰራተኛ ገለጹ
በኢትዮጵያ አየር መንገድ  በበረራ ደህንነት ስራ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ያገለገለውና በክትትልና ደህንነት ስጋት ከአመት በፊት ድርጅቱን ለቆ በስዊዘርላንድ ጥገኝነት የጠየቀው ሚካኤል መላኩ ከኢሳት ጋር ባደረገው  ሰፊ ቃለምልልስ፣ በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ዘረኝነትና የአስተዳደር መበላሸት አጋልጧል።
ወጣቱ ፓይለት የተለያዩ አውሮፕላኖችን አብርሮ ልምድ ካካበተ በሁዋላ 767 የተባለውን አውሮፕላን በረዳት ፓይለትነት ለማብረር መቻሉን የገለጸው ሚካኤል፣ በዚህ ደረጃውም ከፍተኛ የሆነ ክፍያ የሚከፈለው በመሆኑ የገንዘብና የምቾት ችግር እንደማያጋጥመው ገልጿል። አብራሪው የ3 ሺ ሰራተኞችን ዋይታ ይዞ መምጣቱን የሚናገረው ሚካኤል፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎኑ ሊቆምለት ይገባል ብሎአል
የካፒቴን ሃይለመድህን የጠላፋ ምክንያት አወዛጋቢ ሆኖ በቀጠለበት ሁኔታ ፣ ካፒቴኑ ከአጎቱ ከዶ/ር እምሩ ስዩም ሞት ጋር በተያያዘ እየተረበሸ መምጣቱን አቶ አሳምነው መላኩ የተባሉ የካፒቴን ሃይለመድህንን አጎት በመጥቀስ በአሶሺየትድ ፕሬስና በክርስቲያን ሞኒተሪንግ ተዘግቧል። አዲስ አበባ የኑቨርስቲ በድረገጹ ባሰፈረው መረጃም የዶ/ር እምሩ አሟሟት መንስኤ እንግዳ እንደሆነ ጠቅሷል። ኢሳት በበኩሉ ከዘመዶቹ ባገኘው መረጃ መሰረት ዶ/ር እምሩ በሰዎች መገደላቸውን አንዳንድ የቤተሰብ አባሎች እንደሚያምኑና አጎቱን ማን ገደላቸው የሚለው ጥያቄ አለመመለሱን ዘግቧል።
ይሁን እንጅ የዶ/ር ስዩም ባለቤት ነኝ ያሉ ወ/ሮ አንጓች ቢተው ባለቤታቸው የሞቱት ታህሳስ ወር ላይ ጧት ፍላሚንጎ አካባቢ ተሳፍረው ቤተመንግስት አካባቢ ሲደርሱ ከጠዋቱ 2፡30 ላይ መሞታቸውን፣ የሞታቸውም ምክንያት በልብ ህመም ምክንያት መሆኑን በመግለጽ ሰው ገደለው ተብሎ የቀረበው ዘገባ ስህተት መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል። ወ/ሮ አንጓች ካፒቴን ሃይለመድህን በአጎቱ ምክንያት እንደተረበሸ ተደርጎ በሚሰጠውን አስተያየት ዙሪያም ምንም የሚያዉቁት ነገር እንደሌለ፣ ከካፒቴኑ ጋር በአመት በአል ወቅት ካልሆነ ብዙም እንደማይገናኙ  ተናግረዋል።
ካፒቴን ሃይለመድህን ከአጎቱ ሞት ጋር በተያያዘ ይረበሽ ነበር በማለት መግለጫ የሰጡትን ሌላውን አጎት አቶ አሳምነውን ለማግኘትና ማብራሪያ ለመጠየቅ የተደረገው ሙከራ አልተሰካም። በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየቱን የጠየቅነው ዘጋቢያችን፣ ዶ/ር ስዩም በልብ ህመም መሞታቸውን ካፒቴን ሃይለመድህን የሚያውቅ ከሆነ፣ የሚጨነቅበት ምክንያት አይኖርም፣ ከአጎቱ ሞት ጋር በተያያዘ የሚሰጠው አስተያየትም ትክክል ላይሆን ይችላል ብሎአል።
ጠላፊው አውሮፕላኑን ወደ ጄኔቭ ከመውሰዱ በፊት ሮም ላይ ማረፉን የገለጸቸውን ዜና በተመለከተ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች አውሮፕላኑ ሮም ላይ እንዳላረፈ በመግለጽ አስተያየታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ኢሳት በድጋሜ ተሳፋሪዋን ባነጋገረበት ወቅት፣ በአቋሟ በመጽናት አውሮፕላኑ ሮም ላይ አርፎ ወደ ሚላን ሲያቀና መጠለፉን፣ የበረራ ትኬቱዋን ለኢሳት በመላክ ትክክለኛ መረጃ መስጠቱዋን በድጋሜ ተናግራለች።
ጉዳዩ እንዴት ሊሆን ይችላል ስንል ጥያቄ ያቀረብንለት ሚካኤል መላኩ አውሮፕላኑ ሮም ላይ አርፎአል በሚል የተላለፈው ዘገባ ትክክለኛ ነው ብሎ እንደሚያምን የአየር መንገዱን አሰራር በመግለጽ አስረድቷል
የመንግስት የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን አውሮፕላኑ ካርቱም ላይ ማረፉን ፣ ቀጥሎ ደግሞ ካርቱም ላይ ማረፍ የነበረበት ቢሆንም ተጠልፎ ማረፍ ሳይችል ቀረ ብለው የገለጹት የአየር መንገዱን አሰራር ሳይዉቁ የተናገሩት አሳፋሪ ንግግር ነው ብለዋል። በአየር መንገድ የበረራ ታሪክ አውሮፕላኑ በቀጥታ ከአዲስ አበባ ወደ ሮም እንደሚያርፍ በመግለጽ ካርቱም ላይ ማረፍ ነበረበት የሚለውም ትክክል አይደለም ብሎአል።
አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ፓይለቱ አውሮፕላኑን ይዞ ጄኔቫ ላይ በመሽከርከር ለማስፈራራት ሙከራ አድርጎ ነበር በማለት ዘገባዎችን አቅርበዋል። ይሁን እንጅ እንደ ሚካኤል ገለጻ ማንኛውም አውሮፕላን ከማረፉ በፊት ነዳጅ ማቃጠል ስለነበረበት ፓይለቱ ይህን ማድረጉን እንዲሁም ለ10 ደቂቃ ጉዞ ብቻ የሚበቃ ነዳጅ ነበረው ተብሎ በመገናኛ ብዙሃን የቀረበውም ትክክል ያልሆነና በአየር መንገዱ ህግ መሰረት ለ2 ሰአት በረራ የሚያበቃ መጠባበቂያ ነዳጅ እንደሚይዝ ገልጿል።
የኢትዮጵያን አየር መንገድ የውስጥ አሰራርና ችግሮች በተመለከተ ከሚካኤል መላኩ ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለምልልስ ነገ የምናቀርብ መሆኑን እንገልጻለን;

tirsdag 18. februar 2014

ሎንዶን፤ የኢትዮያዊዉ የሳይበር ጥቃት ክስ




ብሪታኒያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ፤ የኮምፒዉተራቸዉን ፕሮግራም በመጥለፍ የሚጠረጥሩትን የኢትጵያን መንግሥትን እርምጃ እንዲመረምር የብሪታንያን ፖሊስ ጠየቁ።

 አቶ ታደሰ ከርሰሞ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በስካይፕ ከተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ጋ የሚያደጓቸዉን ግንኙነቶች ለመከታተል የኢንተርኔት ስለላ ፕሮግራም ልኮብኛል ባይናቸዉ።

 የግል ፋይሎቻቸዉም እሳቸዉ ባላወቁት መንገድ በኢንተርኔት መለቀቃቸዉንም ገልጸዋል። ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም፤ ተሰደዉ ብሪታንያ ሲገቡ እንዲህ ካለዉ ክትትል ነፃ የሆኑ መስሏቸዉ እንደነበር ነዉ ያመለከቱት።

 ሎንዶን የሚገኘዉ ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል፤ ባዘጋጀዉ መድረክ ጉዳዩን ይፋ ሲያደርጉም የብሪታኒያ ኩባንያ በዚህ ተግባር ተሳትፎ እንደሆነ እንዲጣራላቸዉ ጠይቀዋል። ቶሮንቶ የሚገኘዉ የኢንተርኔት ተከታታይ ቡድን ሲቲዝን ላብ፤ ባደረገዉ ምርመራም ኮምፕዩተራቸዉ ብሪታንያ የሚገኘዉ ጋማ ቡድን በሚያከፋፍለዉ የኮምፒዩተር ስለላ ፕሮግራም መጠመዱን የሚያሳይ ማስረጃ አግኝቷል።

 እንደዘገባዉ ግለሰቡ በዉጭ ሃገራት ከሚገኙና ተመሳሳይ የሳይበር ጥቃት ከሚደርሳቸዉ ኢትዮጵያዉያን አንዱ ናቸዉ። የኢትዮጵያ መንግስትን በግለሰቡ የቀረበዉን አቤቱታ መሠረተ ቢስ ሲል አጣጥሏል።

የረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ የአውሮፕላን ጠለፋ የአለም መነጋገሪያ በመሆን ቀጥሎአል


የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 702 የሆነውን አውሮፕላን በመጥለፍ ጄኔቫ ስዊዘርላንድ ያሳረፈው ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ እስካሁን ድረስ የጠለፋውን መንስኤና ምክንያት በግልጽ የመናገር እድል ባለማግኘቱ የአለም የመገናኛ ብዙሃን የተለያዩ አስተያየቶችን እየሰጡ ነው።
አንዳንዶች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አስከፊ ጭቆናና ፓይለቱ አውሮፕላኑን እንዲጠልፍ እንዳነሳሳው ሲገልጹ ሌሎች ወገኖች ደግሞ ጥገኝት ለመጠየቅ ተብሎ ከተደረገ ስህተት ፈጽሟል ብለው ይተቻሉ።
ባህርዳር አካባቢ ተወልዶ ያደገው ሃይለመድህን አበራ በአንጻራዊ መልኩ ሀብታም ከሚባል ቤተሰብ መምጣቱን የሚናገሩት ፓይለቱንም ሆነ ቤተሰቦቹንም እናውቃለን የሚሉ የባህርዳርና የአካባቢው ሰዎች፣ ፓይለቱ በትምህርቱ እጅግ ጎበዝ የሚባልና ታታሪ ሰራተኛ እንደሆነ ይገልጻሉ።
አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ ሰው ሃይለመድህን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ስላለው ቢሮክራሲና ዘረኝነት ደጋግሞ ይናገር እንደነበር ገልጿል።
ታናሽ እህቱ እንደሆነች የምትገልጽ ትንሳኤ አበራ በበኩሉዋ ሃይለመድህን ” የሰዎችን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል አይደለም እንስሳትን ለመጉዳት የሚፈልግ ሰው አለመሆኑን፣  ከአገር ውጭ ወጥቶ ለመኖር ፍላጎት እንዳልነበረውም ገልጻለች።
በብሄራዊ መልቀቂያ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ትምህረቱን ያጠናቀቀው ሀይለመድህን የጀመረውን የ አርክቴክቸር ትምህርት ትቶ ወደ ፓይለትነት የገባው ለሙያው ካለው ፍቅር የተነሳ መሆኑንም ገልጻለች።
“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህይወቱ ደስታ የራቀው መሰለ” የምትለው እህቱ፣ ስለሁኔታው ሲጠየቅ ” ጠላቶች እንዳሉ እንደሚያምን ፣ ስልኩን እንደጠለፉት እንደሚያስብ፤ በላፕቶፑ ካሜራ ሳይቀር ያዩኛል ብሎ ስለሚሰጋ ካሜራውን ሳይሸፍን እንደማይከፍት እንዲሁም፤ ወጥቶ እስኪገባ ቤቱን ሲበረብሩ የቆዩ ስለሚመስለው ካሜራ ጠምዶ መሄድ ሁሉ እንደጀመረ ገልጻለች።”
” ባጠቃላይ በታላቅ የመንፈስ ጭንቀት እየተሰቃየ ነው”፣ የምትለው እህቱ፣  የሚያሳዝነው ደግሞ ይህንን ጉዳቱን ለኛ ለቤተሰቡንኳ አብራርቶ አለመናገሩ ነው ” ብላለች።
ሌሎች ጓደኞቹ በበኩላቸው ሃይለመድህን የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ የገባው አጎቱ ባለፈው ጥር ወር ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ከተገደሉ በሁዋላ ነው ይላሉ። አጎቱ ዶ/ር እምሩ ስዩም ባለፈው ጥር ወር ከስራ ሲወጡ ታክሲ ውስጥ ሞተው የተገኙ ሲሆን፣ ዶ/ሩን ማን እንደገደላቸው በውል ባይታወቅም፣ አንዳንድ ወገኖች ግን ግድያው ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ  በድረገጹ ላይ ባሰፈረው ሪፖርት የፕሮፌሰር  እምሩ  ስዩም ሞት አስገራሚ መሆኑን ገልጿል።
ሃይለመድህን ከአጎቱ ሞት በሁዋላ እርሱም በተመሳሳይ አደጋ ውስጥ እገኛለሁ ብሎ ሲሰጋ እንደነበር፣ በተለይም በአየር መንግዱ ውስጥ የተሰባሰቡት ካድሬዎች፣ ያሳድዱኛል ብሎ እንደሚያስብ ፓይለቱን ባለፈው ጥር ወር ላይ እንዳገኘው የሚገልጽ ወጣት ለኢሳት ተናግሮአል።

mandag 17. februar 2014

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጠለፈበትን ምክንያት ለማወቅ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንደቀጠሉ ነው

አየር መንገዱ ከአዲስ አበባ ወደ ሮም ጣሊያን በማምራት ላይ በነበረበት ጊዜ  ረዳት አብራሪው የጉዞውን አቅጣጫ በመቀየር ጄኔቭ አውሮፓላን ማረፊያ በማሳረፍ እጁን ለፖሊስ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት የኮሚኒኬሽን ባለስልጣን የሆኑት ሬድዋን ሁሴን አየር መንገዱ የተጠለፈው ሱዳን በቆመበት ጊዜ በተሳፈሩ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ነው በማለት መጀመሪያ ላይ ለረዩተርስ መግለጫ ቢሰጡም፣ የስዊዘርላንድ ፖሊስ ግን ፈጥኖ ጠላፊው የአየር መንገዱ ረዳት አብራሪ መሆኑንና የደህንነት ስጋት እንዳለበት በመግለጽ እጁን በሰላም መስጠቱን አስታውቀዋል።
በአለም የጠለፋ ታሪክ ያልተመደ ክስተት ነው የተባለው ይህ የአውሮፕላን ጠለፋ፣ የፖለቲካ ይዘት ያለው ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል።
ማንነቱ ያልታወቀው ረዳት ፓይለት በ30 ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ጄኔቭ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሰ በመስኮት በኩል በመውጣት እጁን በሰላም ለፖሊስ ሰጥቷል። ፖሊስ እንዳስታወቀውም ጠላፊው ምንም አይነት የጦር መሳሪያ አልያዘም።
በአውሮፕላኑ ውስጥ በነበሩ ተሳፋሪዎች ላይ ምንም አይነት ጉዳትም አልደረሰም።
ጄኔቭ የሚገኘው የኢሳት ወኪል እንደዘገበው ምንም እንኳ ጄኔቫ አየር ማረፊያ ከሰአታት በሁዋላ ተራግገቶ ስራውን ለማከናወን የቻለ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር እስከ ቀኑ 9 ሰአት ድረስ ተሳፋሪዎች ወደ ሮም አልተመለሱም፣ አውሮፕላኑም ባለበት ቆሞ ይታይ ነበር። ከቀኑ 9 ሰአት ከሰላሳ አካባቢ አውሮፕላኑ ለጥገና ወይም ተሰፋራዎችን ወደ ሮም ለመመለስ ሲንቀሳቀስ መታየቱን ወኪላችን ገልጾ፣ ጠላፊውን ለማግኘት የተደረገው ሙከራ በፖሊስ ጥብቅ ቁጥጥር የተነሳ ሊሳካ አልቻለም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች በተለያዩ ጊዜያት በአስተዳደሩ እንደሚማሩ ይታወቃል። አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በማንሳት ጠለፋውን ከፖለቲካ ጋር በማያያዝ ለማየት እየሞከሩ ነው።
ረዳት ፓይለቱ አላማው ጥገኝነት መጠየቅ ቢሆን ኖሮ አውሮፕላኑን ሮም ላይ ካሳረፈ በሁዋላ ጄኔቭ ገብቶ በሰላም እጁን መስጠት ይችል እንደነበር ጁኔቭ የሚገኙ አንዳንድ አስተያየት ሰጪ ይናገራሉ።  ረዳት ፓይለቱ ይህ እድል እያለው እና አውሮፕላን መጥለፍ ወንጀል መሆኑን እያወቀ እንዲህ አይነት እርምጃ ለመውሰድ የተነሳሳው አንድ ከባድ ምክንያት ቢኖረው ነው በማለት እኝሁ አስተያየት ሰጪ ገልጸዋል።
በስዊዝ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጠበቆች ረዳት ፓይለቱን ለማግኘትና ጠበቃ ቐጥረው ለመከራከር ፍላጎት እንዳላቸው ለኢሳት ገልጸዋል።
ስቱዲዮ ከመግባታችን በፊት በአውሮፕላኑ ወስጥ ተሳፍራ የነበረች አንዲት ወጣት አግኝተናል። ወጣቱዋ እንደምትለው አውሮፐላኑ የተጠለፈው ከሮም ወደ ሚላን በሚመበርበት ጊዜ ነው። ሮም ማረፉንና መንገደኞችን ማሳፈሩን ወጣቷ ተናግራለች። አቶ ሬድዋን በበኩላቸው አውሮፐላኑ ሮም ሳያርፍ ወደ ጄኔቭ መሄዱን ተናግረዋል። ወጣቱዋ አብራሪው ረጅም ና ጠይም መሆኑንሮም ላይ ሻንጣውን ማውረዱንና ፊቱ ላይ አለመረጋጋት ይታይበት እንደነበር ገልጻለች።
ከወጣቱዋ ጋር ያደረግነው ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል።

søndag 16. februar 2014

የቡና ኤክስፖርት ለሙስናና ብልሹ አሰራር ተጋልጧል



ቡናን ኤክስፖርት ከማድረግ ጋር በተያያዘ በክትትልና ቁጥጥር፣ በመረጃ አያያዝ፣ ያለብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ቡናን ወደውጭ ኤክስፖርት ከማድረግ እና በሁሉም አካባቢ የቡና ድርጅቶችን መጋዘኖች ክምችት ቆጠራ በወቅቱ ባለማድረግ ላይ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ያጠናው አንድ ጥናት አመለከተ፡፡
ጥናቱ  ኤክስፖርት በማያደርጉ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ያለመውሰድ፣ በንግድ ፈቃድ ላይ የተጠናከረ ቁጥጥር ያለማድረግ እና በሕገወጥ የቡና ምርት ዝውውርና ግብይት ላይ የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው ያለመስራት በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውን ማመላከቱን ኮምሽኑ በድረገጹ ላይ ባሰፈረው ዜና ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው የግብርና ምርቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የቡና ኤክስፖርት ሒደት ለሙስናና ብልሹ አሠራር ያለውን ተጋላጭነት አስመልክቶ በኮሚሽኑ የተካሔደው ጥናት ይፋ የሆነው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ሰሞኑን በግዮን ሆቴል ጥናቱን ለማዳበር በተከናወነ የምክክር ስብሰባ ላይ ነው፡፡
የውይይት መድረኩ የተዘጋጀበት ዓላማ በዘርፉ ስለሚስተዋሉ የአሠራር ጉድለቶች ለሚመለከታቸው ክፍሎች ግልጽ ግንዛቤ ለማስያዝና ችግሮቹን በመቅረፍ ረገድ የተሻለ አሠራር በማመላከት የመፍትሔው አካል ሆነው የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል እንዲሁም በክፍተቶቹ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ለመፍትሔው በጋራ ለመንቀሳቀስ ነው ተብሎአል፡፡
አገሪቱ ከቡና ኤክስፖርት የምታገኘው ገቢ በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ማሽቆልቆሉ የሚታወቅ ሲሆን ችግሩ ከዚህ ዓይነቱ ሙስናና ብልሹ አሰራር ጋር በቀጥታ ይያያዝ ፣አይያዝ የተገለጸ ነገር የለም፡፡

fredag 14. februar 2014

በርካታ የየረር ጎሳ አባላት የአገር ሽማግሌዎች ታሰሩ


በሶማሊ ክልል በቀላፎ አካባቢ የሚኖሩ 19 የየረር ባሬ ጎሳ የአገር ሽማግሌዎች በክልሉ ውስጥ የተፈጸመውን ከፍተኛ እልቂት ለጠ/ሚንስትሩ አቤት ለማለት ወደ አዲስ አበባ በሄዱበት ወቅት  አካባቢውን በሚጠብቁ ልዩ ሃይሎች ተይዘው መታሰራቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ከእስር ያመለጡ አንዳንድ ሽማግሌዎች በትናንትናው እለት ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ከዚህ ቀደም በልዩ ሚሊሺው በቀጥታ የተገደሉትን የ47 ሰዎች ስም  ፣ ከቆሰሉ በሁዋላ በህክምና እጦት የሞቱትን የ 17 ሰዎች ስም እንዲሁም ከ100 በላይ ቁስለኞችን እና የታሰሩትን ሰዎች ስም ዝርዝር የያዘውን ደብዳቤ ለቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ፣ በአሁኑ አጠራር ለሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ፣ በመንግስት እንደሚደገፍ ለሚነገርለት ለኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ለእንባ ጠባቂ እና በድጋሜ ለጠ/ሚንስትር ጽ/በት አስገብተዋል።

በደብደቤያቸው ላይ ለጠ/ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ያስገቡትን ደብዳቤ ቁጥር በመጥቀስ ፣ ጠ/ሚንስትሩ እስካሁን መልስ እንዳልሰጡዋቸው በደብዳቤያቸው ላይ ገልጸዋል።
የአገር ሽምግሌዎቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሀመድ ኡመር እና ጄኔራል አብርሀም በቅጽል ስማቸው ኳታር የሚመራው ልዩ ሚሊሺያ እየተባለ የሚጠራው ሀይል ታህሳስ 1 እና 2 በከፈተው ተኩስ በትምህርት ላይ

የነበሩ ህጻናትንና ወጣቶችን ጨምሮ 47 ሰዎችን መግደሉን የሟቾቹን ስም ዝርዝር በመጥቀስ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወቃል።

 
ልዩ ሚሊሺያው ተማሪዎች በትምህርት ላይ እንዳሉ ተኩስ መክፈቱን የአገር ሽማግሌዎቹ በደብዳቤያቸው ላይ የገለጹ ሲሆን፣ የፌደራሉ መንግስት በአስቸኳይ ደርሶ እንዲታደጋቸውም ጠይቀዋል።

የየረር ባሬ ጎሳ አባላት የክልሉ መንግስት እንደ ተወላጅ ባለመቁጠር ጭቆና እንደሚያደረስባቸው በመግለጽ ራሳቸውን የማስተዳደር መብት እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በክልሉ መንግስት ልዩ ሚሊሺያዎችና በየረር ባሬ ጎሳ አባላት መካከል ተደጋጋሚ ግጭት ሲደረግ ከቆየ በሁዋላ ሰሞኑን መሳሪያ ለማስፈታት ወደ አካባቢው የተጓዘው የክልሉ ልዩ ሚሊሺያ ሃይል ካፍ እየተባለ በሚጠራው ትምህርት ቤት ላይ በከፈተው ተኩስ ህጻናትንና ሴቶችን ጨምሮ 47 ሰዎች መገደላቸውን ፣ ጥር 11 በተቀሰቀሰው ግጭት ደግሞ  ከ100 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውንና 17 ሰዎች በህክምና እጦት መሞታቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የብሄረሰቡ ተወካይ ለኢሳት ገልጸው ነበር።


ዜናው በኢሳት መተላለፉን ተከትሎ የሚሊሺያ ሃይሉ በሶስተኛው ቀን 16 የአገር ሽማግሌዎችን ይዞ ማሰሩንም መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ባለፉት 6 ቀናት የታሰሩትን የአገር ሽማግሌዎች ጨምሮ እስካሁን ከ35 በላይ የብሄረሰቡ ተወካዮች ታስረዋል።

የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽነር ለማነጋገር ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም።