mandag 27. mars 2017

የየካ አባዶ ደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን እንድትፈርስ ፍ/ቤት ወሰነ


የደብሩ አስተዳደር ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ ጠይቋል

(አዲስ አድማስ፤ ቅዳሜ፣ መጋቢት 16 ቀን 2009 ዓ.ም.)

አበባ የካ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 12 ውስጥ የምትገኘው፣ የየካ አባዶ ደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን፣ በሕገ ወጥ ይዞታ ላይ፣ ያለግንባታ ፈቃድ መሠራቷን የገለጸው ፍ/ቤት፣ እንድትፈርስ ወሰነ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት፣ የካ ምድብ ችሎት፣ ባለፈው ረቡዕ በሰጠው ውሳኔ፥ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዳትፈርስ፣ በደብሩ ለቀረበው የሁከት ይወገድልኝ ክሥ፣ ኅዳር 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ሰጥቶት የነበረው የእግድ ትእዛዝ መነሣቱን አስታውቋል፡፡
በከሣሽ፥ የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን እና በተከሣሽ፥ የወረዳው ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት መካከል የቀረቡትን አቤቱታዎችና ሲካሔድ የቆየውን የቃል ክርክር መመርመሩን የገለጸው ፍ/ቤቱ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ የተሠራችበትን ቤትና ቦታ፣ ሰኔ 24 ቀን 2008 ዓ.ም በተደረገ የስጦታ ውል ያስተላለፉት ግለሰቦች፤ ይዞታውን በሕጋዊ አግባብ ባልተጨበረበረ ኹኔታ እንዳገኙት የሚያስረዳ ማስረጃ በከሣሽ በኩል አልቀረበም፤ ብሏል፡፡
ቤቱም፣ የሚመለከተው የከተማው አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽ/ቤት ፈቃድ ሰጥቶ ስለ መሠራቱ ማስረጃ አለመቅረቡንና በመሥመር ካርታ ወይም በ1997 ዓ.ም. የአየር ካርታ ላይ እንደማይታይ፣ የክፍለ ከተማው የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽ/ቤት፣ በፍርድ ቤቱ ትእዛዝ
አጣርቶ በሰጠው ምላሽ ማረጋገጡን አስረድቷል፡፡
ለክሡ መነሻ የኾነው ቤት፣ በደብሩ አስተዳደር የቤተ ክርስቲያን ቅርጽ እንዲኖረው ተደርጎ በድጋሚ የተሠራውም፣ በሕግ ሥልጣን ከተሰጠው የከተማው አስተዳደር አካል፣ በቅድሚያ የግንባታ ፈቃድ ሳይገኝ መኾኑን ፍ/ቤቱ በውሳኔው ጠቅሷል፡፡
የወረዳው ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ግንባታ እንዲያቆምና የተሠራውም እንዲፈርስ፣ ለደብሩ የሰጠው ማስጠንቀቂያ፦
“በሕግ የተሰጠውን፥ የከተማውን ማስተር ፕላን የማስጠበቅ ሓላፊነት መወጣቱ እንጂ፣ የሁከት ተግባር አይደለም፤ በደብሩ የቀረበውም ክሥ ተቀባይነት የለውም፤” ሲል ወስኗል፡፡ ለለይዞታ ክሡ መነሻ በኾነው ግንባታ ላይ ቀደም ሲል ተላልፎ የነበረው የእግድ ትእዛዝ መነሣቱንም አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል፣ የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ የፍ/ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ መጠየቁ ተጠቁሟል፡፡
ይዞታውን ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ በስጦታ ውል ያስተላለፉት በጎ አድራጊዎች፣ በሕጋዊ ውርስ ያገኙትና የመንግሥት ግብር ይገብሩበት እንደነበር፣ አዋሳኙ ተጠቅሶ በፍ/ቤት የተረጋገጠ ማስረጃ፣ በደብሩ በኩል ለችሎቱ ቀርቦ እንደነበር ተገልጧል፡፡
ቤቱም የተሠራው ከ1997 ዓ.ም. በፊት ሲኾን፣ ቆርቆሮውን በመቀየር ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲመች ለማድረግ መለስተኛ ለውጥ መደረጉ ተጠቅሷል፡፡ ይህም፣ በቁጥር 217 ያኽል የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በቅድስት አርሴማ ስም ቤተ ክርስቲያን እንዲተከልላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ መሠረት አድርጎ የተከናወነ መኾኑ ታውቋል፡፡
ምእመናኑ፣ ለየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የአቀረቡትን ጥያቄ መነሻ በማድረግ፣ ቤተ ክርስቲያን ማቋቋም እንዲቻል፣ ሀገረ ስብከቱ፣ ለየካ ክፍለ ከተማ መሬትና ልማት አስተዳደር ጽ/ቤት በደብዳቤ ቢያሳውቅም፣ ለሳምንታት ምላሽ ሳይሰጥ በመቆየቱ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በቅድስት አርሴማ ስም የተፈቀደው ጽላት ገብቶ ቤተ ክርስቲያኒቱ ላለፉት አራት ወራት አገልግሎት በመስጠት ላይ እንዳለች ውዝግቡ መቀስቀሱ ተመልክቷል፡፡
“ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ከላይ በተገለጸው አግባብ ተቋቁማ ለአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት እየሰጠች ባለችበት፣ የወረዳው ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ሥልጣኑን ያለአግባብ ተጠቅሞ ለማፍረስ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ በመኾኑም፣ እየፈጠረ ያለው የሁከት ተግባር እንዲወገድ አመልክተናል፤” ይላል፣ በደብሩ ቀርቦ የነበረው የክሥ ማመልከቻ፡፡
Source:  አዲስ አድማስ

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar