lørdag 26. august 2017

የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ” አማካይነት በኦሮሚያ እና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተፈፀመዉን ወረራ በማስመልከት የኦሮሞ ዲ. ግንባር ባለ6 ነጥብ መግለጫ አወጣ

በ”የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ” አማካይነት በኦሮሚያ እና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተፈፀመዉን ወረራ በማስመልከት ከኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር የተሰጠ መግለጫ
(PDF) ባለፉት ሦስት ዓመታት ዉስጥ በሕወሐት የሚመራዉና ለስሙ “የኢትዮጵያ መንግሥት ነኝ” የሚለዉ ገዢ ቡድን የተስፋፊዉን የሶሚሊያ መንግሥት የ“ታላቋ ሶማሊያ” ምሥረታ ህልም ዕዉን ለማድረግ እንደሚሠራ የሚያመለክቱ የተለያዩ ደባዎችን “አስተዳድረዋለሁ” በሚለዉ የኦሮሞ ሕዝብ ለይ እየፈፀመ መሆኑን በግልፅ አሣይቷል፡፡ እንደሚታወቀዉ የኦሮሚያን መሬት እና ሌሎች የአካባቢዉ ግዛቶችን አጠቃሎ “ታላቋን ሶማሊያ“ የመመሥረት ሙከራ የተጀመረዉ በዚያድባሬ ዘመነ መንግሥት ነበር፡፡ የ“ታላቋ ሶማሊያ” ምሥረታ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በጂቡቲ ግዛቶቸ ዉስጥ የሚኖሩትን የሶማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በወታደራዊ ኃይል በማንበርከክ እነዚህ ሕዝቦች የሰፈሩበትን መሬት ወደ ሶማሊያ ግዛት ለማጠቃለል የታለመ እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ ይህ የ“ታላቋ ሶማሊያ” ህልም እንግዲህ በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ በባሌ፣ በአርሲ፣ በጉጂ እና በቦረና የሚኖሩትን የኦሮሞ ብሔር አባላት እስከነመሬታቸዉ “ሶማሌ አቦ“ የሚል ስያሜ ሰጥቶ የሶማሊያ አካል ለማድረግ ታስቦ የተጀመረ የተስፋፊነት ህልም ነበር፡፡
በ1977 የሶማሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የከፈተዉ ጦርነትም ይህን ህልም ዕዉን ለማድረግ ታስቦ የተከፈተና በኢትዮጵያ ሕዝብ ድል አድራጊነት የተደመደመደ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነዉ፡፡ ይህ በምሥራቁ የአገራችን ክፍል የተካሄደዉና የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወገኖቹ ጋራ በመሆን በጀግንነት ያከሸፈዉ የሶማሊያ የመስፋፋት ህልም ኋላ ላይ ሶማሊያ የምትባለዉም አገር እንድትፈርስ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ በዕብሪተኝነት የመስፋፋት ዓላማን ይዞ የተነሣዉ የዚያድባሬ መንግሥት ይመራቸዉ የነበሩት ልዩ ልዩ ጎሣዎች መስፋፋቱ ሣይሣካላቸዉ ሲቀር ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ገብተዉ የገዛ አገራቸዉን እስከማፍረስ እና መንግሥት-አልባ እስከመሆን ደረሱ፡፡
የ“ታላቋ ሶማሊያ“ ህልመኞች ያተኮሩባቸዉን የአገራችንን ግዛቶች ስናስብ እንግዲህ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መንግሥታት መካከል ተካሂዶ የነበረዉና በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት የተደመደመዉ የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት በኦሮሞ ሕዝብ እና በዚያድባሬ ተስፋፊ መንግሥት መካከል የተደረገ ጦርነት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በወቅቱ የኦሮሞ ታጋዮችና መሪዎች ይህን ኦሮሞን ወደሶማሌነት ለመለወጥና በባርነት አስገድዶ ለመግዛት ታቅዶ የተከፈተብንን የመስፋፋት ጦርነት በጀግንነትና በቆራጥነት ተቋቁመዋል፡፡ በጣም ብዙ የኦሮሞ ታጋዮችም የደም፣ የአጥንት እና የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር ለ1977 የዚያድባሬ ወረራ መክሸፍ የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ የማይረሣዉ አኩሪ ሚና ተጫዉቷል፤ ከፍተኛ መስዋዕትነትም ከፍሏል፡፡
ይህ የኦሮሞን መሬት ቆርሶ በተዘዋዋሪ መንገድ ለሶማሊያ የመስጠት ዓላማ ዛሬም ቢሆን በሕወሐት አበረታችነትና ደጋፊነት መልኩን ቀይሮ እንደቀጠለ ነዉ፡፡ ይህ የአሁኑ ወረራ ከማንም በላይ የሚመለከተዉ የተወረረዉ ግዛት ባለቤት የሆነዉን የኦሮሞ ሕዝብ እንደመሆኑ መጠን እያንዳንዱ ኦሮሞ ከተወረረዉ አካባቢ ያለዉ ርቀት ሣያግደዉ፣አቅጣጫ ሣይከልለዉ፣ የአፋን ኦሮሞ የአነጋገር ዘይቤ ሣይከፋፍለዉ እና የፖለቲካ አመለካከት ብሎም የፖለቲካ ድርጅት አባልነት ወይም ደጋፊነት ሣይለያየዉ እስከዛሬ ሲያደርግ እንደነበረዉ ሁሉ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተነቃንቆ በኦሮሞነቱ ብቻ አብሮ በመቆም ለወራሪዉ ቡድንም ሆነ ቡድኑን አቅፎና ደግፎ በእጅ አዙር ላሰማራዉ የሕወሐት ገዢ ቡድን የማያዳግም ትምህርት የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ይህ ግዴታ የሚመነጨዉ ደግሞ የዚህ ወይንም የዚያ አካባቢ ተወላጅ ከመሆን፣ ወይም የዚህ ወይንም የዚያ ፖለቲካ ድርጅት አባል ወይም ደጋፊ ከመሆን ሣይሆነ ከኦሮሞነት እና ኦሮሞነት ብቻ ነዉ፡፡ ክምንም በላይና ከየትኛዉም አመለካከታችን በፊት ኦሮሞነታችን (ማንነታችን) ሊያቀራርበንና አንድ ላይ ሊያቆመን ይገባል፡፡ ስለሆነም በኦሮሚያ መሬትና በኦሮሞ ሕዝብ አንድነት ላይ አነጣጥሮ የተከፈተብንንና የሕወሐት እጅ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መንገድ ያለበትን ይህን የአሁኑን የመስፋፋት ጦርነት የኦሮሞ ሕዝብ ከዳር እስከዳር ተንቀሣቅሶ በጀግንነት፣ በአንድነት እና በወንድማማችነት ስሜት በጋራ በመታገል ማክሸፍ አለበት፡፡ የተጠየቀዉን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍለን ይህን መልኩን ቀይሮ በአዲስ መንገድ የተሰነዘረብንን የታላቋ ሶማሊያን ህልም እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም ማክሸፍ ብቻም ሣይሆን ዳግም እንዳያንሠራራ አድርገን ከመሠረቱ መምታት ይኖርብናል፡፡ በአንድነት ቆሞ ለአንድ የጋራ ዓላማ አብሮ መታገልን ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ በፊንፍኔ ጉዳይ ማለትም በ”የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን” ተብዬዉ የሕወሐት ሴራ ላይ፣ በቁቤ አፋን ኦሮሞ ጉዳይ እና ኦሮሞን እንደኦሮሞ በሚመለከቱ ሌሎች ሕወሐት-ሠራሽ ጥፋቶች ላይ በተግባር አሣይቷል፤ አሁንም እያሣየ ነዉ፡፡ በ”ሶማሌ ልዩ ፖሊስ” ስም ከሕወሐት የተሰነዘረብንን ወረራ ለማክሸፍም በኦሮሞነት ላይ የተመሠረተ አንድነታችን ከምን ጊዜዉም በላይ አስፈላጊ ነዉ፡፡
ስለሆነም በሕወሐት ግፊት ብሎም በሕወሐት አገዛዝ የጦር መሣሪያና የሞራል ድጋፍ የተጀመረዉን የሶማሌ ክልል ወረራ የማክሸፉ ተግባር የእያንዳንዱ ኦሮሞ የማይናወጥ ጠንካራ የኦሮሞነት አቋም የሚንፀባረቅበት የኦሮሞ አንድነትም በተግባር የሚታይበት እንደሚሆን የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር በፅኑ ያምናል፡፡ ይህን ፅኑ እምነት መሠረት በማድረግም የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ለሁሉም ነፃነት ፈላጊ ወገኖች፤ በኦሮሞ ሕዝብ ስም ተደራጅተዉ ለሚንቀሣቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት በሙሉ እና ለመላዉ የኦሮሞ ሕዝብ የሚከተለዉን የትግል ጥሪ ያቀርባል፡-
1. የኦሮሞ የሲቪክና የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ በአስቸኳይ ተሰብስበን ይህን በኦሮሚያ መሬትና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተሰነዘረዉን ወረራ እንዴት ማክሸፍ እንደሚቻል ተወያይተን ዉጤታማ የሚያደርገንን መፍትሔ በጋራ እንድንፈልግ ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡ በመሠረቱ በነፃነት ጉዳይና የኦሮሚያን ግዛት በማስከበር ጥያቄ ላይ ካልተስማማን በምን ላይ ልንስማማ እንችላለን?
2. አሁን በሥልጣን ላይ ካለዉ የኢትዮጵያ መንግሥት ተብዬ የጥቂቶች ገዢ ቡድን ጋር እየሠራችሁ ያላችሁ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆናችሁ ሕዝባዊና የሙያ ማህበራት አብራችሁ እየሠራችሁ ያላችሁት የሕወሐት ገዢ ቡድን የኦሮሚያን መሬት ለባዕዳን አሣልፎ ከመስጠት ወደኋላ የማይል፣ የኦሮሞን ሕዝብ ከአገር ባለቤትነት ወደተዋራጅ ባርነት ዝቅ ለማድረግ ሌት ከቀን የሚሠራ መሠሪ ቡድን መሆኑን ተረድታችሁ አሰላለፋችሁን በአስቸኳይ አስተካክሉ ልንላችሁ እንወዳለን፡፡ ከምንም በላይ የኦሮሞን ሕዝብ ደም እያፈሰሰ፣ ሕይወት እየቀጠፈ፣ ብሎም ሌሎች ፀረ-ኦሮሞ የሆኑ ኃይሎችን በኦሮሚያና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የበላይ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ካለ መንግሥት ነኝ ባይ የጥቂት ወያኔዎች ቡድን ጋር በመሰለፋችሁ ከታሪክ ተጠያቂነት አትድኑም፡፡ ስለሆነም የኦሮሚያ ምክር ቤት አባላት፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) አባላት እና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ነኝ ከሚለዉ የጥቂቶች ቡድን ጋር በአንድ ወይም በሌላ መልኩ እየሠራችሁ ያላችሁ ኦሮሞዎች በሙሉ ዛሬ ነገ ሣትሉ የተሣሣተ አሰላለፈችሁን እንድትመረምሩና ሕዝባችሁን ከሶማሌ ወራሪና ከሕወሐት አገዛዝ ነፃ ለማድረግ የሚካሄደዉን ፍትሃዊ ትግል እንድትቀላቀሉ ጥሪ እናደርግላችኋለን፡፡
3. ኦሮሞ ሆናችሁ የህወሀትን መንግሥት በማገልገል ላይ የምትገኙ የአገር መከላከያ፣ የፖሊስና የደህንነት አባላት በሙሉ ከአብራኩ የወጣችሁት የኦሮሞ ሕዝብ በቆራጥነት ያነሣዉ የነፃነት፣ የሰላም፣ የአንድነትና የአገሩ ባላቤት የመሆን ጥያቄ እናንተንም ስለሚመለከት ከገዢዉ ቡድን ተፅዕኖ ሥር በመዉጣት የኦሮሞን ሕዝብ ትግል እንደትቀላቀሉ ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡
4. ታላቁ የኦሮሞ ሕዝብ ሆይ፡- እንደማንኛዉም የዓለም ሕዝብ በገዛ አገርህና ተፈጥሮ በለገሰችህ ለም ምድር ላይ በሰላም፣ በክብርና በነፃነት ሠርቶ የመኖር ሙሉ መብት አለህ፡፡ ለጊዜዉ ግን የጠላቶችህ አፈናና ጭቆና ከዕለት ወደዕለት እየጨመረብህ ነዉ፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ጠንክረህ በመታገል ድልን እንደምትጎናፀፍ አንጠራጠርም፡፡ ለአስተማማኝ ድል ለመብቃት ግን ወራሪ ጠላትን ከኦሮሚያ ምድር ጠራርጎ ማስወጣትና ሰብዓዊ መብትህን ማስከበር ብሎም በገዛ አገርህ በሰላም፣ በነፃነትና በተረጋጋ ሁኔታ ለመኖር የሚያስችልህን ሁኔታ ለማመቻቸት ኃይልህን አስተባብረህ ጠንክረህ ከመታገል ዉጭ ሌላ አማራጭ የለህም፡፡ ስለሆነም የጀመርከዉን የነፃነት፣ የእኩልነት፣ የፍትህና የአገርህ እዉነተኛ ባለቤት መሆንህን የማረጋገጥ ትግል የበለጠ እንድታፋፍም ስናሣስብህ የጀመርከዉ ትግል ከአስተማማኝ ድል በመለስ የማይቆም መሆኑን በማስገንዘብም ጭምር ነዉ፡፡
5. የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሆይ፡- በሕወሐት አቀነባባሪነትና ሁለ-ገብ ድጋፍ በኦሮሚያ ምድርና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተፈፀመዉ ወረራ በመላዉ ኢትዮጵያና በሁሉም ኢትዮጵያዉያን ላይ የተፈፀመ ወረራ መሆኑን መረዳት ይኖርባችኋል፡፡ አሁን በኦሮሚያ ምድርና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተፈፀመዉ ሕወሐት-መራሽ ወረራ በጀግንነታችን ያከሸፍነዉን የትናንቱን የ“ታላቋ ሶማሊያ” ምሥረታ ተልዕኮ ያነገበ በመሆኑ በመላዉ ኢትዮጵያና በሁሉም ኢትዮጵያዉያን ላይ የተፈፀመ ወረራ እንደሆነ ተረድታችሁ ከኦሮሞ ሕዝብ ጎን እንድትሰለፉ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ያለአግባብ የመደፈር፣ የመወረር እና የመጠቃት ወቅት አብሮ መቆም አንድነታችንን የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ አንድ ላይ መቆማችንን የማይወደዉንና የማይፈልገዉን የሕወሐት ገዢ ቡድን የሚያሣፍር ብሎም የሚያዳክም መሆኑን ተረድታችሁ ከኦሮሞ ወገናችሁ ጎን እንድትሰለፉ ጥሪያችንን ስናቀርብላችሁ ለወገናዊ ጥሪያችን አጥጋቢ መልስ እንደምትሰጡ በመተማመን ነዉ፡፡
6. ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ችግር፣ መከራና ስቃይ ዋነኛዉ ምክንያት እና ብቸኛዉ ምንጭ ሥልጣንን በሕዝብ ፍላጎት ሣይሆን በጠመንጃ አፈሙዝ የተቆጣጠረዉ ጨካኝ፣ ዘራፊና ግፈኛ የሆነዉ የሕወሐት ገዢ ቡድን ነዉ፡፡ ይህ ቡድን በመንግሥት ሥልጣን ላይ ተደላድሎ እስከተቀመጠና ሁሉንም የመንግሥት ሥልጣን በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ጠቅልሎ ይዞ ጭቆናዉን እስከቀጠለ ድረስ ለየትኞቹም ችግሮቻችን መፍትሔ፣ ለየትኞቹም ፍትሃዊ ጥያቄዎቻችን ተገቢ መልስ ልናገኝ አንችልም፡፡ ስለዚህ “በሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ” ስም በአገራችን ላይ የተፈፀመዉን ወረራ ለማክሸፍም ሆነ የሕወሐትን የጭቆና አገዛዝ ከሥር መሠረቱ ለመናድ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሙሉ በብሔር-ብሔረሰብ፣ በቋንቋ፣ በትዉልድ አካባቢ፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በሃይማኖት፣ ወዘተ ሣንለያይ እጅ ለእጅ ተያይዘን አንድ ላይ በመቆም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በአጠቃላይ፣ በመላዉ ኦሮሚያ ደግሞ በተለይ የተቀጣጠለዉን የነፃነት ትግል የበለጠ እንድናፋፍምና ለድል እንድናበቃ ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡
ነፃነት እና ፍትህ ለሁሉም!!
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ነሐሴ 2009
P.O.BOX 56224 | Washington, DC, 20040 USA | Email: OromoDemocraticFront@gmail.com | Web: www.OromoDemocraticFront.org

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar