mandag 5. februar 2018

እየታወቀ የማይታወቀዉ ወታደር!

ይህንን ሰዉ ያስታዉሱታል? ያኔ በኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ወቅት፣ ሰራዊቱ በጥላሁን ገሰሰ ሙዚቃ በስሜት በሚናጥበት ወቅት፣ ይህ ወታደር በካሜራዉ ሞጭላፊ ሌንስ ተጠለፈ፡፡ ፊቱን እያባበሰና ዓይኑን በስሜት እየከደነ ከዘፈኑ እኩል ሲዘፍን፣ ሌሎች እሱን-መሳዮች አብረዉ በ’ሱ ‹‹ስታይል›› ያንጎራጉሩ ነበር፡፡ ለመሆኑ ይህ ወታደር ከጦርነቱ በኋላ ወዴት ገባ? እንዴትስ ኖረ? ዉጊያዉ ዉስጥ ምን ያህል ተሳተፈ?…ሁሉንም እሱ ያወጋችኋል!፠፠፠፠፠፠፠፠፠
‹‹ከዘሬ ጦረኛ ነበርኩ፡፡ በልጅነቴ ጓደኞቼን በቡድን እደለድልና ሚና እሰጣቸዋለሁ፡፡ አንዱን ወታደር፣ አንዱን አዛዥ፣ አንዱን መድፈኛ አደርጋለሁ፡፡ ሁሉንም ቦታ አስይዛለሁ፡፡ ከ’ዛ መዋጋት ነዉ፡፡
‹ቱሩሩሩሩሩሩሩሩ…ቱርርርርርር…›
ምራቃችንን እየረጨን እንጮሃለን፤ እንጨቱን እንደጥይት ይዘን፡፡
‹ድዉዉዉዉዉዉ…ብዉዉዉ…›
ጉሮሮኣችን እስከሚሰነጠቅ እናጓራለን፤ የዘይቱናዉን ፍሬ እንደቦንብ ይዘን፡፡
እስከምናድግ በዚሁ ጨዋታ ቆየን፡፡ ትምህርት ቤትም መሄድ ጀመርን፡፡ ስምንተኛ ክፍል ስደርስ፣ ሰዉነቴ ደነደነ፤ ሃይለኛ ጉልቤ ወጣኝ፡፡ የሰፈሩ ሰዉ እኔን መፈራት ጀመረ፡፡ ‹ቶሎሳ መጣ!› ከተባለ፣ መንደሩ ጭር ይላል፤ ድምጽ የሚባል ነገር አይሰማም፤ የመርፌ ኮሽታ እንኳ አይሰማም፡፡ የግሩፕ ድብድቦች ላይ ፊት-አዉራሪ እኔ ሆንኩ፡፡ ፖሊሶችም በ’ኔ መፈተኑን ወድደዉታል መሰለኝ፣ ‹ቶሎሳ ዳዉድ የተባለዉን ወመኔ ከ’ነሙሉ ሰዉነቱ አምጥቶ ላስረከበ፣ የ1000 ብር ወሮታ እንከፍላለን!› የሚል ማስታወቂያ በየጊዜዉ መለጠፉን፣ ‹ስራዬ› ብለዉ ያዙት፡፡
ልክ አስራ ሁለተኛ ክፍልን ጨርሼ፣ ዉጤት በ’ምጠብቅበት ጊዜ፣ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ተቀሰቀሰ፡፡ በሃገር-አቀፍ ደረጃ ወታደር መመልመል እንደተጀመረና ዕድሜዉ ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ወጣት በሙሉ፣ መሰረታዊ ስልጠና ወስዶ ወታደር መሆን እንደሚችል ሰማሁ፡፡
ቀበሌ ሄጄ ተመዘገብኩ፤ ከተለጠፈዉ ስም ዝርዝር ዉስጥ የ’ኔ ስም ተገኘ፡፡
ወደማሰልጠኛ ካምፕ ልሄድ እንደትናንት፣ አባቴ ትከሻዬን አቅፎ መከረኝ፡፡ በለምጥ የጎበረዉ ቅንድቡ ከፍ፣ ዝቅ ይል ነበር-በየሰከንዱ፡፡
‹ልጄ! በቀ.ኃ.ስ ዘመን ወታደር ነበርሁ፡፡ ያኔ ወደኮንጎ ዘምተዉ፣ ሰላም ካስከበሩት ዉስጥም እኔ አንዱ ነበርሁ፡፡ ይህ የምታየዉ ለምጥ የመጣዉ ከዚሁ ስራ’ጋ በተያያዘ ችግር ነዉ፡፡ ስለዚህ ልጄ! ጀግና ሁን! እንደአባትህ ሃገርህን አስከብር!›
በነጋታዉ በሎንቺና ተጭኜ ወደካምፕ ሄድኩ፡፡ ወቅቱ ፈታኝ ነበር፡፡ የወታደር ዕጥረት ስለነበር፣ የለብ-ለብ ስልጠና ነበር የሚሰጡን፡፡ ሩጫዉ፣ የአካል ግንባታ ስልጠናዉ፣ የፖለቲካ ስልጠናዉ…በሙሉ አድካሚ ነበሩ፡፡ ቢሆንም፣ የአባቴን ምክር ከዳር አድርሶ የመታየቱ ህልም ስለሚወዘዉዘኝ፣ በየሰዓቱ ተነስቶ መስራቱ ላይ በርታሁ፡፡ በመጨረሻም፣ ስልጠናዉን በተሳካ መልኩ ጨረስኩ፡፡
አሁን ጊዜዉ የስምሪት ነዉ፤ ጓደኞቼ ዛላንበሳ፣ ሽሬ…ሲመደቡ፣ እኔ ግን ጾረና ግንባር ተመደብኩ፡፡ ወደአካባቢዉ ተንቀሳቅሼ፣ የአካባቢዉን መልክዓ-ምድር ተመለከትኩ፡፡ አስቸጋሪ ወጣ-ገባዎችና ተራራዎች አሉበት፡፡ ‹እዚህ ላይ ነዉ የምዋጋዉ?› አልኩ፣በልቤ፡፡ በሌላ በኩል ግን ራሴን አጀገንኩት፡፡ ‹አንተ ጀግና ነህ! የአሉላ አባነጋ ወራሽ! የ’ነደጃች ሰባጋዲስ ተከታይ! የአባቱ ልጅ! ፈርጥም! ወደፊት ተራመድ!›
ሌሊቱኑ በቅዠት ስታመስ አደርኩ፡፡ 
መደገፊያ የሌለዉ ደረጃ ላይ ስወጣ ይታየኛል፡፡ እሱን በጥንቃቄ ለመዉጣት ስጥር፣ ተንሸራትቼ ወደቅኩ፡፡ ጉዳቱ ለክፉ አይሰጥም ነበር፡፡ ታፋዬና ጭኔ በደም ጭጋግ ቢሸፈኑም፣ ወገብ አገዳዬ በትንሹ ቢጎመድም፣ ትንፋሼና ልቦናዬ አብረዉ ነበሩ፤ አልተለዩኝም፡፡ ከወድቅኩበት አፋፍሰዉ የወሰዱኝ ሰዎች እነማን እንደሆኑ፣ አሁን አላስታዉስም፡፡
ይህን ሁሉ ካለምኩ በኋላ፣ በላቦት ተጥለቅልቄ ከእንቅልፌ ነቃሁ፡፡ በረዥሙ አየር አስወጣሁና ወደቀልቤ ለመመለስ ጣርኩ፡፡ ‹ጀግንነቴ ወዴት ነህ? ናልኝ!› በልቤ ተጣራሁ፡፡ ‹አቤት!…እዚህ ነኝ!› አላለኝም፡፡ ዝምታዉ በዛብኝ፡፡ ‹ፈሪ ነኝ!› አልኩ እንደገና፤ ድምጼን ከፍ አድርጌ፡፡
‹አንተ?!› አጠገቤ የተኛዉ ሃጎስ የተባለዉ ወታደር፣ ራሱን አንሶላ ዉስጥ ደብቆ ጠየቀኝ፡፡
‹አይ!…› አልኩና ነገሩን አለባበስኩ፡፡ ሌሊቱም ተጠናቅቆ፣ ጀምበር ወጣች፡፡
ቁርስ ካደረግን በኋላ፣ ታዋቂ ዘፋኞች እንደመጡ ተነገረን፡፡ ታምራት ሞላ፣ ጥላሁን ገሰሰና መሃሙድ አህመድ ነበሩ፡፡ ተሰብስበን-ከ’ነጠብመንጃችን-ወደሜዳዉ ወረድን፡፡ ባንዱ ወታደራዊ ልብስ ለብሶ፣ የሙዚቃ መሳሪያዉን ይዞ ተዘጋጅቷል፡፡ አስተዋዋቂዉ ጥላሁን አልፍነህ ነበር፡፡ በሃይለኛዉ ጮሆ፣ የዘፋኞቹን ስም ዘረዘርልን፡፡ መጀመሪያ ታምራት ሞላ ወጣ፤ ዘፈነ፡፡ ዘፈኑ ሆድ ያስብስ ነበር፡፡ ከ’ሱ ቀጥሎ፣ ጥላሁን ገሰሰ ተከተለ፡፡ ‹እናት ሃገር ኢትዮጵያ!› የሚለዉን ዘፈን ሲጫወት፣ ሁሉም ስሜታዊ ሆነ፡፡ ከጎኔ ያለዉም፣ ከፊትለፊቴ ያለዉም፣ ከኋላዬ ያለዉም…በጠቅላላ ሁሉም፣ እንባ በእንባ ሆኖ ይዘፍናል፡፡ እኔም ሳላስበዉ አለቀስኩ፤ አባቴን አስታዉሼ፡፡ ከዛ በስሜት መዝፈኔን ቀጠልኩ፡፡ ዘፈንኩ! ዘፈንኩ!…ለካስ እየተቀረጽኩ ነበር፡፡
በዚህ መልኩ የኪነት ዝግጅቱ ተጠናቅቆ ወደነበርንበት ተመለሰን፡፡ ያን ቀን በጣም ስሜታዊ ሆኜ ነበር፡፡ የአባቴ አደራ! የሃገሬ አደራ! የልቤ አደራ!…አደራ!…አዕምሮዬ ‹አደራ› በተሰኘዉ ቃል ተሞልቶ ዋለ፡፡
ምሽቱን የሻዕቢያ ወታደሮች ሲያጠቁ አደሩ፤ እኛም በመከላከሉ ላይ አተኩረን ቆየን፡፡ ቀኑን ሙሉ ስንዋጋ ዉለን፣ አመሻሹ ላይ ድል ቀናን፡፡ አቤት የተፈጀዉ ወታደር ብዛቱ! ‹ቀጥታ ግቡ!› ተብለን ነበር የገባነዉ፡፡ በእሱ መሰረት ያለደፈጣ የገባ ወቴ ሁሉ ተመታ፤ የተወሰነዉ ተዋግቶ ድል አደረገ፡፡ ዜናዉ በሬዲዮና በተሌቪዥን ተነገረ፡፡ እኛም ወደየክፍላችን ተመለሰን፡፡ እንደገባን የአዛዦቻችንን ሽኩቻ በሰሚ-ሰሚ አወቅን፡፡ በ’ነርሱ ሽኩቻ እኛ አላግባብ መስዋዕትነትን ተቀበልን፡፡ ግን አይቆጨንም፤ ለሃገራችን ያደረግነዉ ስለሆነ፣ ምንም አይመስለንም፡፡
‹ከጦርነቱ በኋላ፣ መከላከያ ዉስጥ ስንት ጊዜ ቆየህ?› አይደል ያልከኝ? አንድ ዓመት ቆየሁ፡፡ መልቀቂያ ጠየቅኩ፡፡ የአገልግሎት ዘመኔ ታይቶ፣ ክፍያ ተከፈለኝ፤ ወጣሁ፡፡ እነ’ዛ ያከሰሩን አዛዦች ግን ‹ይቆይ!› ብለዉ ነበር፡፡ እኔ ግን ‹አልፈልግም!› አልኩ፡፡ የ’ነርሱን ዘረኝነትና አድልዎ ማየቱ ስላስጠላኝ ለቀቅኩ፡፡ በ’ዛ ላይ በጣም ተዳክሜ ነበር፡፡
…ያኔ የተቀረጽኩትን በቲቪ ስመለከት፣ ‹እንዴ!…እንደዚህ ቀጨሞ ነበርኩ እንዴ!› እላለሁ፡፡ አሁን-ተመልከተኝ’ስቲ- ቦርጫም ሆኛለሁ፣ ጠጉሬ ተመልጦ አልቋል፣ በአጠቃላይ አርጅቼያለሁ…አይ! ጎልምሼያለሁ ማለቱ ይቀላል!…በአጭሩ የቶሎሳ ዳዉድ ታሪክ ይህንን ይመስላል፡፡ ቶሎሳን እንዴት አገኘኸዉ?››
‹‹ጎበዝ ሰዉ ነዉ፤ መሰናክሎቹን በጥረትና በትጋት ያለፈ!›› አልኩ፡፡
‹‹ይሁንልህ!…እኔ እንግዲህ-አንተ እንዳ’ልከዉ ዓይነት ‹ሰዉ ነኝ!› ብዬ ራሴን አልስለዉም፡፡ ለማንኛዉም፣ አመሰግንሃለሁ!››
‹‹እኔም!››
ጨበጥኩት፤ አጁ ሻከረኝ፡፡ ጾረናን አስታወሰኝ፡፡ ከጾረና በመለስ፣ የግብርና ሰራተኝነቱንም አስታወሰኝ፡፡ ቶሎሳ ዳዉድ ባ’ሁኑ ሰዓት፣ በአንድ የግል እርሻ ልማት ድርጅት ዉስጥ ተቀጥሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ 
ምንጭ ሚኪያስ ጥላሁን

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar