lørdag 11. mai 2013

የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሀመድ ኡመር አድገናል በማለት የምናቀርበው ሪፖርት ሁሉ ውሸት ነው አሉ


ፕሬዚዳንቱ የካቢኔ አመራሮችን እና የሶህዴፓ ፓርቲ አባሎችን በመሰብሰብ እንደተናገሩት ክልሉ እንደ ለማ እንደ አደገ ተደርጎ ለመንግስት የሚቀርበው ሪፖርት ሁሉ ግምገማ ለማለፍ ተብሎ የሚቀርብ በውሸት የተሞላ ነው ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ በስሜት ውስጥ ሆነው ባደረጉት ንግግር “ እኛ እንዳደግን ፣ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደደረስን ተደርጎ በየጊዜው የሚቀርበው ሪፖርት ፍጹም ትክክል ያልሆነ ውሸት ነው። አሁን በእጄ የያዝኩት ሪፖርት እውነት ስለመሆኑ እርግጠኞች አይደለንም፤ ከአሁን በፊት ይቀርቡ የነበሩ ሪፖርቶችም እንዲሁ ናቸው። ግምገማ ለማለፍ ተብሎ በውሸት የተሞሉ ሪፖርቶች ናቸው የሚቀርቡት ” ብለዋል

ፕሬዚዳንቱ ” 10 ሚሊዮን እንስሶች ክትባት እንደተደረገላቸው ሪፖርት አድርገናል፤ ሪፖርቱ እውነት ስለመሆኑ እንኳ የግብርና ቢሮው ሃላፊው መማል ( ማረጋገጥ) አይችልም። እንኳንስ 10 ሚሊዮን 500 ሺ እንኳን ስለመከተቡ ምን ማረጋገጫ ይገኛል። ለመሆኑ ህዝቡ ይህ ሁሉ ሲከተብስ አያይም ወይ?” በማለት የሚቀርበው ሪፖርት በሙሉ ውሸት መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ አብዲ ሬዲዮ አዲስ አበባና ሬዲዮ ፋና ስለሌሎች አካባቢዎች እየዘገቡ ስለ ኦጋዴን ችግር አለመዘገባቸውንም ኮንነዋል።
“አዲስ አበባና ሬዲዮ ፋና ስለሌሎች አካባቢዎች ይዘግባሉ ፣ ነገር ግን ስለዚህ ህዝብ ችግር መዘገብ ነበረባቸው። አይዘግቡም። ማን ነበር ቃለምልልስ መስጠት የነበረበት? የወረዳ እና ዞን ሀላፊዎች ነበሩ።
አቶ አብዲ ” በክልላቸው ያሉ ባለስልጣናት በሰላም ገብተው በሰላም ማደራቸውንም እንኳ ለመንግስት ሪፖርት እንደማያደርጉ ገልጸዋል።

ኢሳት የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት የደረጉትን ሚስጢራዊ ንግግሮች ባቀረበው የመጀመሪያ ክፍል ፕሬዚዳንቱ ” ትግሬዎች፣ አማራ መልሶ ስልጣን እንዳይዝ ኦጋዴኖችን አስታጥቀው በጋራ አገሪቱን እንድንመራ ይፈልጉ ነበር፣ እኛ ግን እንደ አማራ ቆጥረናቸው ተኩስ ከፈትንባቸው፤ አማራ እና ትግሬ፣ አማራ እና ኦሮሞ መቼውንም አይታረቁም ፣ አይተባበሩም ስለዚህ የኦጋዴን ህዝብ ከትግሬ ጎን እንዲቆም፣ አማራ እና ትግሬን፣ አማራ እና ኦሮሞን አንድ አድርጎ አማራ እያለ መጥራቱን ያቁም” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

በጉዳዩ ዙሪያ የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንትን ለማግኘት ሙከራ ብናደርግም ፕሬዚዳንቱ ስብሰባ ላይ ናቸው በሚል ጸሀፊያቸው ልታገናኝን አልቻለችም።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar