torsdag 17. desember 2015

ከቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዓለም አቀፍ ህብረት የተሰጠ መግለጫ – “አገር ህዝብ እንጂ መንግስት አይደለም”





የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት የተጫነበትን የጭቆና ቀንበር ሲታገልና እራሱን ነፃ እያወጣ የኖረ ህዝብ ነው ። በፊውዳሉ የዘውድ ስርዓትም ሆነ በማርክሲሳዊው ወታደራዊ አገዛዝ ለዴሞክራሲና ለህግ የበላይነት በብዙ ታግሏል ። የሚገጥሙትን የአስተዳደር በደሎች ጐዳና ላይ በመውጣት ብሶቱን ሲያሰማ የኖረ ቢሆንም እንደዚህ ዘመን ግን የመከላከያ ሰራዊቱ በአልታጠቀ ሰላማዊ ህዝብ ላይ አልሞ ሲተኩስና የጅምላ ፍጅት ሲፈፅም ታይቶ አይታወቅም ።

በመሰረቱ የአገር መከላከያ ሰራዊት ከህዝቡ አብራክ ውስጥ የተገኘ እንደ መሆኑ መጠን የህዝቡ ብሶትና በደል የእራሱም በደል ሊሆን ይገባዋል ። የተመሰረተበት ዋና ዓላማም የአገርን ዳር ድንበር ማስከበርና የህዝብን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ነው ። ይሁን እንጂ አሁን በስልጣን ላይ ያለው የህውሃት/ኢህአዴግ ስርዓት ህዝቡን በዘር በመከፋፈል አገራችንን ወደ አደገኛ ብጥብጥና ፍጅት እየወሰደ ሲሆን ሰራዊቱም ብሶቱን ለማሰማት ወደ ጐዳና በወጣ ያልታጠቀ ሰላማዊ ህዝብና ገና አድገው ያልጨረሱ ወጣት ተማሪዎች ላይ ዓልሞ በመተኰስ አሰቃቂ ፍጅት እየፈፀመ ነው ።

የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዓለም ዓቀፍ ህብረት የህውሃት/ኢህአዴግ ስርዓት ከህዝብ ፈቃድ ውጪ ከሱዳን ጋር የሚያደርገውን የድንበር መካለል ፣ የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ በህዝባችን ላይ እየፈፀሙ ያሉትን የጐዳና ላይ አሰቃቂ የጅምላ ፍጅት አጥብቆ ያወግዛል ።

በመሆኑም የመከላከያ ሰራዊቱም ሆነ የፌደራል ፖሊስ መንግስት አላፊ ፣ አገርና ህዝብ ግን ሁልጊዜም ቋሚ መሆናቸውን በማስታወስ በገዛ ወገናቸው ላይ የሚያደርሱትን የጅምላ ፍጅት በማቆም ከህዝቡ የነፃነት ትግል ጐን በመሰለፍ ህዝባቸውን ከማንኛውም ጥቃትና አደጋ እንዲታደጉ ጥሪ ያቀርባል ።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar