torsdag 11. januar 2018

ትግላችን የችግሩ ስር የሆነዉን ስርዓቱን ማስወገድ ላይ ያትኩር

ዶ/ር አበራ ቱጂ
በእራቱ የኢህአዲግ ድርጅት መሪዎች የተሰጠዉን ረጂም መግለጫ በጥሞና ተከታተልኩ። አራቱም ባለስልጣኖች አሁን ኢትዮጵያ ለገባችበት የፖለቲካ ቀዉስ ዋናዉ ምክንያት ራሳቸዉ የኢህአዲግ ባላስልጣናትና የነሱም የአመራር ዉድቀት ያመጣዉ መሆኑን ገልጸዋል።  እንዲሁም በኢህአዲግ አመራሮች ዉስጥ ዲሞክራሲያዊ አሰራ እንዳልነበረ፤ በዚያም የተነሳ በህዝቡና ተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ ላይ በተለያየ መንገድ አፈናና ማኮላሽት ጭምር ይፈጽሙ እንደነበረ ገልጸዉልናል።  ለህዝቡ የሚገልጹት ጉዳይ ታአማኝነት እንዳልነበረውም አቶ ሃይለማሪያም የአሰፋንና የእናቱን ታሪክ በመጥቀስ ነግረዉናል። በዉስጣቸው ያለው ችግር፣ ከግል ከስልጣን ጥም የተነሳ እንደሆነ፣ በዚህም በመቧደን አንዱ አንዱን ለማጥፋት ይሰሩ እንደነበር፣ የግል ሃብት ለማከበትም ሲሉ ኮንትሮባንድ አንዳስፋፉ የመሳሰሉትን ሁሉ ዘርዝረዋል። ባለስልጣኖች፣ ያሚመሩበት ስርዓትና የፈጠሩት የጎሳ ፈደራሊዝም ግን ምንም ችግር አላመጣም፤ ችግሩ እኛው ራሳችን ብቻ ነን፣ የምንከተለው መርህና ስርዓት ፍጹም ትክክል ነዉ ይሉናል። ይህ ሁሉ ቀዉስና የሰዉ እልቂት የመጣዉ በነሱ መሆኑን ቢገልጹም አንድም ሰዉ እንኳ ተጠያቂ ሁኖ ለፍርድ ሲቀርብ አላየንም።  የችግሩን ዋና ምንጭ በትክክል  ለመመርመርና ለመለወጥ ፍላጎቱ የላቸዉም። ጉዳዩ ጊዜ ለመግዛት የተደረገ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ነው።
የችግሩ ምንጭ ራሳቸው መሆናቸዉን ማመልከታቸው ባልከፋ፤ ነገር ግን አሁንም ከኛ ዉጭ ለኢትዮጵያ ህዝብ አማራጭ የለም እያሉን ነው። የህዉሃት-ኢህአዲግ ባለስልጣናት ብዙ ጊዜ እንደሚናገሩት ድርጅቱ እንደእባብ ነው።  እባብ ቆዳዉ ሲያረጅ፣ ያረጀዉን ቆዳ ገልፍፎ ጥሎ፣ ለተመልካች አዲስ መስሎ ብቅ ይላል። አሁን በኢትዮጵያ ላይ ለሃያ ስድስት ዓመታት ይህን ሁሉ ግፍ ከፈጸሙ በኋላ አሁንም እንግዛችሁ፣ እንጋልባችሁ ይሉናል።  የህዉሃት-ኢህአዲግ መሪወች አሁንም ከአንድ መቶ ሚሊዮኑ ኢትዮጵያዊ ዉስጥ ከኛ ዉጭ አገር መሪ ሊኖር አይችልም እያሉን ነዉ። ከኛ የተሻለ አዋቂና ለአገር አሳቢ የለም ማለታቸዉ ነው። ይህም ህሊና ከማጣትም ያለፈ፣ በህዝብ ሰቆቃ መሳለቅ ነው። መግለጫቸው ከምንም ነገር በላይ የሚያሳየው ለአገሪቱና ለህዝቡ ያላቸዉን ጭንቀት ሳይሆን፣ ይፋ የወጣዉንና ያስፈራቸዉን፣ በዉስጣቸው ያለዉን ልዩነት እንዴት አጥፍተው አሁንም የተለመደዉን የግፍ ስራቸዉን ለመቀጠል መዘጋጀታቸዉን ነው።
ኢትዮጵያዊያን ልንጠይቀዉ ያሚገባ አንድ ዋና ጥያቄ አለ። ለመሆኑ ህዉሃት-ኢህአዲግ አገር አስገንጥሎ፣ የኢትዮጵያን የባህር በር ዘግቶ፣ ንጹህ ዜጎችን ፍትህን ስለጠየቁ በአነጣጣሪ ተኳሾች እየገደለና፣ የተለየ ሃሳብ ያላቸዉንና የመንግስትን ስህተት ያሳዩትን ሁሉ አስሮ እያሰቃየ፣ እያኮላሸ፣ ሊወራ የማይገባው ነዉር በፖለቲካ እስረኞች ላይ እየፈጸመ፣ አዉሮጳዊያን ቅኝ ገዢወች በፈጠሩት ዘመን ያለፈበት ስልት፣ ዜጎችን በጎሳና ቋንቋ ከፋፍሎ እያጫረሰ፣ ይህን ሁሉ ስቃይ በህዝብና በአገር ላይ እያደረሰ፣ እንዴት ከእሩብ ምዕተ ዓመታት በላይ አገሪቱንና ህዝቡን መግዝት ቻለ? አሁንስ እንዴት በዚሁ የግፍ አገዛዙ ለመቀጠል ድፍረት አገኘ?  የተማመነው በመሰረተው መሰሪ ስርዓት በመሆኑ ነው።
በኢትዮጵያችን አሁን የተፈጠረው ቀዉስ ዋናው መንስዓኤ የህዉሃት-ኢህአዲግ መሪወች እንደሚሉት የነሱ የአመራር ዉድቀት ሳይሆን፣ ለህዉሃት-ኢህአዲግ ደም፣ አጥንትና ህይወት የሆነዉና የተመሰረተበት ጨካኝ ስርዓት ነው።  የችግሮቹ ዋናው መንስዓኤው ከሰወቹ በላይ የሆነው ስርዓቱ ነው።
በስርዓቱ ላይ ያላነጣጠር የመፍትሄ ሃሳብ፣ ችግሩን ከስር መሰረቱ ለመንቀልና ችግሩ ተመልሶ እንዳይመጣ ለማድረግ አይችልም። ወያኔ ኢህአዲግ፣ የችግሩን ዋና ስር ወይም መሰረት፣ የተወሰኑ ባለስልጣኖች የፈጠሩት ነው በማለት ብቻ፣ የተወሰኑ ባለስልጣኖችን በማተካካት የጥገና ለውጥ በማድረግ አሁንም አረመኒያዊ አገዛዙን አጠናክሮ ለመቀጠል እየተዘጋጀ ነው።
ችግርን ለማስወገድ፣ የችግሩን ስር (root cause) በዘዴ መመርመርና በትክክል መለየት ያስፈልጋል። የዚህም ጽሁፍ ዓላማ ይህ ነው። አሁን አገራችን የገባችበትን ችግር ምን አመጣዉ የሚለውን ጥያቄ በትክክል መመለስ ይገባል። የችግሩ ዋና ስር፣ የችግሮች ሁሉ መሰረት ሆኖ፣ ችግሮች ወይንም ችግሮችን የሚያስከትሉ ሰንሰለታዊ ሁነቶችን የሚቀሰቅስና፣ ልናስውግደው የሚገባው የችግሮችን ስርዎ-መንሴ ነው። ይህን የችግር መንስዔ በአግባቡ ካስወገድነው የፈጠራቸው ችግሮችና፣ ችግሮቹን ተከትለው የሚመጡ መጥፎ ወይም የማይፈለጉ ሁነቶች ለዘለቄታው ይጠፋሉ ወይም ተመልሰው አይመጡም።  የችግሩን ዋና ስር ሳናጠፋ ሰበብ (triggering event) ወይንም ከላይ ከላይ ያሉ ችግሮች ወይንም የዋናዉን ችግር ምልክቶች ወይም መገለጫወች (manifestations or symptoms) ላይ ብናተኩር፣ ችግሩ ተመልሶ መምጣቱ ወይንም ሌላ መልክ ይዞ ተጠናክሮ መከሰቱ አይቀርም።
በሌላ በኩል፣ ይህ አገራችን የገባችበትን ችግር፣ ኢትዮጵያ በተሻለ አቅጣጫና አስተዳደር ለመመራት የምትዘጋጅበት ጥሩ እድልም ይዞልን እንደመጣ በመቁጠር፣ ይህን የቁጣና የቁጭት ሃይል ወደ አዎንታዊ ጉልበት በመቀየር፣ ከችግሩ አዙሪት መውጣት እንድንችል የአገራችንን የፖለቲካ ስርዎ-ችግር በማስወገድና፣ አገራችን የህግ የበላይነት የሰፈነባትና የቂም-በቀል ፖለቲካ የማይኖርባት፣ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት አስተዋጾዖ የሚያደርግባት፣ ሆና እንድትቀጥል መስራት አለብን።
አሁን ያለውን ችግር ከስፋቱና ጥልቀቱ የተነሳ በተወሰኑ ዓርፍተ ነገሮች መግለጽ ያስቸግራል።  ዋናው ችግር ግን ኢትዮጲያዊያን እንደ አንድ በአገሩ በነጻነት ሰርቶ የመኖር መብት እንዳለው ሰብዓዊ ፍጡር ሳይሆን፣ የወያኔ መንግስትና የፈጠረው ስርዓት፣ ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ ያለፍርድ ይገድሏቸዋል፣ አስነዋሪ ሰቆቃ ይፈጽሙቧቸዋል፣ ንብረታቸውን ይቀማሉ፣ እንዳይናገሩና አንዳይደራጁ ያፍኗቸዋል፣ የወያኔን ብልሹ መርህ፣ ‘ፖሊሲ’ ወይም ‘ዶክትሪን’ እንዲቀበሉ ያስገዲዷቸዋል።  ሰወች በሰብዓዊ ሃይላቸው ተጠቅመው በነጻነት ማሰብ፣ መስራትና ማደግና ይከለከላሉ። በአጭሩ የኢትዮጲያ ዜጎች በወያኔወችና  ወያኔወች በፈጠሩት ስርዓት ተፈጥሯዊና ህጋዊ መብታቸው ተገፎ እንደእንሰሳ ተቆጥረው ወንጀል እየተፈጸመባቸው ነው።
የዚህን የአገራችንን ዘርፈ-ብዙ ችግር ምንጩን ለማወቅ “ችግሩ ለምን ተፈጠረ ወይም ምን አመጣው’ በማለት የችግሩን ስር እስከምናገኝ ተከታታይ ጥያቄወችን ማንሳት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል አንድ የችግሩን ሁነት (event) እንመልከት።  በሰላም የመብት ጥያቄ ያቀረቡ ሰለማዊ ሰልፈኞች ለምን በመንግስት አነጣጥሮ ተኳሾች ይገደላሉ?  ለዚህ የሚጠበቀው መልስ የመንግስት ባላስልጣን የግድያ ትዕዛዝ ስለሰጠ ነው እንበል። ይህን የግድያ ትዕዛዝ የሰጠ የመንግስት ባላስልጣን ከቦታው ቢነሳ፣ ሰለማዊ ሰልፈኞችን መግደል ያቆማል ወይ? ለዚህ ምሳሌ ማየት ያለብን፣ አቶ መለስ ዜናዊ የ1997 ምርጫ ተክትሎ ግድያ አዘው ወደ ሁለት መቶ የሚሆኑ ሰለማዊ ሰልፈኞችን አዲስ አበባ ዉስጥ ብቻ በግፍ አስገድለዋል። እሳቸው በሞት ሲለዩ የተኳቸውና እግዚአብሄርን ይፈራሉ ይባል የነበሩት አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ ህዉሃትን ለማስደሰት፣ ተመሳሳይ ትዕዛዝ በመስጠት በመቶወች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎችን እያስገደሉ ነው።
የክልል መሪወችም ሆነ የተውሰኑ የጦር ጄኔራሎች የወያኔን አጥፊ ተልዕኮ ከፈጸሙ በኋላ ተተክተው አይተናል።  የህዝብ ሃብት ዘረፉ የተባሉና፣ በዘረኛ ቅስቅሳ ህዝቡን በጠላትነት ያነሳሱ የነበረው ጠቅላይ ሚኒስተር፣ ተተክተው አይተናል።  ሰወቹን በመቀያየር መንግስት የበለጠ ችግር ሲፈጥር እንጂ ሲያሻሽል አልታየም። የይምሰል ህግም ማውጣት ችግሩን አልፈታም።  ሰወችን በመቀየር፣ የማሰቃያንና የማኮላሻን ቦታ በመቀየር ብቻ ችግሩን ማጥፋት ወይም ተመልሶ እንዳይከሰት ማድረግ አይቻልም። በመሆኑም የችግሩ ምንጭ የተወሰኑ ስልጣን ላይ ያሉት ሰወች ወይንም የህግና፣የብልሹ አስተዳደር፣ የሙስና፣ የህዝብ ንብረት ምዝበራ፣የችሎታ ማነስ ወይም የአፈጻጸም ጉድለት አይደለም። እንዚህ ስርዎ-ችግሩ ያመጣቸው የችግሩ ምልክቶች ወይም ሁነቶች ብቻ ናቸው።
ዛሬ የሚገድሉትና የሚያስገድሉት የወያኔ ባለስልጣኖች ከስልጣን ቢወገዱና የመሰረቱት ዘረኛ፣ አድሏዊና አፋኝ ስርዓት (system) እስካለ ድረስ፣ ሌሎች በቦታዉ ተተክተዉ፣ ችግሩ ይቀጥላል፣ ወይንም መልኩንና ሰወችን እየቀያየረ በድጋሜ ይመጣል። ስርዓቱ የወያኔን መሰሪና በጥላቻ ላይ የተመሰረተ ተልዕኮ ለመፈጸም ሲባል በልዩ ሴራ የረቀቀ መዋቅር ተዘጋጅቶለታል። ስርዓቱን እንዳይወድቅ ደግፈው የያዙ፣ የተሳሰሩና እርስ በርሳቸው የሚደጋገፉ፣ ተደጋግፈዉም የከፋ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያመጡ ብዙ ምሶሶወች አሉት።  ስርዓቱን ቀጥ አድርገው የያዙት፣ እያደሱና እየጠገኑ ያቆሙት የሚከተሉት የስርዓቱ ዋልታወች ናቸው።
  1. በዘርና ቋንቋ ከፋፋይ መርህ፤ የዚህ ስርዓት የመሃል ምሰሦ የሆነው አገሪቱን በዘርና ቋንቋ መከፋፈሉና የፈጠረውን የዘራው የዘር ወይም የጎሳ ጥላቻ ፖለቲካ ነው።  ይህ ወያኔወች የኢትዮጲያን ታሪክና አንድነት በማጥፋት፣ ህዝቡን ለመቆጣጠር ያመጡት የጎሳ ፖለቲካ ለወያኔው ስርዓት ከሁሉም በላይ መድህኑ ሁኗል። ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን ችግር በጋራና በሰለጠነ መንገድ ተወያይተው፣ መክረዉና ተቀራርበው እንዳይፈቱ፣ በአገር አቀፍ ጉዳይ ላይ ከማትኮር ይልቅ በመንደር ድንበርና በጥላቻ ፖለቲካ እንዲጠመዱ አድርጓቸዋል።
  2. አፋኝ ጦርና የስለላ ድርጅት፤ ስርዓቱን የሚቃወሙትን ሁሉ ለማፈን፣ በወያኔ ታማኞች በበላይነት የሚመራ አገርና ህዝብን ሳይሆን፣ ወያኔወችንና አፋኝ ስርዓቱን የሚጠብቅ የጦርና የፖሊስ ሃይል አለ። የዜጎችን ዕለት-ከዕለት ህይወት ለመቆጣጠርና ለመሰለል፣ የሃሳብ ልዩነት ያላቸዉን ተቃዋሚወች ለማጥፋት ወያኔወች ከሚመሩት የስለላ ድርጅት በተጨማሪ፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩና ቴሌኮሙኒኬሽን የመሳሰሉትን ለማፈኛነት ይጠቀማል ።
  3. በፖለቲካ ድርጅቱ ቁጥጥር ስር ያለምጣኔ ሃብትና የዕምነት ተቋማት፤ስርዓቱን በገንዘብ ሃይል ለመደገፍና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በመስጠት፣ ደጋፊውችን ለማብዛትና፣ ተቃዋሚወችን ለማዳከም፣ የኢኮኖሚ አውታር የሆኑትን የአገሪቱን መሬት፣ ማአድን፣ ባንክ፣ የንግድ ተቋማትን እንደ አየር መንገድ፣ ኤፈርት፣ ሜቴክ፣ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ መብራት ሃይልና የመሳሰሉትን በቁጥጥሩ ስር አስገብቷል። የመንግስት መስሪያ ቤቶችን በደካሞችና በወያኔ ደጋፊወች ብቻ በመሙላት፣ ዜጎችን በህዉሃት ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ በማድረግ፣ የስርዓቱን እድሜ ለማራዘምና የዜጎችን ዕለት ከዕለት ኑሮ ለመቆጣጠር ይጠቀምባቸዋል። የዕምነት ድርጅቶችንም እንደዚሁ በወያኔ ታማኞች እንዲመሩ በማድረግ ህዝብ ሲበደል አንዳይነሱና፣ ግፍ ሲፈጸም እዉነትን እንዳይናገሩ አድርጓል።
  4. ተቃዋሚወችን የሚያጠፋየይስሙላ የፍትህና የምርጫድርጅቶች፤ ወያኔ ካለው የአንድ-ድምፅ ፓርላማ በተጨማሪ ለይስሙላ ያሉ የፍትህ መስሪያ ቤቶች፣ የወያኔን ስርዓት “ህጋዊ” ጠለላ ይሰጣሉ። አፋኝ ህጎችን እንደ ጸረ-ሽብርና፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ህግ በማውጣት፣ መንግስትን የሚቃወሙትንና የመብት ጥያቄ ያነሱትን በእስር ያሰቃያል፣ ሰቆቃ ይፈጽማል። ዜጎችን የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት መብታቸውን ይነፍጋል። ለይምሰል ያክል ምርጫ ያካሂዳል፣ ከወያኔ በስተቀር ተመራጭ እንዳይኖር ያደርጋል። ምርጫን ያጭበረብራል።
  5. አማርጭ ሃሳብ የሚዘጋና ጥላቻየሚነዛ የመገናኛ ብዙሃን፤ወያኔወች የሚመሩዋቸዉን በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የመገናኛ ብዙሃንን፣ በህዝቡ መሃል ጥላቻን ለመዝራት፣ ውሸትን ለማሰራጨት፣ ህዝቡን የመንግስትን አቋም ብቻ እንዲከተል ለማድረግ፣ አማራጭ ሃስቦችን ዝግ ለማድረግ ይጠቀምባቸዋል። የግል መገናኛ ብዙሃንን፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን፣ የዝቡን ችግርና በደል እንዳያሳውቁ ፣ህዝቡን እንዳያነቁ ያጠፋል። የትምህርት ተቋማትን ወጣቱን በዘር ለመከፋፈል፣ ሰላዮችንና ጆሮ-ጠቢወችን በመሰግሰግ፣ የጎሳ ጥላቻ ማስተማሪያ በማድረግ፣ የአዕምሮ ነጻነት እንዳይኖር በማፈን፣ የወያኔ ካድሬ መፈልፈያ አድርጓቸውል።
እነዚህ እርስ በእርስ የሚደጋገፉናየተሳሰሩ ምሶሶወችና፣ ምሶሶወቹየቆሙለት መሰሪና አገር አጥፊተልዕኮና መርህ፣ ምሶሶወቹ የቆሙበት መዋቅሩና፣ ስርዓቱን የሚመሩትናየሚያገለግሉት ሰወች፣ በአንድተዋህደውና ተቀናጅተው ነው አሁንየደረስንበትን ችግር የፈጠሩት።ለዚህም ነው ችግሩ ስርዓታዊ(systemic) ነው፣ ወይም የችግሩ ዋና መንስዔ ስርዓቱ ነው የምንለው።  
ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ያለው አደገኛ ሁኔታ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ድርጅት ማንፌስቶ እንደሚገልጸው ወያኔውች በደደቢት የጀመሩት በይበልጥ በአማራ ላይ በአላቸው ጥላቻ ላይ የተመረኮዘ በልዩ ተንኮል የተዘጋጀ፣ ከፋፋይ፣ አድሏዊና አፋኝ ስርዓት ነው። አሁን ያለው ችግሩ በተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ የተፈጠረ ወይም በተናጠል የሚታይ አይደለም። በአገራችን ያለው ችግር ይህ ስርዓት እስካለ ድረስ ይቀጥላል። የችግሩ ስርዎ-መንስዔ (root cause) ይህ ወያኔ የፈጠረው ስርዓት ነው። የችግሩን ወቅታዊ ሁነቶች፣ ለምሳሌ ሰዎችን መቀየር፣ አንደ የአዲስ አበባ ድንበር መስፋፋት ችግር ወይም የወልቃይት ጉዳይ ለጊዜው መልስ በመስጠት ችግሩን ለዘለቄታው መፍታት አይቻልም።
ወያኔወች ዛሬ የፖለቲካ እስረኞችን፣ ምህረት ጠየቁ እያሉ፣ ካደነዘዙና የማይድን የአዕምሮ ሰቆቃ ከፈጸሙባቸው በኋላ ቢፈቷቸውም፣ ነገ ደግሞ ባለተራወችን ያስራሉ። ዛሬ ግድያቸውን  ለጊዜው ቢያቆሙ፣ ከተውሰነ ጊዜ በኋላ ይጀምራሉ። ወያኔወች በሃያ ስድስት ዓመታት አገዛዛቸው ያሳዩን ሃቅ ይህን በደል፣ ተራ በተራ፣ መርሃ-ግብር አውጥተዉለት፣ በተለያየ የህብረተሰቡና የአገሪቱ ክፍል ላይ መፈጸማቸውን ነው። ከሁሉም በላይ አገር ሊመሩ የሚችሉ ዜጎችንና ድርጅቶችን ገና ብቅ ሲሉ ያጠፋሉ። ዜጎችን ሰላማዊ አማራጮች ሁሉ እንዲዘጉባቸው በማድረግ ተስፋ በማስቆረጥ ወደጦርነትና ሃይል አማራጭ ይገፋሉ። በአገሪቱ የዘር ጥላቻን ይዘራሉ።  እኛ ካልገዘናችሁ ህዝቡም አገሪቱም ትጠፋለች በማለት ህዝቡን ያሸብራሉ። በመግደል፣ በመዝረፍና በማሸበር ረግጦ መያዝ ከአገዛዙ ስርዓት እምነትና ተልዕኮ የመጣ እንጂ የተወስኑ አምባገነኖች ብቻ ፍላጎት አይደለም።  ሰወቹ ቢቀያየሩም፣ ይህ ስር የሰደደና በተንኮል የተዘጋጀ አፋኝ ስርዓት እስካለ ድረስ፣ ባለው አጥፊና የማያፈናፍን የድርጅት ባህል (organizational culture)፣ በስፋት በተደራጀው የስለላ ድርጅትና ሌሎች ከላይ የተጠቀሱ ዋልታወቹ ጋር በመሆን፣ አዲስ የሚቀላቀሉትን ግለስቦች ባህሪ ስርዓቱ በተቃኘበት መንገድ ይቀርጸዋል።
ሰላማዊ ሰልፈኞችን ለመግደል ትዕዛዝ የሚያስተላልፉት ወያኔወች የተለመደ ድራማቸውን ይዘው ቀርበዋል። የታዘዙትም የክልል ባለስልጣኖች ትዕዛዙን ተቀብለዋል። ወያኔወች “በጥልቀት እንታደሳለን” እያሉ የሚያላዝኑት፣ ችግሩን የሚያዩበት መነጸራችው ያው ሃያ ስድስት ዓመታት የገዛን ወያኔ የዘረጋው ዘረኛዉና መሰሪዉ ስርዓት ነው። የሚመሩበትም ፍጹም የተማከለ፣ ሚስጥራዊና ከፋፋይ፣ የማያፈናፍንና፣ በተወሰኑ የህወሃት ሰወች የሚመራ፣ ስርዓት ነው።
ወያኔወች ፈታኝ ወቅት ሲያጋጥማቸው በሚስጥር በመወሰን፣ ከስራቸው ያስጠጓቸውን ተለጣፊወች ተጠያቂ ያደረጉ ይመስላሉ፤ ወይንም አንዳንዶቹን ሆዳሞች የመስዋዕት በግ ያደርጓቸዋል። በረከት ስምኦን ባለፈዉ ዓመት ይህን ነበር ያለው።  “በኢትዮጲያ ዉስጥ ፈደራል የሚባል ህዝብ የለም ክልላዊ ህዝብ ነው ያለው ኢህአዲግ ለብልሽት ብሄራዊ ካባ ልንደርብለት አይገባም የሚል በጣም ጠንካራ አቋም ነው ያለው፣ በጣም ጠንካራ፣እያንዳንዱ ክልል፣ እያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት የራሱን ብልሽት ራሱ ይታገል።”  ይህም ወንጀሉን የሚፈፅመዉን የፌደራል መንግስትና ወያኔ ከደሙ ንጹህ እንደሆነ በማቅረብ፣ አፋኙን ስርዓት ለማዳንና ለማጠናከር የተወሰኑ የአማራና የኦሮሞ ተለጣፊ መሪወችን፣ ህዝባቸውን ካስጨፈጨፉ በኋላ ሊወረዉሯቸው መሆኑን ሲገልጽ ነበር። የአሁንም ድራማ ከዚያ የተለየ አይደለም።
የወያኔ ኢህአዲግ ሰወች ማሰብና መጓዝ የሚችሉት ይህ ስርዓት ባሰመራላቸው ቀጭን መስመር ብቻ ነው።  አንዳንድ የሚባንኑ የኢህአዲግ ሰወች ቢኖሩም እንኳ፣ ከዚህ ከተሰጣቸው፣ ነገሮችን የመመልከቻ ዘይቤ (paradigm) ዉጭ ሊያስቡ አይችሉም። ሌላ አዲስ ነገር እንዳያስቡ ይህ ስርዓት አፍኖና አስሮ ይዟቸዋል። በወያኔ የአዕምሮ ማደንዘዣና አስገዲዶ ማሳመን (indoctrination and brainwash) ያልተረቱ እንደ አቶ ለማ መገርሳ ያሉ አንዳንድ የስርዓቱ አባላት ቢኖሩም እንኳን፣ ከዚህ ወጭ ማሰብ ከጀመሩ ስርዓቱ በተለያየ ተንኮል ያጠፋቸዋል። ይህ የችግሮቹ ሁሉ ዋና ምንጭ የሆነ ስርዓትና፣ የችግሩን ሁነቶች የፈጠሩት ግለስቦች፣ ችግሩን በፈጠሩበት አስተሳሰባቸው፣ አገራችንን አሁን ከገባችበት የፖለቲካ ምስቅልቅል ሊያወጧት አይችሉም።  እንዲያውም የህወሃት መንግስት ተጠናክሮ ለመቀጠል ይህን አጋጣሚ ይጠቀምበታል።
መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በአለባት ኢትዮጵያ ይህን እየገደለ፣ በሰቆቃ የገዛንን ስርዓት ተጭኖብን እንድንቀጥል የሚያስገድደን ምን ሁኔታ አለ?  ወያኔ ለህዝብ ባለው ንቀት፣ ይህን ሁሉ ወንጀልና ግፍ በረቀቀ ዘዴ አቀነባብሮ እየፈጸመ፣ አሁንም ለኢትዮጵያ ከኔ በላይ አሳቢ የለም፣ መፍትሄዉም እኔዉ ነኝ ይለናል። ከዘረፉት በተረፋቸው የብድርና እርዳታ ገንዘብ መንገድ ሰርተናል ከሆነ የሚሉን፣ ፋሺስት ጣሊያንም እየጨፈጨፈን በአምስት ዓመታት የበለጠና እስካሁን እያገለገለ ያለ መንገድ ሰርቷል።
የበደለ ቢረሳ የተበደለ አይረሳም። የኢትዮጲያ ህዝብ በዚህ ስርዓትና በወያኔ የደርሰበትን ግፍ ህሊና ያለዉ ሰዉ ፍጹም አይረሳዉም።  አገር ለመገንጠልና ለማስገንጠል አቅዶ የተነሳው የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር (ህዉሃት)፣ ብዙ ሺህወችን ጨፍጭፎና አስጨፍጭፎ ስልጣን ላይ ወጥቶ፣ በኢትዮጲያ ላይ ያደረሰውን በደል በዚህ አጭር ጽሁፍ ጨርሶ መዘርዘር አይቻልም። በመሃል አዲስ አበባ የተገደሉት እነ አሰፋ ማሩ፣ የእነ ሽብሬ ህይወት በግፍ የተጨፈጨፉት የጋምቤላ፣ ኦሮምያ፣ሲዳሞ፣ ኡጋዴን፣ አዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወገኖቻችን ደም አሁንም ወደሰማይ ይጣራል።  በገደሉት ልጇ አስከሬን ላይ አንድትቀመጥ አስገድደው የደበደቧትን የወለጋዋን እናት ሰቆቃ እግዚአብሄር ያያል። በወያኔ እስር ቤት የሚሰቃዩና የተገደሉ በሺወች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን፣ የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች እምባ ወደአምላካቸው ይፈሳል። ይህንና ሌሎች ተዘርዝረው የማያልቁ በደሎችን የፈጸመብንን ስርዓት ተሸክመን የምንጓዝበት ምን ምክንያት ሊኖር ይችላል? የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ ስርዓትና፣ ከህዉሃት-ኢህአዲግጋር አልቆረበም። በቃ።
አሁን ለደረስንበት የፖለቲካ ችግርና ዋናዉ መንስዔዉ ይህ የወያኔ አፋኝና ጨፍጫፊ ስርዓት ነው። ይህ ስርዓት በኢትዮጲያ ህዝብ ላይ የፈጸመው ወንጀል ራሱን ገፍቶ ሊያጠፋው ተቃርቧል። ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጲያው በዘር በሃይማኖት ሳይከፋፈል በአንድ ላይ ተባብሮና ተነስቶ ይህን ግፈኛ ስርዓት ያስውግድ። ከዛ ዉጭ በችግሩ ምልክት ወይም እዚህም-እዛም ያሉ ግለሰቦች ላይ ያተኮረ፣ ያዝ-ለቀቅ የሆነ ትግል ወያኔወች የመሰረቱትን ስርዓት ዕድሜ ያራዝማል። ወያኔና ስርዓቱ አንገፍግፎናል። ይህ መሰሪ ስርዓት ፈርሶ በህግ የበላይነት የሚመራና፣ ለሁሉም ዜጎች መብት የቆመ ስርዓት መመስረት አለበት። ትግላችን የጥላቻንና የመከፋፈልን ፖለቲካ የሚዘጋና፣ የችግሩ ስርዎ-መንሰዔ ላይ ያተኮረ ይሁን። የኢትዮጲያ ህዝብ የአጋዚን ‘ስናይፐር’ ሳይፈራ መስዋዕትነት እየከፈለ ያለው፣ የተወሰኑ ትንንሽ ሌቦችን ከስልጣን ለማባረር ሳይሆን፣ ሃያ ስድስት ዓመታት እየጨፈጨፈ የገዛንን ስርዓትና በላዩ ላይ የሰፈሩትን ወንጀለኞች እስከመጨረሻዉ ለማስወገድ ነው። ይህን ስርዓት ለመጣልና ትግሉን ከግብ ለማድረስ፣ ኢትዮጵያዊያን በመተባበርና፣ ጥቃቅን ልዩነታቸውን ወደጎን በመተው፣ በአንድ ላይ ተነስተን የችግሩ ስርዎ-መንሰዔ  ላይ የተቀነባበረና ዘርፈ-ብዙና ስልታዊ እርምጃወችን ልንወስድ ይገባል። ይህ ህዉሃት የመሰረተዉ አፋኝና ከፋፋይ ስርዓት መወገድ አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብ ክዚህ አስከፊ ስርዓት እስር ነፃ መዉጣት አለበት።
አንድነት ሃይል ነው

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar