søndag 1. juni 2014

ድምፃዊ ጌዲዮን ዳንኤል ‹በቅድሚያ እግዚአብሔርን በመዝሙር ለማመስገን እፈልጋለሁ›


የዛሬ 11 ዓመት ገደማ የመጀመሪያ አልበሙን ባወጣ ማግስት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከዳንሰኞች ጋር ታጅቦ አንድ መልከ መልካም ወጣት ማቀንቀን ሲጀምር ከአይን ያውጣህ ተብሎ ነበር፡፡ ይህ ወጣት ድምፃዊ ጌዲዮን ዳንኤል ነው፤ ጌዲዮን ለአምስት ዓመታት ያህል የለፋበትን አዲስ አልበሙን በኤልያስ መልካ አቀናባሪነት ይዞ የዛን ጊዜ ብቅ ሲል የሙዚቃ አድማጩን ጆሮ በዛ ደረጃ ይቆጣጠራል ብሎ እሱም ራሱ አልገመተም ነበር፤ ግን ሆነ፡፡ በ1985 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ካሳንቺስ በሚገኘው ወረዳ 15 ቀበሌ 19 አዳራሽ ውስጥ ከእድሜ እኩዮቹ ተለይቶ መድረክ
ላይ ወጥቶ እንዲዘፍን ዕድል ሲሰጠውና ‹ግጥሙ ከዕድሜህ ጋር አይሄድም› ተብሎ
በሌላ ዘፈን እስኪቀየርበት ጊዜ ድረስ የቴዎድሮስ ታደሰን ዘፈን ለመዝፈን ነበር የተዘጋጀው፡፡ አድናቂውም ነው፡፡ ሁለት አልበሞችን እና ሌሎች በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ዘፈኖችን ለአድማጭ ያቀረበው ጌዲዮን ዳንኤል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከሙዚቃ ሥራ ርቆ ሰሞኑን ‹አለሁ› ብሏል፡፡ የሙያ ጓደኞቹም አለኝታነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ጌዲዮን ስላሳለፈው ህይወትና ውጣ ውረድ እንዲህ ተጨዋውተናል፡፡
ቁም ነገር፡- ድምፃዊ ጌዲዮን በቅድሚያ ጥሪያችንን ተቀብለህ በመገናኘታችን በጣም አመሰግናለሁ፤የዛሬ አምስት ዓመት ሁለተኛ አልበምህን ካወጣህ በኋላ ጠፍተህ ነበር፤
ምንድነው መንስኤው?
ጌዲዮን፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ ታሜ፤እንግዲህ እንዳልከው በ2001 ዓ.ም ‹አንደኛ
ናት› የተሰኘውን ሁለተኛውን አልበሜን ካወጣሁ በኋላ ትንሽ ችግር ገጥሞኝ ነበር፤
ቁም ነገር፡- ምንድነው የገጠመህ?አልበምህ እንደጠበቅከው አልሆነልህም ወይስ ?
ጌዲዮን፡- እሱም አንዱ ምክንያት ነው፤ ግን ጊዜው ራሱ ጥሩ አልነበረም ለኔ፡፡የጤና ችግር
ገጠመኝ፡፡ምን እንደሆንኩ እንደነካኝ አላውቅም፤ መንፈሴ ትክክል አልነበረም፡፡አልበሙ በጣም
አሪፍ ስራ ነበር፤ ብዙዎቹን ኤልያስ መልካ ነበር ያቀናበረልኝ፡፡ ከኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ጋር በ1998 ዓ.ም ስለነበር የተዋዋልነው በዛን ወቅት ሲወጣ ብዙም አልተደመጠም፡፡
ቁም ነገር፡- ከዛ በኋላ ምን ትሰራ ነበር?
ጌዲዮን፡- ከቤትም አልወጣም ነበር፤ሥራ ሁሉ መስራት አልቻልኩም፡፡ ነገሮች ሁሉ ለኔ በጣም ከብደውኝ ነበር፡፡
ምን እንደነካኝ አላውቅም፤ ደንዝዤ ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- ታዲያ ምን አደረግህ?
ጌዲዮን፡- ወደ ፀበል ቦታ ነው የሄድኩት፤
ቁም ነገር፡-የት?
ጌዲዮን፡-ሽንቁሩ ሚካኤል ፤ ቅዱስ ኤልያስ፤ማርያም ነው ለረዥም ጊዜ ሄጄ የተቀመጥኩት፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል ሽንቁሩ ሚካኤል ነበር የተቀመጥኩት፡፡ ሁኔታው በጣም ከባድ ነበር፤ ሥራ ሁሉ መስራት እንዳልችል ተደርጌ ነበር፡፡
ቁም ነገር፡-ማን ነበር ፀበል ቦታ የሚወስድህ?
ጌዲዮን፡- ከጓደኞቼ ጋር ነበር እየሄድኩ
እዛ ተቀምጩ እጠመቅ የነበረው፡፡ በተለይ ሽንቁሩ ሚካኤል ስሄድ ሰላም ነበር የማገኘው፡፡

  1. ቁም ነገር፡- በመሀል እኮ ተሽሎህ ነበር ተብሎ ነበር?


ጌዲዮን፡- ልክ ነው፤ ከሽንቁሩ ሚካኤል ዓመት ያህል ተቀምጬ ከተመለስኩ በኋላ ትንሽ
ለውጥ ነበረኝ፤ባህሬን ሁሉ ሄጄ ለሁለት ወራት ሥራ ሰርቼ ነበር የተመለስኩት፤ የሚገርምህ በዛን
ወቅት ምን ሆነ መሰለህ፤ ሐመልማል አባተ ስልኬን አፈላልጋ ትደውልልኛለች፤የሆነች ልጅ በህልሟ
አይታኝ ነው ለእሷ የነገረቻት፡፡ ልጅቷ እንደዚህ አይነት ልጅ ጌዲዮን የሚባል ታውቂያለሽ ወይ?
ትላታለች፤ አዎ ስትላት፤ ታሟል አፈላልገሽ ሽንቁሩ ሚካኤል ሂድ በይው ትላታለች፡፡ እሷም ይህንን
ትነግረኛለች፡፡ ከዛ እንደገና ተመልሼ ሄድኩ ማለት ነው፡፡መገጣጠሙ በጣም ይገርማል፡፡
ቁም ነገር፡- በመሀል ግን ከአርቲስቶች ጋር አትገኛኝም ነበር?
ጌዲዮን፡-ከማንም ጋር አልገኛኝም ነበር፤ ሰው አያገኘኝም፤አልፎ አልፎ ሮባ ነበር የሚያገኘኝ፡
ቁም ነገር፡- ጉዳዩ ከፍቅር ጋር
የሚያያዝ ነው ይባላል?
ጌዲዮን፡- እንደዛም ነገር አለበት/ሳቅ/
ቁም ነገር፡- እሙ ናት?
ጌዲዮን፡- አዎ ያው እሙን የማያውቃት የለም፡፡ እሙ በጣም ጥሩ ልጅ ናት፤ እሷን ማጣቴ በህይወቴ ውስጥ ትልቅ ነገር ጎድሎኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ከልጅነት ጀምሮ ነው የምንተዋወቀው፤ማንም ቤተሰብ አጠገቤ ስለሌለኝ ያለችኝ እናቴም አባቴም እሷ ነበረች፡፡ብዙ ነገር አብረን አሳልፈናል፡፡
ቁም ነገር፡-ምን አጣላችሁ ታዲያ?
ጌዲዮን፡- የመጣላት ጉዳይ አይደለም፡፡
እሷ ትኖር የነበረው ዱባይ ነበር፤ ወደ አሜሪካ ነው የሄደችው፤ ግን አልቀርም እመጣለሁ ብላኝ ነበር፡፡ ከሁለተኛው አልበሜ በኋላ ድምጿን አጠፋችብኝ፡፡
ቁም ነገር፡- አሁን ስለ እሷ ምን መረጃ አለህ?
ጌዲዮን፡- ያው አሜሪካ ነው ያለችው፤ቁም ነገር፡- ትዳር መያዝ አለመያዟንስ?
ጌዲዮን፡- ደህና መሆኗን እንጂ ስለዚህ ጉዳይ አልጠይቃትም፤ ማወቅም አልፈልግም፤በነገራችን
ላይ አልፎ አልፎ ትደውልልኛለች፤ አይዞህ በርታ ጠንክር ትለኛለች፤
ቁም ነገር፡-እንዴት ነው ወደ አሜሪካ የሚያስኬድ ሥራ አልመጣልህም እስከዛሬ?
ጌዲዮን፡- አሁን በቅርቡ የእስራኤል ስራ አለኝ፤ ከዛ በኋላ ወደ አሜሪካ የሚያስኬደኝ ስራ
እየተነጋገርኩ ነው፤ ቁም ነገር፡- ድምፃዊ አበበ ተካ እንኳ ሚስቱን እዛው ድረስ ሄዶ ፈልጎ አግኝቷታል፤ አንተስ ምን ታስባለህ?
ጌዲዮን፡- እንግዲህ እኔም ሀሳቡ አለኝ፤ ሰዎቹ እያነጋገሩኝ ነው፤ ከተሳካ …
ቁም ነገር፡- ያለችበትን ስቴት ታውቀዋለህ?
ጌዲዮን፡-አዎ ዋሽንግተን ዲሲ ነው ያለችው፡
ቁም ነገር፡- ምናልባት ይህንን መፅሔት የምታነብ ከሆነ/በፌስ ቡክም ቢሆን/ ምላሿን
ትሰጥሃለች ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤በነገራችን ላይ ባለፈው አልበምህ ላይም አሁንም ነጠላ ዜማ
ለእሷ የዘፈንከው አለ አይደል?
ጌዲዮን፡- አዎ፤ ‹እሙ አይኔን› የሚለው የመጀመሪያ አልበሜ ላይ ያለው ለእሷ ነው፤ አሁን
ደግሞ የለቀቅሁት ‹ያመመኝ በእሷ ነው›የሚለው ነጠላ ዜማ ለእሷ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ግጥሙን ሰምቼዋለሁ፤ በጣም ስሜት የሚነካ ነው፤ እስኪ ትንሽ ስንኙን በልልኝ 
ጌዲዮን፡- ያመመኝ በእሷ ነው
እንዴት ብወዳት ነው
ያየሁትን መአት ችዬ አለሁኝ በእውነት
ያመመኝ በእሷ ነው
እንዴት እንዴት እንዴት
እንዴት ብወዳት ነው
እኔማ ኪሴን ልቤን
ፈትሼ ዝር የሚል ሳጣ ለነፍሴ
የሰው ልጅ እንዲህ ይሆናል
ስል ወደ ቀራኒዮ አዬ መንፈሴ› ነው
የሚለው፡፡ ከግል ህይወቴ ጋር የሚገናኝ በመሆኑ
በዚሁ መልኩ ክሊፕ እየሰራሁለት ነው፡፡
ቁም ነገር፡- አሁን በመልካም ጤንነት ላይ ነው የምትገኘው፤ እንዴት ወደዚህ ህይወት
ተመለስክ?
ጌዲዮን፡- እኔ ወደ ሽንቁሩ ሚካኤል ከገባሁ ጊዜ ጀምሮ በሚዲያ ላይ ምን እንደሚነገር
እንደሚወራ አላውቅም፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ከዛ ከቤተ ክርስቲያኑ ግቢ ስወጣ አንድ ሰው ያገኘኝና ሰይፉ ፋንታሁን በሬዲዮ ስላንተ ሲናገር ሰምቻለሁ፡፡ ያገኛችሁት ሰዎች ካላችሁ ጠቁሙን ብሏል
ስለዚህ አሁን በስልክ ላገናኝህ ብሎ ደውሎ አገናኘኝ፡፡ በእውነት ሰይፉ ፋንታሁንን በጣም
ነው የማመሰግነው፡፡ እግዚአብሔር ይባርከው፡፡ ከሱ ጋር መነጋገር ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ
ነገሮች ሁሉ እየተለወጡ መጡ፡፡ ያኛውን ጌዲዮን ረስቼ አዲስ ሰው እንድሆን ነው ያደረገኝ፡፡ከዛ
በሬዲዮ አነጋገረኝና ጤነኛ መሆኔን ከተናገረ በኋላ ኢቢኤስ ቲቪ ላይ መቅረብ አለብህ
ህዝብ ሊያይህ ይገባል ብሎኝ ጥሩ ፕሮግራም ተሰራ፤ሰዎችም አርቲስቱም አይዞህ አሉኝ ማለት
ነው፤ እንግዲህ አስበው ፤ የወጣሁት ከፀበል ቦታ ነው፤ ግን በአንድ ጊዜ ወደ ስራ የምገባበትና አሁን
ያለሁበትን ጎተራ ኮንዶሚኒየም ተከራይተው አዲስ ህይወት ውስጥ እንድገባ አድርገውኛል፡፡
ቁም ነገር፡- ምንድነው ያገኘከው ድጋፍ?
ጌዲዮን፡- እንግዲህ የገንዘብ መዋጮ
ያደረጉልኝ ሰዎች አሉ፤ ጎሳዬ ተስፋዬ ፤የክለብ ኤችቱኦ ባለቤት፤ የኪንግ ሲልቨር ባለቤት እንዲሁም
ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ አንድ ባለሀብት ድጋፍ አድርገውልኛል፡፡ በሙያ በኩል አቀናባሪዎቹ
ኤልያስ መልካ፤ ካሙዙ ካሳ፤ አማኑኤል ይልማ፤ አበጋዙ ክብረወርቅ ሁሉም ሊሰሩም ቃል ገብተዋል፡፡ እንዲሁም ሄኖክ ነጋሽ ከአሜሪካ ደውሎ አንድ ዘፈን ግጥምና ዜማ ጨርሼልሃለሁ እልክልሃለሁ ብሎኛል፡፡
ሌሎችም ጓደኞቼ ታደለ ሮባ ያው የታወቀ ነው ከሰይፉ ጋር ሆነው አሁንም አንዳንድ ነገሮችን እያሟሉልኝ ነው፡፡ የአዲሱ አልበሜም ፕሮውዲውሰሩ ሮባ ነው፡፡ ማዲንጎ ፤ ጆሲ፤ ዳዊት ፅጌ፤ ሳምሶን ማሞ፤ሰራዊት ፍቅሬ፤ ቴዲ አፍሮ ከነባለቤቱ ትልቅ ተስፋ ነው የሰጡኝ፡፡ ቴዲ እንደውም ግጥምና ዜማ እሰጥሃለሁ ምንም ነገር እንዳታስብ ነው ያለኝ፡፡ሀይልዬ ፤ፀጋዬ እሸቱ ብቻ በጣም ሁሉንም በስም ያልጠቀስኳቸውንም በሙሉ እግዚአብሔር ያክብርልኝ ነው የምልው ፡፡
ተቦርነም አሜሪካ ካሉ አድናቂዎቼ ጋር አገናኝቶኛል፤በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በዛወርቅ አስፋው አክስቴ ነች፤ የእናቴ እህት ናት፡፡ ደውላ አናግራኛለች፡፡ ቴዲ የማርሸት ልጅም አግኝቶኛል፡፡ መንግስቱ አሰፋንና አለምነህ ዋሴን፤ሁሉንም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ቁም ነገር፡-ስራስ አልጀመርክም?
ጌዲዮን፡- እየሰራሁ ነው፤ ሐረር መሶብ ሀሙስ፤አርብ፤ቅዳሜና እሁድ እሰራለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- የድሮውን ጌዲዮን አሁን ድጋሚ እናገኘዋለን?
ጌዲዮን፡-በበለጠ ሁኔታ ይገኛል፡፡ በጣም ብዙ ነገሮችን ስላሳለፍኩ ጠንካራ ሆኛለሁ ብዬ ነው የማስበው፡፡ ብዙ ነገር ተምሬያለሁ፤በህይወቴ ውስጥ ያየሁትን ከባድ ነገር ወደ ጥሩ ነገር መቀየር እፈልጋለሁ፡፡ ከዚህ የበለጠ ከባድ ነገር ከዚህ በኋላ ቢገጥመኝ እንኳ በቀላሉ አልሸነፍም፡፡ ስለዚህ በአዲስ መንፈስ ነው ወደ ስራ የተመለስኩት፡፡ በዚህ አጋጣሚ በየሄድኩበት ቦታ ሁሉ ህዝቡ ለሚሰጠኝ ፍቅና አክብሮት ምላሽ ለመስጠት ቃላት የለኝም፡፡ እግዚአብሔር ያክብርልኝ ብቻ ነው
ለማለት የምችልው፡፡
ቁም ነገር፡- ከዚህ ሁሉ በኋላ እግዚአብሔርን በመዝሙር ለማመስገን አላሰብክም?
ጌዲዮን፡- በደንብ ነዋ፤የኔ ፍላጎትማ ሙሉ ካሴት መዝሙር ለመስራት ነው፤ቢፈቀድልኝ አምላኬን በዚህ መልኩ ባመሰግን ደስ ይለኛል፡፡ ግን በቅድሚያ በነጠላ መዝሙር ላደረገልኝ የማይመለስ ውለታው እግዚአብሔርን ለማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- ከዚህ በፊት ቃለ ምልልስ ስናደርግ ወደ ፊልም ስራ የመግባት ሀሳብ እንደነበረህ ነግረከኛል፤አሁንስ እንዴት ነው?
ጌዲዮን፡- በፊት እኮ የመጀመሪያ አልበሜን ካወጣሁ በኋላ ‹የማያልቀው መንገድ› የሚል ፊልም ላይ ሰርቼ ነበር፡፡ እንደ አሁኑ በየሲኒማ ቤቱ መታየት ሳይጀመር በቪዲዮ ሲዲ ነበር የወጣው፡፡ አሁን እንግዲህ የሚያሰራ ካለ እናያለን..
ቁም ነገር፡- በመጨረሻስ
ጌዲዮን፡- ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ የሙያ ጓደኞቼን ጋዜጠኞችን በሀገር ውስጥም በውጪም አረብ ሀገራትም አውሮፓና አሜሪካ ያሉ የሙዚቃ አድናቂዎቼን በሙሉ አመሰግናለሁ፡፡በጥሩ የሙዚቃ ሥራ አስደስታችኋለሁ ነው የምለው፡፡
ቁም ነገር፡- አመሰግናለሁ፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar