mandag 2. juni 2014

ለብዙ ዓመታት ከኖሩበት ቀየ መፈናቀላቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ

በኦሮምያ ክልል በምእራብ ሸዋ ዞን በዳኖ ወረዳ አጂላ ዳሌ ቀበሌ ይኖሩ የነበሩ አርሶ አደሮች ለኢሳት እንደገለጹት ከ19 ዓመታት በላይ ከኖሩበት ቀየ በተለያዩ ሰበቦች ሀብትና ንብረታቸውን ተቀምተው ለቀው እንዲወጡ በመደረጋቸው  ቤት አልባ ሆነው ለችግር ተዳርገዋል።
“መንግስት በአካባቢው እንድንኖር ፈቃድ ሰጥቶን የሚፈለግብንን ግብር እየከፈልን አካባቢውን ስናለማ ነበር” የሚሉት አርሶ አደሮች፣ ሀብትና ንብረት ካፈራን በሁዋላ ” የያዛችሁት መሬት ለቤተክርስቲያን ማሰሪያ ይፈለጋል” በሚል ሰበብ ምንም ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጠን በፍርድ ቤት እንድንለቅ ተደርገናል ብለዋል።
“ጉዳዩን ለሚመለከታቸው የወረዳ ባለስልጣናት ቢያመለክቱም፣ የወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ለገሰ ንጉሴ  ከሳሽ ሆነው በመቅረባቸው ምንም መፍትሄ ሊያገኙ አለመቻላቸውን አርሶደአሮች አክለው ገልጸዋል።
ጌታቸው ገዴ፣ ዘውዱ ገብረመድህን፣ ቦጋለ ተካ፣ ወ/ሮ ጌጤ ሃይሌ፣ ዳኜ ይልማ፣ ቄስ ልኬ አወቀ፣ አበራ ካሳ፣ ቄስ ተካ ጸጋው፣ ሃብታሙ ክብረት እና ደብረ ደነቀ የተባሉትና ሌሎችም ተፈናቅለዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ ለገሰ ንጉሴን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሰካልንም።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar