mandag 21. januar 2013

በኤርትራ የወታደሮች አመፅ ቆመ





            ያመፁ የኤርትራ ወታደሮች የማስታወቂያ ሚኒስቴሩን ለአንድ ቀን ከተቆጣጠሩ በኋላ ለቅቀው መውጣታቸው ተዘግቧል፡፡


           ወደ አንድ መቶ እንደሚሆኑ የተነገረው ወታደሮች ወደ ደቡብ የጦር ሠፈራቸው የተመለሱት ከፕሬዚዳንት   ኢሣያስ  አፈወርቂጋር ከተነጋገሩ በኋላ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡


ዛሬ አብዛኛውን ቀን ዝግ ሆኖ የዋለው የሃገሪቱ ቴሌቪዥን ጠፍቶ የዋለበትን ምክንያት ሣይናገር ምሽት ላይ መደበኛ ፕሮግራሙን ቀጥሏል፡፡

የቴሌቪዥን ጣቢያው ድንገት ከመቋረጡ በፊት አንባቢው ሕገመንግሥቱ እንዲከበር እና የፖለቲካ እሥረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅ መግለጫ ያነብብ እንደነበረ ታውቋል፡፡


ስድስት ሚሊየን ሕዝብ ባላት ኤርትራ ከአምስት ሺህ እስከ አሥር ሺህ የፖለቲካ እሥረኞች ወህኒ ቤት ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ቢሮ ገልጿል፡፡


እሥረኞቹ ዛሬ (ሰኞ) ረፋዱ ላይ በብረት ለበስ መኪና መምጣታቸውንና ቅሬታዎቻችን ናቸው የሚሏቸውን ጉዳዮች ዝርዝር ይዘው እንደነበረ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ብዙ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሠራተኞች አመልክተዋል፡፡

የወታደሮቹ ጥያቄ ምን እንደነበረ እና አመፁ በምን እንደተፈታ ለጊዜው የተገኘ ዝርዝር መረጃ የለም፡፡

አሥመራ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎቹ አሥመራ ከተማ ውስጥ ከሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ አውጥቷል፡፡

የኤምባሲው መግለጫ የሚናገረው በአንዳንድ የዋና ከተማይቱ አካባቢዎች ወታደሮች በብዛት እየታዩ መምጣታቸውን ዲፕሎማቶች መናገራቸውን ነው፡፡


በሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተገነጠለችበት ጊዜ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ መንበሩን እንደተቆናጠጡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡


ኤርትራ ለውጭው ዓለም በአመዛኙ ዝግ የሆነችና በጠንካራ እፍኞች ተጨብጣ የሆነች ሃገር እንደሆነች ይነገራል፡፡

ዛሬ ስለተፈጠረው አጋጣሚ የመንግሥቱን አስተያየት ለመጠየቅ ስልክ በተደጋጋሚ ቢደወልም ባለሥልጣናቱ ስልኮቹን ሳያነሱ ቀርተዋል፡፡



ኤርትራ ሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሣቀሱ አማፂያንን ታስታጥቀለች፤ ትረዳለች በሚል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ - እአአ በ2009 ዓ.ም ማዕቀብ እንደጣለባት ይታወሣል፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar