lørdag 26. januar 2013

ገቢዎች እና የከፍተኛ ግብር ከፋይ ኩባንያ ባለአክስዮኖች እንደተፋጠጡ ነው




የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በንግድ ማኀበራት ባልተከፋፈለ ትርፍ ላይ የ10 በመቶ የጣለው የግብር ውሳኔ
ከፍተኛ ግብር ከፋዮችን ኩባንያዎችና ባለአክስዮኖችን አስቆጥቷል፡፡

ባለስልጣኑ በተሻሻለው የገቢ አዋጅ ቁጥር 286/94 በአንቀጽ 4 ላይ የአክስዮን ማኀበራትና ኀላፊነቱ የተወሰነ
የግል ማኀበር ካከፋፈሉት የአክስዮን ድርሻ ትርፍ ገቢ የሚያገኝ ማንኛውም ሰው ባገኘው ገቢ ላይ የ10 በመቶ
ግብር እንደሚከፍል ይደነግጋል፡፡
ባለስልጣኑ ከዚህ በተጨማሪ ባልተከፋፈለ የአክስዮን ድርሻ ላይ ግብር እንዲከፈል

ወስኖ ከ1ሺ461 ያህል ኩባንያዎች 816 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ በማቀድ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡
ባለስልጣኑ
ለግብር ከፋዮቹ በላከው የግብር ውሳኔ መሰረት ወደኃላ ሄዶ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በሂሳብ ሚዛናቸው ላይ
ለባለአክዮኖች ሳያከፋፍሉ የቆዩትን በዓይነትም ሆነ በጥሬ ገንዘብ ያለን ሐብት ላይ ታክስና ግብር እንዲከፍሉ
ወስኗል፡፡

በዚሁ የባለስልጣኑ እርምጃ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የአንድ የግል ባንክ የሕግ ባለሙያ እርምጃው አክስዮን
ማኀበራት ሥራቸውን ለማስፋፋት የሚያደርጉት ጥረት ላይ አሉታዊ ውጤት ከመጣሉም በላይ ተደራራቢ ታክስን
የሚያስከትል በመሆኑ ተቀባይነት ያለው አካሄድ አይደለም ብለዋል፡፡

አያይዘውም በርካታ አክስዮን ማኀበራት በአነስተኛ ካፒታል ተቋቁመው በየዓመቱ ከሚያስመዘግቡት ትርፍ ባለአክስዮኖችን እያስፈቀዱ ገንዘቡን ከመከፋፈል ይልቅ ለኩባንያው ማጠናከሪያ እንዲውል በማድረግ የተሻለ ኢንቨስትመንት እንዲካሄድ የሚያደርጉበት ሁኔታ እንደነበረጠቅሰዋል፡፡

 በዚህ መንገድ ኩባንያዎች ሲጠናከሩ አዳዲስ ሥራዎችን በመክፈትና ያሉትን በማስፋፋት ተጨማሪ የሥራ
ዕድሎች እንዲፈጠሩ አስተዋጽዖ ከማድረጋቸው በተጨማሪም አዲስ በፈጠሩት እሴት አማካኝነት ለአገር ልማት ሊውል
የሚችል ታክስና ግብር የሚያስገቡበት ሁኔታ እንዳለ አስታውሰዋል፡፡


እሳቸው የሚሰሩበትን ባንክን በምሳሌነት በማንሳት ባለአክዮኖቹ ትርፍ ላለመከፋፈል በመወሰናቸው ባንኩ ለብድር አገልግሎት የተሻለ የፋይናንስ አቅም በማግኘቱ ትርፋማነቱ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

የአሁኑ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ታክስና ግብር ለማስገባት ብቻ
ያለመው አካሄድ ለአገር የማይጠቅምና የከፍተኛ ኩባንያዎች ባለአክዮኖች ሐብታቸውን ወደተጨማሪ ኢንቨስትመንት
እንዳያውሉ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ብለዋል፡፡

ከጥር ወር 2005 ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን በባለስልጣኑ የተወሰነው ይህው ለግብር ከፋዮች ተላከው ማስታወቂያ
በአመዛኑ ከፍተኛ የሚባሉ ግብር ከፋዮችን ማለትም ባንኮችን፣የመጠጥና የለስላሳ ኢንዱስትሪዎችን፣ሌሎች በአክስዮን
የተመሰረቱ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን የሚመለከት ነው፡፡እነዚህ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ግን በገቢ ረገድ
ከባለስልጣኑ ዓመታዊ ጠቅላላ የግብርና ታክስ ገቢ እስከ 80 በመቶ ገደማ የሚሸፍኑ ናቸው፡፡


Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar