torsdag 31. januar 2013

የአቶ ጁነዲን ያለመከሰሰ መብት ያለመነሳት ጉዳይ ማነጋገሩን ቀጥሏል



ከሁለት ሳምንት በፊት ያለመከሰሰ መብታቸውን ለማንሳት በአጀንዳ መልክ ለፓርላማ ቀርቦ የነበረውና ባልታወቀ
ምክንያት ፓርላማው እንዳይወያይበት በተደረገው የቀድሞ የኦህዴድ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር
አቶ ጁነዲን ሳዶ ጉዳይ _ሕግ አስፈጻሚው አካል አሁንም ዝምታን መምረጡ አነጋጋሪነቱ ቀጥሎአል፡፡

ፓርላማው ከሁለት ሳምንት በፊት ባቀረበው አጀንዳ የአንድ የም/ቤት አባል ያለመከሰሰ መብት ስለማንሳት በሚል
ለውይይት አጀንዳ መያዙን ካስታወቀ በኃላ በድንገት ስብሰባው ከተጀመረ በሁዋላ ለሌላ ጊዜ መተላለፉ በአፈጉባዔው
በኩል ተገልጾአል፡፡

የፓርላማው ምንጮች እንደገለጹት አጀንዳው በፓርላማው ከኦሮሚያ ደራ ወረዳ ተመራጭ የሆኑትን አቶ ጁነዲን ሳዶን
የሚመለከት ነበር፡፡

ሆኖም ባልታወቀ ምክንያት አጀንዳው እንዲያድር ከተደረገ በሃላ ላለፉት አስራአምስት ቀናት
በላይ ዝምታ መመረጡ የብዙዎችን ትኩረት መሳቡ ታውቋል፡፡

አቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤታቸው ወ/ሮ ሐቢባ መሐመድ አዲስአበባ ከሚገኘው ሳዑዲ ኤምባሲ ገንዘብና የተለያዩ
መጽሐፍትን ተረክበው ሲወጡ እጅ ከፍንጅ ከተያዙበት ከሐምሌ 9 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ከመንግስታዊ
ኃላፊነታቸውን በተጨማሪ በመስከረም ወር መጨረሻ የዓመቱ መደበኛ ሥራውን የጀመረው ፓርላማ ተገኝተው አያውቁም፡፡

ከባለቤታቸው ጥፋት ጋር ተያይዞ ከኦህዴድ አመራርነት ተገምግመው እንዲነሱ የተደረጉት አቶ ጁነዲን በጠ/ሚ
ኃይለማርያም አዲሱ ካቢኔም ተወግደው በአቶ ሙክታር ከድር መተካታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ባለቤታቸው በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ክሳቸውን እየተከታተሉ ቢሆንም ከሳዑዲ ኤምባሲ ጋር ከነበራቸው ግንኙነት ጋር
በተያያዘ የምዋች እናታቸውን ኑዛዜ ለማስፈጸም የገንዘብ ዕርዳታ የጠየቁት ራሳቸው መሆናቸውን በመግለጽ ባለቤታቸው
በጉዳዩ እጃቸው እንደሌለበት በይፋ ቢናገሩም እስካሁን የተጠየቁበት ሁኔታ አለመኖሩ የህግ ሥርዓቱን ፍትሐዊነት
ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል፡፡

ፓርላማው ያለመከሰሰ መብታቸውን ለማንሳት ያደረገው ሙከራም የከሸፈበት ምክንያትም ለብዙዎች እንቆቅልሽ እንደሆነ ነው፡፡

በተያያዘም ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም ባለቤታቸውን አቶ መለስ ዜናዊን በድንገተኛ በሞት ያጡት ወ/ሮ አዜብ
መስፍን ከሐዘናቸው ካገገሙም በሃላ በፓርላማ ውስጥ ተገኝተው እንደማያውቁ ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡

ፓርላማው በ3ኛ ዓመት የስራ ዘመኑን በመስረም ወር መጨረሻ ጀምሮ እስካሁን መደበኛ ስብሰባዎችን እያስተጎጎለም
ቢሆን 15 መደበኛ ስብሰባዎችን ያካሄደ ቢሆንም የፓርላማው አባል የሆኑት ወ/ሮ አዜብ በአንዱም ስብሰባ ላይ
አልታዩም፡፡

እንደ ምንጮቻችን ገለፃ አቶ መለስ ዜናዊ በሕወት በነበሩበት ጊዜ በቁም የተነሱትን ፎቶግራፍ ሁሉም አባላት
ሊያዩት በሚችሉበት ሁኔታ ፊት ለፊት የተሰቀለ ሲሆን ይህ ፎቶ በትልቁ ፊት ለፊት መሰቀሉ በብዙዎቹ የፖርላማ አባለት ዘንድ አሁንም ፖርላማውን እየመሩ ያሉት እርሳቸው እንደሆኑ የሚያሳስብ መንፈስ ፈጥሮባቸዋል::

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar