fredag 26. april 2013

በአፋር የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ልዩ ወረዳ መጠየቃቸውን የአፋር ሰብአዊ መብቶች ድርጅት ተቃወመ



የዞን ሁለት ዋና ከተማ በሆነው አብአላ የሚኖሩ 15 ሺ የሚጠጉ የትግራይ ተወላጆች ራሳችንን በራሳችን ለማስተዳደር ልዩ ወረዳ ይሰጠን በማለት ያቀረቡት ጥያቄ ተገቢ አይደለም ሲሉ የአፋር ሰብአዊ መብቶች ሃለፊ አቶ ገአስ አህመድ ገልጸዋል።

አቶ ጋአስ በዱብቲ ከተማ በርካታ የአማራ፣ የኦሮሞ እና የትግራይ ተወላጆች ቢኖርም አንድም ቀን የወረዳ ጥያቄ አለማንሳታቸውን ገልጸው፣ ከመቀሌ በ45 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አብአላም ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ያቀረቡት ጥያቄ አሳዛኝ መሆኑን ገልጸዋል።

 የአፋር ክልል በህወሀት ሰዎች የሚመራ መሆኑን የገለጹት አቶ ገአስ፣ ተወላጆቹ ወረዳ ይሰጠን ከሚሉ ክልሉ የራሳቸው መሆኑን ቢያውቁት ይሻል ነበር ብለዋል።

አቶ ገአስ እንደሚሉት በአብላ የሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች ከተማዋ ሸከት ተብላ እንድትጠራ እንዲሁም የአፋር ክልላዊ መንግስት በከተማዋ መሬት ለኢንቨስትመንት መስጠት አይችልም የሚሉት ጥያቄዎች የመብት ጥያቄዎች ሳይሆኑ የመሬት ይገባኛል ጥያቄዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ በአፋር ክልል የህወሀት ባለስልጣናት ግምገማ እያስደረጉና የራሳቸውን ሰዎች እየሾሙ ክልሉን ለውድመት መዳረጋቸውን አቶ ገአስ አመልክተዋል
በጉዳዩ ዙሪያ የአብአላ የትግራይ ተወላጆችን ተወካይ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar