torsdag 27. august 2015

አቶ ማሙሸት አማረ ለውሳኔ ተቀጠሩ

‹‹ምስክርነቱ የሀሰትና የተጠና ነው!›› ጠበቃው
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

mamushet
mamushetአይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም መንግስት ከጠራው ሰልፍ አንድ ቀን ቀድሞ ከለቅሶ ቤት ወደ ቤተ መንግስት ለተደረገውና ለዋናው (ለሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም) ሰልፍ አነሳስቷል በሚል ክስ የተመሰረተበት አቶ ማሙሸት አማረ ዛሬ ነሃሴ 20/2007 ዓ.ም አራዳ ምድብ ችሎት ቀርቦ ለነሃሴ 22/2007 ዓ.ም ለውሳኔ ተቀጠሯል፡፡ አቶ ማሙሸት አማረ ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም በተካሄደው ሰልፍ ላይ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥሯል በሚል ተከሶ የነበር ቢሆንም በወቅቱ ከምርጫ ቦርድ ጋር በነበረው ክርክር ሰልፉ ላይ አለመገኘቱን የሚያጋግጥ መረጃ በማቅረቡ በነፃ እንዲለቀቅ ተወስኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ክሱ ወደማነሳሳት ተቀይሮ እስር ቤት እንዲቆይ ተደርጓል፡፡


አቶ ማሙሸት በአዲሱ ክስ የአቃቤ ህግን ምስክሮች ለመስማት ከ5 ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት እንደተመላለሰ የተገለፀ ሲሆን በተለይ አንዱ ምስክር በፖሊስ ተይዞ እንዲመጣ ቢጠየቅም ፖሊስ ሳያስፈፅም ቀርቷል፡፡ ከአራቱ ምስክሮች መካከል ሶስቱ ዛሬ የመሰከሩ ሲሆን ‹‹አቶ ማሙሸት አማረ 300 ብር ከፍሎ ሰልፍ እንድንወጣ አድርጎናል›› ሲሉ መስክረዋል፡፡

ይሁንና ምስክሮቹ ከማሙሸት ጋር በተገናኙበት ወቅት እንዲሁም ገንዘቡ ሲሰጣቸው፣ ሰልፉ ያለፈባቸውን ቦታዎችና ስለ ሌሎችም ጉዳዮች ሲጠየቁ ‹‹አላስታውሰውም›› ከማለት ባለፈ ዝርዝር የምስክርነት ቃል ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ ከምስክሮቹ መካከል ሁለቱ አቶ ማሙሸትን ያስያዙ ደህንነቶች መሆናቸውን አቶ ማሙሸትና ጠበቃው በችሎቱ የገለፁ ሲሆን ምስክሮቹ በበኩላቸው ስራቸውን ሲጠየቁ ‹‹የግል›› እያሉ ከመመለስ ውጭ የመንግስት ስራ እንደማይሰሩ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የመንግስት ሰራተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ መታወቂያ ሲጠየቁ ሊያሳዩ አልቻሉም፡፡ ከሶስቱ ምስክሮች መካከል አንደኛው ስራውን ሲጠየቅ ‹‹የግል›› ብሎ የነበር ቢሆንም በመስቀለኛ ጥያቄ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጥቃቅንና አነስተኛ አመራር መሆኑን አምኗል፡፡

ከምስክሮቹ መካከል ሁለቱ የመኢአድ ደጋፊዎች መሆናቸውን ሲጠቅሱ አንደኛው አቶ ማሙሸት ባቀረቡበት የመስቀለኛ ጥያቄ ከምርጫ በኋላ የወጣቶች ሊግና የኢህአዴግ አባል መሆኑን አምኗል፡፡ የኢህአዴግ አባል ሆኖም ቢሆን መኢአድን እንደሚደግፍም ገልጾአል፡፡ ዳኛው ‹‹በሁለት ወር ውስጥ እንዴት ብለህ የወጣቶች ሊግ አባል መሆን ቻልክ?›› ሲሉት መልስ ሳይሰጥ አልፎታል፡፡
የአቶ ማሙሸት አማረ ጠበቃ ሶስቱም ምስክሮች አብዛኛዎቹን ጉዳዮች እንደማያስታውሱ በመግለፃቸው የተጠና የምስክርነት ቃል መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ከ7 አመት በላይ አዲስ አበባ ውስጥ ኖረው መስቀል አደባባይን ጨምሮ ሰልፉ አመራባቸው የተባሉትን ቦታዎች አናውቃቸውም ማለታቸው፣ መተዳደሪያ ስራቸውን መደበቃቸውና መታወቂያ ለማሳየትም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምስክርነቱ የሀሰት እንደሆነ ስለሚያረጋግጥ ደንበኛቸው በነፃ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar