torsdag 18. juli 2013

የአውሮፓ የፓርላማ ልኡካን በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች እና የሲቪክ ማህበረሰቡ መሪዎች እንዲፈቱ ጠየቁ



በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝነት በማድረግ ላይ ያለው የልኡካን ቡድኑ መሪ ባርባራ ሎክብሂለር ጋዜጠኞች እና የሲቪክ ማህበረሰብ መሪዎች ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የማምለክና የመሰብሰብ መብታቸውን በመጠቀማቸው መታሰራቸው ተገቢ ባለመሆኑ ሊፈቱ ይገባል ብለዋል።


በኢትዮጵያ በስራ ላይ ያለው የጸረ ሽብርተኝነት ህጉ የፖለቲካ ልዩነትን ለማፈን እየዋለ መሆኑን የገለጸው የልኡካን ቡድኑ፣  የአገሪቱ ህገመንግስት ጥሩ ቢሆንም የፍትህ ስርአቱ አድሎአዊ መሆኑን ለመመልከት ችለናል ብሏል።


የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ አገሪቱ ያሰረቻቸው ፖለቲካ እስረኞች የሌሉ በመሆኑ ፣ እነሱ ስላሉ የሚፈቱበት ሁኔታ የለም በማለት የህብረቱ ልኡክ ለሰጠው መግለጫ ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል።


አቶ ጌታቸው አክለውም በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞችና እና የሲቪክ ማህበር መሪዎች የታሰሩት የሽብር ወንጀል ሲፈጽሙ በመገኘታቸው በመሆኑ ሊፈቱ የሚችሉትም የእስር ጊዜያቸውን ሲፈጽሙ ወይም መልካም ስነምግባር ካሳዩ በገደብ ነው ብለዋል።


የአውሮፓ ህብረት የሰጠው መግለጫ ለህብረቱ እና ለኢትዮጵያ ግንኙነት የሚጠቅም አይደለም በማለትም አቶ ጌታቸው አክለዋል።


የአውሮፓ ህብረት የልኡካን ቡድን እስረኞችን ለመጠየቅ ወደ ቃሊቲ ቢያመራም  የእስር ቤቱ ሀላፊ ” ከእናንተ ጋር ለመስራት ጊዜ የለኝም” በሚል እንደሸናቸው ጆርጅ ሊችትፊልድ የተባሉ  የልኡካን ቡድኑ አባል ተናግረዋል። ሁሉም የልኡካን ቡድኑ አባላት የእስር ቤቱ ሀላፊ በሰጡት መልስ መደናገጣቸውን የገለጸው አሶሼትድ ፕሬስ፣ ኢትዮጵያ እስር ቤቱን ለማሻሻል ጥያቄ በማቅረቡዋ እስር ቤቱን በአካል ተገኝቶ ለመጎብኘት አንደሄዱ መናገራቸውንም ዘግቧል።


የአውሮፓ  ህብረት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ልገሳ እንደሚያደርግ ይታወቃል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar