onsdag 12. februar 2014

በሀገረ-ማርያም ከተማ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ የሀገር ሽማግሌዎች ታሰሩ

በአርሴማ ቤተክርስቲያን የተነሳውን የውስጥ ችግር ተከትሎ ችግሩን ለመፍታት የተመረጡት የሰበካ ጉባኤ አባላት ታስረዋል።
በህዝቡ የተመረጡት 15ቱ ሽማግሌዎች ችግሩን ለመፍታት በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የቀጠናው ሃላፊ የሆኑት አቡነ ገብርኤል የሰበካ ጉባኤ አባላቱ እንዲበተኑና ችግሩን ለመፍታት እንደሚሞክሩ መግለጻቸው ህዝቡን አስቆጥቷል። ጳጳሱ  ለፌደራል ፖሊሶች በማመልከት የአገር ሽማግሌዎች እንዲታሰሩ ማድረጋቸውን የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ዛሬ ጳጳሱ ወደ አካባቢው በመሄድ ንግግር ሊያደርጉ ሲሞክሩ ህዝቡ የታሰሩት የሰበካ ጉበኤ አባላት ካልተፈቱ ምንም አይነት ምክንያት አንሰማም በማለት ተቃውሞ አሰምቷል። ጳጳሱም ሰዎቹ የታሰሩት በፖለቲካ ምክንያት ነው በማለት ለማረጋጋት ቢክሩም ህዝቡ ግን አሁንም የሚቀበላቸው አልሆነም። የቤተክርስቲያን ደወል በመደወል ወደ ፍትህ ቢሮ ያመራው የከተማው ነዋሪ፣ ሰዎቹ ካልተፈቱ በተቃውሞአቸው እንደሚገፉበት አስጠንቅቀዋል።
የፌደራል ፖሊስ በበኩለ ማንኛውም ሰው ተቃውሞ ለማሰማት ሙከራ ቢያደርግ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቋል። እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉት 11 ዱ የአገር ሽማግሌዎች  ፍርድ ቤት ቀርበው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል።
ወደ ስቱዲዮ ከመግባታችን በፊት በደረሰን ዜና ደግሞ ጳጳሱ ዛሬ ረቡእ በድጋሜ ከህዝቡ ጋር የተገናኙ ቢሆንም፣ ህዝቡ መሪዎቻችን ሳይፈቱ ምንም አይነት ውይይት አይኖርም የሚል አቋም በመያዙ፣ አቡነ ገብርኤል የሃገር ሽማግሌዎች እንዲፈቱ ጠይቀዋል። የጳጳሱን ጥያቄ በመቀበል የከተማው ባለስልጣናት ሰዎቹን ለመፍታት ቢሄዱም፣ የአገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው ወንጀል ስራተችሁዋል ተብለን የታሰረን በመሆኑና ፍርድ ቤትም የጊዜ ቀጠሮ ለ14 ቀናት የጠየቀብን በመሆኑ፣ ፍርድ ቤት ቀርበን ጥፋታችን ሳይነገረን አንፈታም በማለት ከእስር ለመውጣት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ባለስልጣኖቹም የፍርድ ቤት ቀጠሮው አጥሮ እስረኞች ነገ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ እንደሚያደርጉ ታውቋል። የእስረኞች መፈታት የተፈጠረውን ችግር ያበርደዋል ተብሎ ይጠበቃል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar