onsdag 13. mars 2013

እንደምን ሰነበታችሁ? ይህ ለአፋና እጅ የማይሰጥ የህዝብ ድምፅ ነው፡፡



እንደምን ሰነበታችሁ? ይህ ለአፋና እጅ የማይሰጥ የህዝብ ድምፅ ነው፡፡ለዜጎች ክብር የማይሰጠው ኢህአዴግ፣ ህዝብ በሚከፍለው ግብር መልሶ የሚያፍነው ኢህአዴግ፣ የሀይማኖት ተቋማትን ወደ ‹‹አጋር ፓርቲ››ነት እየቀየረ ያለው ኢህአዴግ ፍትህ ጋዜጣን እና አዲስ ታይምስ መፅሄትን በጉልበት ከነጠቀን በኋላ፣ ለሶስተኛ ጊዜ በሌላ ጋዜጣ ተመልሰናል፡፡ ጋዜጣዋ ‹‹ልዕልና›› ትባላለች፡፡

 ከተመሰረተች ጊዜ ጀምሮ ለአንዴ ብቻ ታትማ ተቋርጣ ነበር፡፡ አሁን ግን የነበረባት የመንግስት ዕዳ ተከፍሎ፣ አሳታሚ ድርጅቱ በሀገሪቱ የአክሲዮን ሽያጭ ህግ መሰረት ወደ እኛ መዞሩን አበስራለሁ፡፡

 እናም ዛሬ በዕለተ ቅዳሜ ለአንባቢያን ትደርሳለች፡፡ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ግን ‹‹አርብ አርብ ይሸበራል፤ …›› እንዲል ንጉስ ቴውድሮስ፣ ልዕልና ጋዜጣም የዕለት አርብ ድምፅ ሆና ትቀጥላለች፡፡

እንደመውጫም ይሆነኝ ዘንድ በአዲሷ ጋዜጣችን ላይ ‹‹ከተዘጋው በር ጀርባ›› በሚል ርዕስ ላቀረብኩት ፅሁፍ መግቢያ ያደረኩትን እዚህም ልድገመው፡-
እነሆ በሶስተኛው በር ተገናኝተናልና አብዝቼ አላማርርም፡፡

 ባማርርስ የት እደርሳለሁ? ማነው አገዛዙንስ ከስሶ የረታ? ደግሞስ ከመቼ ወዲህ ነው በሀገሬ መሬት ላይ ህግ የበላይ ሆኖ የሚያውቀው? ለማንኛውም የጠፋው ብርሃን በዚህ መልኩ ዳግም ይፈነጥቅ ዘንድ ስለተከፈለው ዋጋ ወይም ውጣ ውረድ ገድል የመፃፍ ፍላጎት የለኝም፡፡

 ፍላጎቴ ከባልደረቦቼ ጋ በፀና መንፈስ በጀመርነው ጎዳና እንተም ዘንድ የመንግስትን አፈና አውግዛችሁ የሞራል ድጋፍ ለሰጣችሁን ኢትዮጵያውያን፤ እንዲሁም የአለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ተሟጋች ተቋማት ላሳያችሁት አጋርነትና ተቆርቋሪነት፣ በሀገሬ ላይ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ይሰፍን ዘንድ ዋጋ በከፈሉና እየከፈሉ ባሉ ወንድምና እህቶቼ ስም ልባዊ ምስጋናዬን ማቅረብ ነውና-ቺርስ ለነፃነታችን!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar