onsdag 6. mars 2013

ወታደሮች በኦጋዴን የውሀ ጉድጋዶችን በመያዝ ህዝቡን እያሰቃዩት ነው ተባለ


የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅት ለኢሳት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ሰራዊቱ እና የሶማሊ ልዩ ምልሻ በጋራ ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ የውሀ ጉድጓዶችን ተቆጣጥረው ህዝቡን ገንዘብ በማስከፈል እያሰቃዩት ነው።

ድርጅቱ ለአለማቀፍ ድርጅቶች ባሰማው የድረሱልን ጥሪ ሰራዊቱ በአንድ ሰው እና በእንስሳ ቁጥር ልክ ገንዘብ እያስከፈለ ነው።

አንድ ቤተሰብ ወደ ውሀ በወሰዳቸው ግመሎች፣ ፍየሎችና በጎች ልክ ለውሀው እንደሚከፍል የገለጠው መግለጫው በአማካኝ አንድ ቤተሰብ እስከ 12 ሺ ብር በወር የመክፈል ግዴታ ጠጥሎበታል ሲል አስታውቋል።

ከፍተኛ ድርቅ በተስፋፋበት ኦጋዴን እንዲህ አይነት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ መውሰድ በህዝቡ ላይ የሚፈጸም የዘር ማጥፋት እርምጃ በመሆኑ መንግስት ተጠያቂ መሆን እንዳለበት ድርጅቱ ገልጿል።

በተለይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአስቸኳይ ጣልቃ ገብቶ በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃ እንዲታደግ ድርጅቱ ጥሪ አቅርቧል።

በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው አስተያየት ለማግኘት ጥረት ብናደርግም አልተሳካልንም። የኦጋዴን አካካቢ አሁንም ከፍተኛ የጤር ቀጠና መሆኑ ይታወቃል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar