søndag 13. juli 2014

የተጣረሰ ትዕዛዝ የሚስተናገድበት ‹‹ፍርድ ቤት›› – በሌሉበት መዝገቡ ተዘጋ (ጽዮን ግርማ)

ሁለት ወር ከሃያ ቀናት በእስር ያሳለፉት ስድስቱ ጦማሪያንና (Bloggers) ሦስቱ ጋዜጠኞች በሦስት የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ በሰንበት ፍርድ ቤት ሲመላለሱ ከርመው በዛሬው ቀጠሮ በሌሉበት መዝገቡ ለዐቃቤ ሕግ መተላለፉ ተነገረ፡፡ለዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን ተቀጥረው የነበሩት ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስና፣የሕግ መምሕርና የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ዘለዓለም ክብረት ፣ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬና የዞን ጦማሪዎቹ ናትናኤል ፈለቀና አጥናፉ ብርሃነ በአጠቃላይ ስድስቱ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ብሎ እስከ ጠዋቱ አምስት ሰዓት ተኩል ድረስ ሲጠብቅ የነበረው ችሎት ተከታታይ በመጨረሻም ችሎቱ ማብቃቱ ተነግሮታል፡፡
ዞን 9
—————
ግንቦት ዘጠኝ-
በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡ ግንቦት ዘጠኝ ቀን 2006 ዓ.ም እያንዳንዱ እስረኛ ቤተሰቡን እዲያስገባ ተፈቅዶለት ነበርና ተስፋለዓለም ችሎት እንድታደም ስሜን በማስተላለፉ በጠባቧ ችሎት ቁጭ ብያለኹ፡፡ የዕለቱን የቀጠሮ መዝገብ ለመመልከት የተሰየሙት ወጣት ዳኛ ‘በእነ አጥናፉ መዝገብ’ በማለት የሦስቱ ተጠርጣሪዎች የአጥናፉ ብርሃነ፣ለናትናኤል ፈለቀና ኤዶም ካሳዬ መዝገብ አስቀርበው ከኹለት ቀጠሮ በኋላ ፖሊስ መዝገቡን ወደ ፀረ ሽብር ዐዋጁ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 28 የቀየረበጽ ቀን ነበር፡፤ በዚህም መሰረት ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ፈቅደው ‹‹እነ ዘላለም›› ሲሉ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስና የሕግ መምሕርና የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ዘለዓለም ክብረት የሚቀርቡበትን መዝገብ ተጣሩ፡፡
ነገር ግን ፖሊስ ቀርቦ እስረኞቹ በመንገድ ላይ ስለኾኑ ፍርድ ቤቱ እስከዛው ሌላ መዝገብ እየተመለከተ እንዲቆይ ጠየቁ፡፡ ዳኛው ሌሎች መዝገቦችን እየገለጡ ማየት ጀመሩ፡፡ ሦስተኛውን መዝገብ አነሱና ተጣሩ፡፡ የቀረበ እስረኛ የለም በድጋሚ ተጣሩ፡፡
ፖሊስ ብድግ አለ፤‹‹የተከበረው ፍርድ ቤት እኛ ምርመራችንን ጨርሰናል መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ አስተላልፈናል ስለዚህ ይኽኛው መዝገብ ይዘጋልን›› በማለት አመለከተ፡፡
ዳኛው ‹‹ተጠርጣሪው የታለ?›› ሲሉ ጠየቁ፡፡ ‹‹ማዕከላዊ ነው፤እስር ቤት ነው›› ሲል መለሰ -ፖሊስ፡፡
ዳኛው ተቆጡ፤‹‹እሱን እስር ቤት አስቀምጣችሁ ነው እዚህ መጥታችሁ መዝገቡን የምታዘጉት? እስከዛው የሚታሰረው በማን ትእዛዝ ነው?እስከዛሬ እንደዚህ ነው የምታደርጉት?›› ሲሉ ጠየቁ፡፡
ፖሊሱ ለመከራከር ሞከረ፤‹‹እኛ ምርመራ ስለጨረስን ለዐቃቤ ሕግ ሰጥተናል እንግዲህ መዝገቡ ላይ የሚወስነው ዐቃቤ ሕግ ነው›› አለ ቆፍጠን ብሎ፡፡
ይህን ጊዜ ዳኛው ጠረጴዛውን በእጃቸው አጩኸው መቱት፡፡ ‹‹እናንተ ምርመራችሁን ጨረሳችሁና መዝገቡን ዘጋችሁ መቼ ነው ፍርድ ቤት የምታቀርቡት?በማን ትዕዛዝ ነው አስራችሁ የምታቆዩት?የእርሱስ መብት አይከበርም?እስር ቤት እንደፈለጋችሁ ሰው አስራችሁ ታስቀምጣላችሁ?መዝገቡን ዘግተናል ስትሉ እስረኛውን እዚህ አቅርባችሁ የሚለው ነገር መሰማት የለበትም?መብቱ አይከበርም?እስከዛው የት ነው ታስሮ የሚቆየው? መቼስ ነው ፍርድ ቤት የሚቀርበው?ዋስትና የመጠየቅ መብቱስ›› ከከፍተኛ ብስጭት ጋራ ፖሊሱን አጣደፉት፡፡
በወቅቱም፤‹‹እኚህ ዳኛ ምን አለበት ‘በእነ አጥናፉ መዝገብ’ እንዲህ ቆራጥ በኾኑ?›› ስል መመኘቴም አልቀረም፡፡ እንዲያውም፤‹‹ምናልባት ‘በእነ አጥናፉ መዝገብ’ ሕጉ ሲጣስ እያዩ በሞያቸው ምንም ማድረግ አለመቻላቸው አንገብግቧቸው በዚህኛው እልሃቸውን እየተወጡ ይኾናል›› ስል ከወዳጆቼ ጋራ ተወያይቼበት ነበር፡፡ በመጨረሻም እያጉረመረሙ ‹‹እንደዚህ ማድረግ አትችሉም፡፡ እስረኛም መብት አለው እናንተ እንደፈለጋችሁ እስረኛ ማቆየት አትችሉም ሰኞ ይዛችሁ ቅረቡ›› በማለት ትዕዛዝ ሰጡ፡፡
ሐምሌ አምስት
በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡ መዝገቡም ለቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2006 ዓ.ም የተቀጠረው ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ ዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስና፣የሕግ መምሕርና የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ዘለዓለም ክብረት፣ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬና የዞን ጦማሪዎቹ ናትናኤል ፈለቀና አጥናፉ ብርሃነ በአጠቃላይ የስድስቱ ተጠርጣሪዎች ኹለት መዝገብ፡፡
እስረኞቹ ወትሮ ይቀርቡበት ከነበረው ሰዓት በእጅጉ ረፍዷል፡፡ ቆይታው ግራ ያጋባቸው ጠበቃው አቶ አመኃ መኮንን ኹኔታውን ለማጣራት ወደ ችሎት ገቡና ጠየቁ፡፡
‹‹ውይ አለቀኮ›› የሚል ምላሽ ተሰጣቸው፡፡ ግራ ተጋቡ እዛው ቁጭ ብለው እንዴት ያልቃል፡፡ በዛ ላይ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ደብቆ ወደ ችሎት የሚያስገባበት የተወሳሰበ ሕንጻ የለው ያለችው አንዲት አሮጌ የጓሮ በር ቤት በኩል ገብተው፡፡ ምላሹን ማመን የከበዳቸው አቶ አመሐ ‹‹እዚህ ውጪ ቁጭ ብለን እየጠበቅን እንዴት ነው አለቀ የሚባለው?›› ሲሉ ጠየቁ፡፡ ‹‹ስንጠራችኹ፣ስንጠራችኹ አልሰማችሁም››የሚል ምላሽ ተሰጣቸው፡፡ ችሎቱና ግቢው አፍና አፍንጫ በኾነበት አሮጌው ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ያኹሉ ሰው ቆሞ ሲጠሩ ሊሰሙ አለመቻላቸው አልዋጥ ስላላቸው፤‹‹ግቢ ውስጥ ከሦስት መቶ ሰው በላይ ተቀምጦ የእነርሱን ጉዳይ እየጠበቀ፤ጠበቃቸው እዚህ እያለ እንዴት አልሰማችኹም ይባላል?›› ብለው ቢጠይቁም ‹‹ጠበቃ አያስፈልጋቸውም ነበር›› የሚል ምላሽ ተሰጣቸው፤‹‹ተጠርጣሪዎቹስ መች ቀረቡ?›› ብለው ሲጠይቁም ‹‹እነርሱ አያስፈልጉም ነበር፤ፖሊስ ይህን መዝገብ ዘግቼ ጉዳዩን ለዐቃቤ ሕግ አስተላልፌያለኹ አለ በዛ መሰረት መዝገቡ ተዘጋ›› የሚል ምላሽ ተሰጣቸው፡፡
ሁለቱ ችሎቶች
ሁለቱ ዳኞች ግንቦት ዘጠኝም ሐምሌ አምስት የተሰየሙት በአንድ ችሎት ነው፡፡የተቀመጡበት ወንበርም አንድ ዓይነት ነው፡፡ የቀረበው ማመልከቻ ሐሳብም አንድ ዓይነት ነው‹‹ምርመራችንን ጨርሰናል ለዐቃቤ ሕግ አስተላልፈናል›› የሚል፡፡ውሳኔው ግን ሁለት ነው ያኛው ዳኛ ‹‹እስረኛን በጓሮ በር መቀባበል ወንጀል ነው›› ሲሉ ይኽኛው ዳኛ ደግሞ ሳያንገራግሩ ጥያቄውን ተቀብለዋል፡፡ የውሳኔው ውስጠ ወይራም፤‹‹ግዴለም እንዳሻችሁ ተቀባበሏቸው በፈለጋችሁት ቀንም ፍርድ ቤት አቅርቧቸው እስከዛው እንደፈለጋችሁ አድርጓቸው፡፡ ብትፈልጉ ቃሊቲ፣ብትፈልጉ ቂሊንጦ የፈለጋችሁበት አድርሷቸው ቤተሰቦቻቸውም ፈልገው ያገኟቸዋል፡፡›› ማለት ነው፡፡
ምን ዋጋ አለው እንደዛኛው ዳኛ ‹‹እናንተ ምርመራችሁን ጨረሳችሁና መዝገቡን ዘጋችሁ መቼ ነው ፍርድ ቤት የሚቀርቡት?እስከዛው በማን ትእዛዝ ነው ታስረው የሚቆዩት?የእነርሱስ መብት አይከበርም?በቃ እስር ቤት እንደፈለጋችሁ ነው አስራችሁ የምታስቀምጧቸው?መዝገቡን ዘግተናል ስትሉ እስረኞቹን አቅርባችሁ ጠበቃቸው ቀርቦ የሚያመለክቱት ነገር ካለ መሰማት አልነበረበትም?የዋስትና ጥያቄያቸው መሰማት አልነበረበትም?ከዚህ በኋላስ የሚታሰሩ ከኾነ እንኳን የት ነው ታስረው የሚቆዩት?ፍርድ ቤቱ ማወቅ የለበትም?›› በማለት የሚጠይቅ ሞጋች ዳኛ አልተገኘም፡፡ ለነገሩ ያኛው ዳኛም ይኸኛውን መዝገብ አጎንብሰው አልፈው በነጠላው መዝገብ ላይ ነበር ቀና ብለው የተቆጡት፡፡ የፍትሕ ሥርዐቱ እንደተዘባረቀ የሚቀጥለው እስከመቼ ይኾን?

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar