torsdag 31. juli 2014

እስላም እና ክርስቲያን የተከባበሩበት የኢድ በዓል – ኮልፌ ቀራንዮ

ባለፈው ሰኞ የኢድ በአል በሙስሊሞች በኩል ሲከበር፤ የዚያኑ እለት ደግሞ ማርያም የምትነግስበት እለት ነበር። በአዲስ አበባ ከተማ አጠገብ ላጠገብ ከተሰሩት መስጊድ እና ቤተ ክርስቲያን መካከል በኮልፌ ቀራንዮ ወረዳ 11 የሚገኙት የፊሊጶስ ቤተ ክርስቲያን እና የኢማም ሃሰን መስጊድ ይጠቀሳሉ። እናም ባለፈው ሰኞ የኢድ በአል ሲከበር በሁለቱ የእምነት ተከታዮች መካከል የታየው መተሳሰብ፤ በታሪካዊነት የሚጠቀስ፣ ለሌሎችም  ትምህርት የሚሆን ነውና… የሆነውን አጋጣሚ እዚህ ላይ ለመጥቀስ እንወዳለን።
እለቱ እንደኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች እምነት፤ ወር በገባ 21ኛው ቀን ማርያም የምትዘከርበት ነው። በመሆኑም ቅዳሴ እና ውዳሴ ማርያም በየቤተክርስቲያኑ ይከናወናል። እናም በኮልፌ ቀራንዮ በሚገኘው የፊሊጶስ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተገኙ የእምነቱ ተከታዮች እንደተለመደው የግቢ እና የውጭውን ስፒከር ከፍ አድርገው ቅዳሴ ያከናውናሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከዚያ አጠገብ የሚገኘው ኢማም ሃሰን መስጊድ የኢድ በአል ለማክበር በተዘጋጁ ሙስሊሞች መጨናነቅ ጀምሯል።
ትንሽ እንደቆዩ ሙስሊሞቹ መስገድ ሲጀምሩ እና ተክቢራ ማድረግ ሲጀምሩ ግን ብዙዎች ያልጠበቁት ነገር ሆነ። የፊሊጶስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ውጭ የሚሰማውን ስፒከር ዘግተው፤ የውስጡን ብቻ ለህዝበ ክርስቲያኑ በመክፈት በተመጠነ ድምጽ ቅዳሴያቸውን ማከናወን ጀመሩ። ይህም የሙስሊሞችን ስግደት እና ተክቢራ ላለማስተጓጎል የተደረገ ነገር ነበር።
ፊሊጶስ ቤተ ክርስቲያን ይህን ብቻ አልነበረም ያደረገው። ከሙስሊሙ እና ከመስጊዱ ጋር የሚያገናኘውን ዋናውን የቤተ ክርስቲያን በር በመዝጋት እና በሎሚ ሜዳ በኩል ያለውን የጓሮ በር በመክፈት ህዝበ ክርስቲያኑ የሙስሊሙን ስግደት እና ተክቢራ እንዳያስተጓጉል ትብብር ሲደረግ ታይቷል።
በኢ.ኤም.ኤፍ በኩል ይህ ዘገባ እንዲቀርብ የተፈለገበት ዋናው ምክንያት፤ አሁን ያለው መንግስት በሙስሊሙ እና ክርስቲያኑ መካከል ክፍፍል በመፍጠር እርስ በርስ በጠላትነት እንዲተያዩ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት የማይሰራ መሆኑን ለማሳየት ነው። በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አንዳንድ ሙስሊሞች ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በነሱ ላይ ጥላቻ እንዳላቸው አድርገው ልዩነቱን ለማስፋት የሚያደርጉትን ጥረት ለመከላከል ነው። እውነቱ ግን አንድ ነው። ኢትዮጵያውያን ሙስሊም እና ክርስቲያኖች “ሃይማኖት የግል” እንደሆነ ያምናሉ። እርስ በርስም ይከባበራሉ። አሁን ገዢዎች እንደሚሉት ሳይሆን፤ ከዚህ በፊት በነበሩት ታሪኮች ሁለቱም ወገኖች ተባብረው ሲሰሩ ታይተዋል። ቤተ ክርስቲያን ሲሰራ የረዱ ሙስሊሞች እንደነበሩ ሁሉ፤ መስጊድ ሲገነባ የገነቡ ክርስቲያኖችም ነበሩ። በፊሊጶስ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የታየው ትብብርም ይህንንኑ መከባበር እና ጨዋነትን የሚያድስ ነው።
ፋሲካ እና ገና ሲመጣ ክርስቲያኖችን “እንኳን አደረሳቹህ” የሚሉ ሙስሊሞች እንዳሉ ሁሉ፤ የረመዳን ጾም አብቅቶ ኢድ ሲመጣ “ኢድ ሙባረክ” በማለት ለሙስሊሞች መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹ፤ ብሎም እርስ በርስ የሚገባበዙ ኢትዮጵያውያን በርካቶች ናቸው። ይህንን መከባበር እና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ለልጆቻችን ልናወርስ ይገባል እንጂ፤ ገዢዎች እንደሚፈልጉት በሃይማኖት ልነከፋፈል አይገባም – የዛሬው መልእክታችን ነው። ቢዘገይም “ኢድ ሙባረክ” ብለናል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar