søndag 12. oktober 2014

ማኅበረ ቅዱሳን ይፈርሳል? ይህን ማኅበር ሚገዳደሩት እነማን ናቸው? (በካሌብ ብርሃኑ)


ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ክርስቲያኖች መካከል የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ የሰነበተው የማህበረ ቅዱሳን ጉዳይ ነው። ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ የማህበረ ቅዱሳን ጉዳይን ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርበው ተነጋግረውበት ነበር። ሆኖም ቅዱስ ሲኖዶሱ በማህበረ ቅዱሳኑ ላይ ጠንካራ ተቃውሞ አላቀረበም፤ ወይም እርምጃ አልወሰደም። በመሆኑም ፓትርያርኩ እታች ወርደው የቤተ ክርስቲያኑ ሌሎች አመራሮች ጋር ስብሰባ አደረጉ። የስብሰባው አጀንዳ በቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር ውስጥ ስላለው የመልካም አስተዳደር እጦት ነበር። ሆኖም ስብሰባው ሲጀመር መስመሩን እየለቀቀ ሁሉም በማህበረ ቅዱሳን ላይ የጭቃ ጅራፍ ያወርድበት ጀመር።
በስብሰባው ላይ የተገኙት ሰዎች ማህበረ ቅዱሳንን ከአሸባሪ አካላት ጋር በማያያዝ ሃሳባቸውን ሲገልጹ ሰምተናል። የማህበረ ቅዱሳን የባንክ አካውንት እንዲዘጋም የጠየቁ ነበሩ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ልዩነት ካለ በልዩነት ዙሪያ መነጋገር ሲቻል፤ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን አባላት የጽናት መሰረት የሆነውን ማህበረ ቅዱሳንን “አሸባሪ” ብሎ ስም መስጠት በጣም አሳፋሪ እና አግባብ ያልሆነ ተግባር ነው። አሸባሪ የምትለዋን ቅጽል ይዘው ማህበሩን ሲያብጠለጥሉት ቆዩና በሚቀጥሉት ቀናት “የማህበረ ቅዱሳን የባንክ አካውንት ተዘጋ” የሚለውን ዜና ሰማን። እስካሁን ያልሰማነው “የማህበረ ቅዱሳን አመራሮች በአሸባሪነት ታሰሩ” የሚለውን ነው። ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ግን የመታሰራቸውን ዜና የምንሰማበት ግዜ እሩቅ አይሆንም።
እንግዲህ ሰሞኑን በዚህ አሳዛኝ እና አስደማሚ ዜና እየሰማን ቆየን። ምናልባት ማህበረ ቅዱሳን በዚህ ጉዳይ መግለጫ ይሰጥ እንደሆን ብለንም ጠበቅን። ምንም የሰማነው ነገር የለም። ሆኖም ስለማህበረ ቅዱሳን የሰሞኑ ጉዳይ አጸፋዊ መልስ ባይሆንም ማብራሪያ የተሰጠበት አንድ ጽሁፍ ደረሰን። የጽሁፉ አቅራቢ ካሌብ ብርሃኑ ይባላል። ግላዊ እይታውን አቅርቧል። እናም ይህ በትንሹም ቢሆን የማናውቀውን ያሳውቀናልና ጽሁፉን ልናጋራቹህ ወደድን። ከዚህ በታች ያንብብቡት።
ማኅበረ ቅዱሳን ይፈርሳል? ይህን ማኅበር ሚገዳደሩት እነማን ናቸው? በካሌብ ብርሃኑ (ግላዊ እይታ)
የብዙ ወንድሞች እና እህቶች ጥያቄ ነው፤ እስኪ የኔን አስተያየት ላቅርብ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ማለት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደተነገረው (አንዳንዶች ሰምተው እንዳልሰሙ፤ አንብበው እንዳላነበቡ፤ አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም ብለው ተርተው አልሰማንም አሉ እንጂ) የቅዱሳን ስብስብ ሳይሆን ቅዱሳን ተጋድሎአቸው የሚዘከርበት፤ የመንፈስ ልጆቻቸውም አሰረ ፍኖታቸውን የሚከተሉበት የአገልግሎት ማኅበር ነው፡፡ ቢሆንም ቅሉ ብዙ ሰዎች እዚህ ማኅበር ላይ ቂማቸው እና ጥላቻቸው እየጨመረ መሄዱ የእለት ተእለት ተግባራቸው ለአንዳንዶችም መተዳደሪያ ስራቸው ሆኗል ፡፡ እኔ በግሌ ማኅበሩን ለምን ጠሉት አልልም መውደድና መጥላት የነሱ ነፃ ፈቃድ ነው፤ (እስከማውቀውም ድረስ ማኅበሩ ለመወደድ ብሎ ሲሰራ አላጋጠመኝም)፡፡ በመሆኑም የነዚህ ሰዎች ጥላቻ ማኅበሩን ያፈርሰዋል ወይ ወደሚለው የብዙዎች ጥያቄ ላምራ፤ ይህን ጥያቄ ለመመለስ መጀመሪያ ማኅበሩ ምንድነው ፤ የመጨረሻ ግቡስ የሚሉትን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ምንድን ነው?
ይህን ለመመለስ ከተመሰረተ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየሰራ የለውን ሥራ በተጨባጭ መረጃ መገምገም ቀላሉ መፍትሔ ነው፡፡ በብዙ ቦታዎች እንደተገለፀው ማኅበሩ ሲቋቋም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝ ተማሪዎችን በመንፈሳዊ ህይወት አንፆ ማሳደግ በዓለማዊውም ትምህርታቸው ጠንካራ ኦርቶዶክሶችን ማፍራት በዚህም በስነ ምግባር የታነፁ ዜጎችን ለኢትዮጵያና ለኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ማበርከት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተማሩ ሰዎች ስብስብ እንደመሆኑም መጠን ቤተ-ክርስቲያኗ በተለይም ገዳማቶቿ የእውቀት እና የነገ ቤተ-ክርስቲያን መሪዎች መፍለቂያ እንደመሆናቸው መጠን ከ እርዳታ እና ከ ጥገኝነት ተላቀው እራሳቸውን የሚችሉባቸውን ፕሮጀክቶች በመንደፍ እና ተግባራዊ በማድረግ እንዲሁም የተዘጉና የተዳከሙ የ አብነት ትምህርት ቤቶችን በማጠናገር እና በማስከፈት መምህራንና ተማሪዎችንም ስፓንሰር በማድረግ ለተፈለገው የቤተ-ክርስቲያን አገልግሎት እንዲበቁ የማድረግን ስራ መስራት ነው፡፡ ማኅበሩ ሲቋቋም እንደ ሌሎች ማኅበራት በሰዎች ስምምነት ብቻ ሳይሆን በቤተ-ክርስቲያኗን ከአምላክ ቀጥሎ የመጨረሻ አዛዥ በሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ መተዳደሪያ ደንብ እና ቡራኬ የተሠጠው፤ ለዚህ አገልግሎቱም ከቤተ-ክርስቲያኗ መዋቅር ስር ሆኖ የሚያገለግል የ አገልጋዮች ማኅበር ነው፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ግን ይህ ከላይ የተገለፀው ብቻ አይደለም ባለፉት ሀያ ሁለት አመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ እንደመሆኑ አንፃር በብዙ አባቶች እንዲሁም አገልግሎቱን ቀና እንነት በተገነዘቡ ሰዎች “የቤተ-ክርስቲያን የችግር ጊዜ ልጅ” የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል፡፡ ይህ የተባለበት ምክንያት ደሞ አጽራረ ቤተ-ክርስቲያኖች የመነኩሴ ቆብ ለብሰው ህዝቡን ሊያወናብዱ “ቤተ-ክርስቲያኗ አርጅታለች እናድሳታለን” እያሉ በየአዳራሹ በሚበጠብጡበት ጊዜ ተከታትሎ ጉዳዩን ለቤተ-ክርስቲያኗ የበላይ አካላት (ቅዱስ ሴኖዶስ) በማስረጃ በማቅረብ አባቶች ውሳኔ እንዲሰጡ በማድረጉ እና አለማዊውን ትምህርት በከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያጠናቀቁ ክህናት ሙህራንን ለ ቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት በማቅረቡ ነው፡፡ ይህ ደሞ ኢንጅነሮቻችን በነፃ ዲዛይን በሚያደርጓቸው ቤተ-ክርስቲያኖች፤ ምሁራኖቻችን በሚያቀርቧቸው የጥናት እና ምርምር ስራዎች ውስጥ የሚታይ መሬት ላይ የወረደ እውነት ነው፡፡
በአሁኑ ስዓት ማኅበረ ቅዱሳን ማለት ይህ ማለት ብቻ አይደለም ምክንያቱ ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን ከአገልጋዮች ስብስብነት ወደ እሳቤ (ideology) አዊነት ስለተሸጋገረ ነው፡፡
ይህን ስል ምን ለማለት ፈልጌ እንደሆነ በምሳሌ ልግለፅ ፡-
ከጥቂት ወራቶች በፊት እንዲህ ሆነ በአውሮፓ ሀገር የምትኖር እህት በቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ከኦርቶዶክሳዊ ስርአት ውጪ የሆነ ስራ ሲሰራ አይታ “ለምንድነው እንደዚህ ሚሰራው ከ አባቶች ያልወረስነው በመፅሐፍም ያልተፃፈ ከ ቤተ-ክርስቲያናችንም ትውፊት ውጪ የሆነ ሥራ ለምን ይሰራል ብላ ትጠይቃለች” በዚህ ሰዓት ይህቺ እህት አንቺ እማ ማኅበረ ቅዱሳን ነሽ ሚል ታፔላ ይለጥፉባታል ፤ ማኅበሩ ከነመፈጠሩ የማታውቀው እህት ይህ የተሰደብኩበት ማኅበር ማን ነው ብላ ማፈላለግ ትጀምራለች በመጨረሻም ወደ ኢትዮጵያ በምትመጣበት ወቅት ብዙ ጥናቶችን በማኅበሩ ላይ ካደረገች በኋላ ወደ ስራ አስፈፃሚ ቢሮ ቀርባ የታማሁባችሁ እናንተ የቤተ-ክርስቲያን ተስፋ ናችሁ በማለት ቤተ-ክርስቲያን ሥርዓት ሚፈፀምባቸውን መንገዶች እንድ ማሳያ ፕሮጀክት በመንደፍ የፕሮጀክቱን ማስፈፀሚያም አስተዋፅኦ በማድረግ ወደ አገልግሎቱ ገባች፡፡ ከዚህ ታሪክ የምንረዳው ነገር ስርዓት ሲጣስ የሚጠይቅ ፤ ስለቤተ-ክርስቲያን ፍቅር ልቡ የሚነድ እና ሲለሚፈፀምባት በደል የሚታመም መፍትሄም የሚፈልግ ሰው እሱ ማኅበረ ቅዱሳናዊ ነው ወደሚል መደምደሚያ እየተዞረ መሆኑን ማሳየት ነው ይህ ደሞ በማኅበሩ አባላቶች የተገለፀ ሳይሆን፤ በግልባጩ ቤተ-ክርስቲያኒቷን ለማውደም ከሚንቀሳቀሱ አካላት የመጣ እውነታ ነው፡፡
የማኅበሩ የመጨረሻ ግብ፡-
የማኅበሩ የመጨረሻ ግብ ምንድነው? ወደሚለው ጥያቄ እንዙር፤ ማኅበሩ በግልፅ እንዳስቀመጠው “ቤተ-ክርስቲያን የመሪነት ቦታዋን ማስመለስ” ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው ብዙ ሰዎች ይህን ሲሰሙ ሊደናገጡ ይችላሉ ፤ አንዳንዶችም በስልጣናቸው የተመጣባቸው ሰለሚመስላቸው ማኅበሩን ለማጥፋት ጉድጓድ ሲቆፍሩ ይታያሉ (አጥልቃችሁ አትቆፍሩት ….) ፤ ቤተ-ክርስቲያንን የመሪነት ቦታዋን ማስመለስ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ባጭሩ ላቅርብ፡፡
ቤተ-ክርስቲያን በቀደምት ዘመናት የነበራት ቦታ አለ ይህም የተሰሚነት ፤ አገርን የማገልገል ፤ “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀመዛሙርቴ አድርጓቸው” የሚለውን የአምላኳን ትእዛዝ መፈፀም ፤ በልማትና እርዳታ ከፍተኛ ቦታ ላይ መድረስ ወደምትችልበት ቦታ ማድረስ መቻል ማለት ነው፡፡
ታዲያ ይህን ማኅበር ሚገዳደሩት እነማን ናቸው?
1. መንግሥት ፡-
መንግሥት እንደ አስተዳዳሪነቱ ሁሉም ነገሮች (በተለይም የምሁራን ስብስብ) ያስፈራዋል በተለይ ደግሞ ብሔር ተኮር ለሆነ የገዢ ስርዓት ስለ አንድነት የምታስተምር ቤተ-ክርስቲያን ፈተናው ነች፡፡ ለዚህም ማሳያው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእስራኤላውያን ዘር ቢመጣም በፊቱ ቀለም ሳይሆን ባፈሰሰው ደም አለምን አድኗል፡፡ መልካችን ቢለያይም ደማችን ግን አንድ ነው ብላ ማስተማሯ መንግስት ከ በረሃ ጀምሮ ጥርሱ ውስጥ እንድትገባ አደርጓታል፡፡ ይህን አስተምህሮቷን ለማዳከም በሚሰራቸው ስራዎች ውስጥ ደሞ ቤተ-ክርስቲያኒቷን ሊያጠናክሩ የሚችሉ አካላትን ማጥፋት ካልተቻለ ማዳከም ሁነኛ መፍትሔው ነው፡፡
2. አፅራረ ቤተ-ክርስቲያናት፡-
እነዚህ አካላት ደሞ ቤተ-ክርስቲያኗን ለማፍረስ ምእመናኖቿንም ለመረከብ ብዙ የሚለፉ የእምነት ድርጅቶች ናቸው፡፡ በተለይም በቤተ-ክርስቲያኗ መዋቅር ውስጥ በመግባት ተሐድሶን እናደርጋለን የሚሉ ቅጥር ፕሮቴስታንቶች ሲሆኑ በኦርቶዶክስ ማልያ ለሌላ ቡድን ሚጫወቱ ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት የሉም እያሉ በየቦታው ቢያስነግሩም በየእጆቻችን ያሉት መረጃዎች ይህን አያመላክቱም፡፡ ይባስ ብለው እነዚህ ሰዎች መፃህፍትን እና ቪዲዮችን በመልቀቅ አለን እናድሳታለንም እያሉ ሲፎክሩ ይታያሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች እንደነበራቸው እቅድ በ ሚሊኒየሙ (2000 ዓ.ም) ሙሉ በሙሉ ቤተ ክርስቲያኗን እንረከባታለን ብለው እቅድ ቢያወጡም ሊሳካላቸው አልቻለም ፡፡የዚህን ምክንያትም ሲናገሩ ማኅበረ ቅዱሳን የሚባል የወጣት ሙህራኖች ስብስብ እንቅፋት እንደሆነባቸው ያስረዳሉ በመሆኑም በሚቀጥለው ስትራቴጂያቸው በቻሉት አቅም ቤተ-ክርስቲያኗን ለመረከብ ማኅበሩን ማጥፋት ካልቻሉ ደግሞ ማዳከም ሁነኛ መፍትሔ ነው፡፡
3. ጥቅማቸው የተነካ የቤተ-ክርስቲያኒቷ አካላት ፡-
እነዚህ አካላት ቤተ-ክርስቲያኒቷ ላይ ኑራቸውን ጥገኛ ያደረጉ ነገር ግን ከሚገባቸው በላይ የቤተ-ክርስቲያኒቷን ንብረት ለመቀራመት የሚተጉ ፤ ምንኩስናን እና ቅስናን ክፍት የስሥራ ማስታወቂያ ያደረጉ የቤተ-ክርስቲያኗ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ከ ሰበካ ጉባኤ አባልነት እስከ ቤተ-ክርስቲያኗ ከፍተኛ የስራ አመራር ደረስ የተሰገሰጉ ቡድኖች ሲሆኑ ፤ ማኅበሩ እያደረገ ያለው አገልግሎት የነሱን ጥቅም የነካ (የሚነካ) የመሰላቸው (የነካባቸው) አካላት ናቸው፡፡ ለዚህም ነው የማኅበሩን አገልጋዮች ባዩ ቁጥር “ባለ ድግሪው ሊቀድስ መጣ” እያሉ ሚጨነቁት ምክንያቱ ደሞ የማኅበሩ አገልግሎት መርህ ቤተ-ክርስቲያንን በ ገንዘብ በጉልበት እና በእውቀት ማገልገል በመሆኑ ሚሰራቸው እያንዳንዳቸው አገልግሎቶች ለቤተ-ክርስቲያን በነፃ ሚደረጉ ሲሆን እነዚህ አካላት ደሞ በቤተ-ክርስቲያኗ ተከፋይ (ሊያውም ከሚገባቸው በላይ) በመሆናቸው ነው፡፡ ተከፋይ ስል በቤተ-ክርስቲያን በ አገልግሎት ለሚሳተፉ መደበኛ አገልጋዮች ሚከፈላቸውን ደሞዝተኞች አለመሆኑ ይተወቅልኝ፡፡ ይልቅስ አንዲት ፕሮጀክት ለመተግበር የ አስር ፕሮጀክት ብር የሚበሉትን ለማጠየቅ ነው፡፡ እናም እነዚህ አካላት ተደላድለው የቤተ-ክርስቲያኒቷን ሃብት ለመብላት ማኅበሩን ማጥፋት ካልቻሉ ደግሞ ማዳከም ሁነኛ መፍትሔአቸው ነው፡፡
4. ማኅበሩን ባለማወቅ እንቅፋት የሚሆኑ፡-
እነዚህ አካላት ስለማኅበሩ ምንም ባለማወቅ ወይም ከላይ የተገለፁትን አካላት እንደ መረጃ ምንጭ በመውስድ ለማኅበሩ እንቅፋት የሚሆኑ አካላት ናቸው፤ በዚህ ምክንያትም አንዳንዶች ማኅበሩን የተሐድሶ መነሻና መድረሻ አድርገው የሚያስቡ ሆነዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ማኅበሩ ከ ሰንበት ት/ቤቶች ጋር ፉክክር የገባ የሰንበት ት/ቤቶችን ለመብለጥ (ለማዘዝ) የተቋቋመ እየመሰላቸው ማኅበሩን ለመጣል ብዙ ሲለፉ እናያቸዋለን፡፡ እነዚህ ወገኖች ሁላችንም አንዲት ቤተ-ክርስቲያን ለመገንባት የምንጥር መሆናችንን አልተረዱም፡፡ ይልቅም ማኅበሩ ከብዙ ሰንበት ት/ቤቶች ጋር በጋራ ስለሚሰራቸው ስራዎችም እንዲሁም ሰንበት ት/ቤቶችን ለማጠናከር የሚሰራውን ስራ አልተገነዘቡም፡፡ የዚህም ማሳያው የሰንበት ት/ቤቶችን መጠናከር ሲመለከቱ “እሰይ ከማኅበረ ቅዱሳን እየበለጡ ነው” እያሉ በየመድረኩ የሚሰጡት ያላዋቂ አስተያየት ነው፡፡
ይህን ያህል ማኅበሩን ሊያጠፉት (በማወቅም ሆነ ባለማወቅ) ስለ ሚጥሩት አካላት ከገለፅን እውን ማኅበሩን ማጥፋት ይችላሉ ወይ? ወደሚለው የመጨረሻ ጉዳይ እንሂድ፡፡
ማኅበሩን ሊያጠፉት አይችሉም!!!፡፡ እንደምን እንደማይችሉ በትንሹ ልግለፅ ፤ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ማኅበሩ አሁን የአገልጋዮች ስብስብ ብቻ ከመሆን ዘሎ ኦርቶዶክሳዊ እሳቤ (ideology) ወደ መሆን ተሻግሯል፡፡ እነዚህ ሰዎች ማኅበረ ቅዱሳናውያን ብለው ሚያስቡት በአባልነት የተመዘገቡትን ከ 60,000 በላይ አባላት ሊሆን ይችል ይሆናል ነገር ግን አሁን ከዛም አልፏል፤ ማኅበረ ቅዱሳናዊነት በያንዳንዱ ለቤተ-ክርስቲያን ይገባኛል በሚል ኦርቶዶክሳዊ ውስጥ ያለ አስተሳሰብ ነው፡፡ ቤተ-ክርስቲያኔን ባለኝ ነገር ሁሉ ላገልግል በሚል ኦርቶዶክሳዊ ውስጥ ያለ አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህን ደሞ ተቋሙን በማፍረስ ማጥፋት የሚቻል አይደለም፤ ብዙዎች ማኅበሩ አሁን ካለበት የአደረጃጀት ስርአት ቢበተን የልባቸው የሚሳካ ይመስላቸዋል፡፡ በጣም ትልቅ ስህተት ነው ምክንያቱም አሁን እንደሚታየው ማኅበሩ ላይ ያሉት አባላት በአንድ መዋቅር ስር የተሰበሰቡ ናቸው ይህ ደሞ ተወደደም ተጠላም ለነዚህ አገልጋዮች የሚያስቀምጥባቸው ድንበር (limitation) አለ፤ ይህን መዋቅር መበተን ግን እነዛን ሰዎች ያለ ምንም ድንበር አገልግሎት ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችል ሌላ ትልቅ የአገልግሎት በር መክፈት ነው፤ ይህ ደሞ እያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ወደ ቤተ-ክርስቲያን እንዲመለስ እና በትጋት እንዲያገለግል የሚያደርግ ጥይት መተኮስ ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ሊፈፀም የሚችለው አንድ እና አንድ ነገር ብቻ ነው እያንዳንዱ ሰንበት ት/ቤት እና ሰበካ ጉባኤ ማኅበረ ቅዱሳናዊ እሳቤን ወደመያዝ ይዞራል ያኔ “በተንን” የሚሉት መዋቅር ሺ ጊዜ ጠንክሮ እና አብቦ ይመጣል፡፡ it’s just a win win scenario.

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar